ፈልግ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የዕርገት በዓል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የዕርገት በዓል 

የዕርገት በዓል

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ ሐዋርያቱን ሲያጽናናቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሲነግራቸው ከእነርሱ ጋር አርባ ቀን ከቆየ በኋላ ወደ ሰማይ ወጣ። ለመጨረሻ ጊዜ ሲታያቸው በዓለም ሁሉ ሄደው ወንጌልን እንዲሰብኩ ተማጸናቸው። እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ በመንፈስ ከእነርሱ ጋር ሆኖ እያገዛቸው እንደሚቆይ ተስፋ ሰጣቸው። ከዚህ በኋላ ይዟቸው ወደ ቢታንያ ሄደ።

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብርአቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ደብረ ዘይት ሲደርሱ እጁን አንሥቶ ባረካቸው። ይህን ካደረገ በኋላ እያዩት ከምድር ከፍ አለ ደመናም መጥቶ ከዓይናቸው ሰወረው። ወደ ላይ እየተመለከቱ ሳለ ሁለት ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሰዎች መጥተው «እናንተ የገሊላ ሰዎች ስለምን ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ቆማችኋል? ይህ ወደ ሰማይ ሲወጣ ያያችሁት ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲወጣ ባያችሁት ዓይነት ተመልሶ ይመጣል»(ማር.11፣19፣ ሉቃ. 24፣51፣የሐዋ.1፣11) አሉዋቸው።

ክርስቶስ ወደ ምድር ሲወርድ በትሕትና እንደወረደ ወደ ሰማይ ሲመለስ በክብር ተመለሰ። «እግዚአብሔር በአጀብ ወጣ፤ ጌታችን በመለከት ድምጽ ወጣ» (መዝ. 46፣5) ይላል ዳዊት። ከዚህ ሁሉ ውርደትና ስቃይ በኋላ ክብር ይገባው ነበር። በደስታ ወደ ሰማይ ሊወጣ ያስፈልገው ነበር። ስለዚህ በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ወጥቶ በአባቱ በአብ ቀኝ ተቀመጠ። ሐዋርያት በመሄዱ እንዳዘኑ ሲያያቸው ወደ ሰማይ በመመለሱ እንደማይረሳቸውና ስለ ጥቅማቸው እንደሆነም ነገራቸው። «ልባችሁ አይደንግጥ በአባቴ ቤት ብዙ ሥፍራ አለ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ» (ዮሐ. 14፣1) አላቸው።

እንደ ተናገረው ደግሞ አደረገው። ዕርገቱ ለሐዋርያት ብቻ ሳይሆን ለአዳም ልጆች ሁሉ ትልቅ ጸጋ ሆነ። ወደ ሰማይ በተመለከተ ጊዜ በአዳም ኃጢአት ተዘግቶ የነበረው መንግሥተ ሰማያት ተከፈተ። በአጀብ ወደ መንግሥተ ሰማያት ሲገባ እነዚያ በትልቅ ተስፋ በሲኦል ሆነው ይጠብቁት የነበሩ ጻድቃን ከእርሱ ጋር ገቡ። በመንግሥተ ሰማያት ትልቅ በዓል ሆነ። የሰው ልጅ ከብዙ ዘመን በኋላ ከፈጣሪው ጋር ፊት ለፊት ተያየ። ዕርገቱ ለሞቱ ጻድቃን ብቻ ሳይሆን በሕይወት ላሉትም የበረከት ምንጭ ሆነ። እርሱ ሥራውን ጨርሶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ሲወጣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ሥራውን ሊያሟላ ወደ ምድር ወረደ።

በክርስቶስ ዕርገት መንግሥተ ሰማያት ተከፈተልን መንፈስ ቅዱስ መጣልን። ዕርገቱ ዕርገታችን፣ መንፈሱ መንፈሳችን መሆን አለበት። ከኃጢአት ርቀን በእግዚአብሔር መንፈስ መኖር ይገባናል። «በኋላ ጊዜው ሲደርስ እስከምናየው ድረስ በልባችን ከእርሱ ጋር እንሁን። ግን ከክርስቶስ ትዕቢት፣ ንፉግነት፣ ዝሙት፣ ማንኛውንም ክፋት በእርሱ እንዳልተገኘበት ማወቅ አለብን። ከክርስቶስ ከእውነተኛ መድኃኒታችን ጋር ከዚህ መጥፎ አመል እንድንላቀቅ አመላችንንና ኃጢአታችንን መተው አለብን» ይላል ቅዱስ አውጎስጢኖስ። የክርስቶስ ዕርገት ዕርገታችን እንዲሆን ከፈለግን በምድር ሳለን እንዘጋጅ፣ ኑሮአችን ከኃጢአት ኑሮ እንዲለይ መንፈሳዊ እንዲሆን ያስፈልጋል። ልባችን ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲያዘነብል ያስፈልጋል። ክርስቶስ ያሰናዳልንን ሥፍራ ለማግኘት ለእርሱ የሚበቃ የጽድቅ ሥራ እናድርግ።

ኃይል ከላይ እስኪመጣላችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲመጣ ለሐዋሪያቱ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልካቸው ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። መንፈስ ቅዱስን እንዲጠብቁ አደራ አላቸው። «መንፈስ ቅዱስን አልክላችኋለሁ። እናንተም ከላይ ኃይል እስኪሰጣችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ (ሉቃ. 24፣49) አባቴን ዘወትር ከእናንተ ጋር የሚኖር አጽናኙን መንፈስ ቅዱስ እንዲልክላችሁ አለምነዋለሁ´ (ዮሐ. 14፣15) «ከሰማይ የሚወርድ ኃይል ትቀበላላችሁ»(ዮሐ 1፣8 ) አላቸው። ቀጥሎም ደግሞ «እኔ ብሄድ ይሻላችኋል። ምክንያቱም እኔ ካልሄድኩ መንፈስ ቅዱስ አይመጣላችሁም። እኔ ከሄድኩ ግን እልክላችኋለሁ» (ዮሐ 16፣67) እያለ ተናገራቸው። ኢየሱስ ከዓይናቸው ሲሰወር ሐዋርያት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ልክ መምህራቸው እንዳላቸው በጽርሐ ጽዮን ተሰበሰቡ። እዚህም በጽሞና፣ በጸሎት፣ በተጋድሎ መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል ተዘጋጁ።

በየዓመቱ ይህ የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ይደጋገማል። ለዚህ በዓል እንዘጋጃለን። እንዴት አድርገን እንጠብቀዋለን? በምን ዓይነት መንፈስ እንዘጋጅለታለን? አባቶቻችን ሐዋርያት በጥሩ ስለተዘጋጁ መንፈስ ቅዱስ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ ኃይል ሰጣቸው። የልባቸውንም ምኞች ሞላላቸው። አዲስ መንፈስ አለበሳቸው። በኃይሉ የድሮ ሕይወታቸውን ትተው አዲስ የሚያንጽ የክርስትና ሕይወት ያዙ። እኛ ግን በዚህ ቀን መንፈስ ቅዱስ አንድ ነገር ሳይሰጠን ያልፋል። መንፈሳችን እንደ መጀመሪያው ሳይታደስ ይቀራል። ጳራቅሊጦስ በመንፈስ እንደ ማንኛውም የአዘቦት ቀን ሆኖ ያልፋል።

ይህን የመንፈስ ቅዱስ በዓል ለምንድነው ሳንጠቀምበት በጸጋ ላይ ጸጋ ሳንቀበል፣ በመንፈስ ሳንነቃቃ የሚያልፈው; እንደ ሐዋርያት በሚገባ በጽሞና፣ በጸሎት፣ በተጋድሎ የማንዘጋጅ ስለሆነ ነው። ለጳራቅሊጦስ በዓል አንጨነቅም። እንደ ማንኛውም ተራ በዓል አድረገን እንቆጥረዋለን፣ በቸልተኝነት በቀዘቀዘ እምነት እናከብረዋለን። ይህም ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን ሀብቶች እንደ ትልቅ ነገር አድረገን እንደማናያቸው ይገልጻል። እንዴት ያለ ደካማ መንፈስ ነው መንፈስ ቅዱስ እንደ ዝግጅታችን ይክሰናል እንደ ስንፍናችን ይተወናል።

ቸልተኝነትን አንጥላ፣ እንደ ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን መምጣት በጽሞና በጸሎት፣ በተጋድሎ በመጠበቅ መንፈሳችንን እናዘጋጅ።

 

15 June 2024, 16:12