ፈልግ

በድሮን የተነሳው ምስል ላይ በኢራቅ ከተማ በሆነችው  ሞሱል የሚገኘው የአል-ታሂራ ቤተክርስትያን የጥገና ሥራ ሲሰራ ያሳያል በድሮን የተነሳው ምስል ላይ በኢራቅ ከተማ በሆነችው ሞሱል የሚገኘው የአል-ታሂራ ቤተክርስትያን የጥገና ሥራ ሲሰራ ያሳያል 

ጥቂት የክርስትና እምነት ተከታይ ኢራቃዊያን ከ10 ዓመታት በኋላ ወደ ሞሱል ተመለሱ

እስላማዊ መንግሥት እየተባለ የሚጠራው ቡድን ኢራቅን እና ሶሪያን በመውረር አከባቢዉን ካተራመሰ ከ10 ዓመታት በኋላ ሞሱል ከተማ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የተመለሱት በጣት የሚቆጠሩ ክርስቲያን ቤተሰቦች እንደሆኑ ተዘግቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከአሥር ዓመታት በፊት በሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት እና በዓመፅ ምክንያት የኢራቅ ከተማ በሆነችው ሞሱል ውስጥ የሚገኘውን ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት ከተገደዱ በርካታ ክርስቲያኖች መሃከል ወደ ቤታቸው የተመለሱት በጣም ጥቂት ክርስቲያን ቤተሰቦች ናቸው።

በሞሱል የቻልዳውያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ አሜል ሺሞን ኖና እንዳሉት 1,200 የሚሆኑ የክርስትና እምነት ተከታይ ቤተሰቦች እስላማዊ መንግሥት (አይ ኤስ) የሚባለው ቡድን ባደረሰው ጥቃት ከሞሱል ከተማ ለቀው መውጣታቸውን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ከቫቲካን የፊደስ ዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ እሳቸውና ካህናቶቻቸው በጦርነቱ ወቅት በነነዌ ክልል ውስጥ በሚገኙ እንደ ክራምለስ እና ቲልኪፍ ባሉ መንደሮች ተጠልለው የነበሩትን ተፈናቃዮች ይጎበኙ እንደነበር አስታውሰዋል።

በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያታውሱ “ለመንፈስ ቅዱስ የተሰጠችው ቤተክርስቲያናችን ከተማዋ በአይ ኤስ ቁጥጥር ሥር በገባችበት ወቅት በዘራፊዎች ቡድን ተዘርፋለች፥ ነገር ግን በአቅራቢያው የሚኖሩ የሙስሊም ቤተሰቦች እስላማዊ ሚሊሻዎችን በመጥራት ጣልቃ በመግባት ዘረፋውን አስቁመውታል” ብለዋል ሊቀ ጳጳስ ኖና።

አይ ኤስ ቤቶቻቸውን ለመቀማት ለይቶ ‘ምልክት’ ካደረገበት በኋላ በርካታ ክርስትያኖች በገፍ መሰደድ እንደጀመሩ እና ሁለት መነኮሳት እና ሶስት ወጣቶች በጂሃዲስቶች ለጊዜው ታግተው እንደነበርም አብራርተዋል።

ብጹእነታቸው እንደገለጹት ጥር 2007 ዓ.ም. የአይኤስ ወታደሮች ክርስትናን ክደው እስልምናን አንቀበልም በማለታቸው አስር አረጋውያን የቻልዳውያን እና የሶሪያ ካቶሊክ ክርስቲያኖችን ከሞሱል ማባረራቸውን አስታውሰዋል።

ሰኔ 2007 ዓ.ም. ላይ አይ ኤስ የኢራቅን አንድ ሶስተኛውን እና የሶሪያን ግማሽ ያህሉን እንደተቆጣጠረ ብሎም ሊቢያንም ሲያተራምስ እንደነበር እና በመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ውስጥ በደርዘን የሚቆጠሩ የታጠቁ ቡድኖች አባልም እንደነበር ይታወሳል።

በ 2009 ዓ.ም. ታጣቂዎቹ ለረዥም ጊዜያት ከተደረገ ጦርነት በኋላ ራሳቸው የኢራቅ ዋና ከተማ ናት ብለው ባወጁባት ሞሱል ከተማ ላይ ተሸንፈዋል።

ቻልዳዊው የአልቆሽ ጳጳስ ፖል ታቢት መኮ ለፊደስ እንደተናገሩት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከሞሱል የተሰደዱ ክርስቲያኖች በስነ ልቦና ጉዳት ምክንያት ለመመለስ እንደማያስቡ ተናግረዋል።

በርካታ ክርስቲያኖች አይ ኤስ ሞሱልን ተቆጣጥሮ ይገዛ በነበረበት ጊዜ በአንድ ወቅት የተለያየ እምነት ተከታዮች በጋራ በሰላም አብሮ የሚኖሩባት ቦታ ተብላ በምትጠራው ከተማ ላይ ከባድ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ አሰቃቂ ጊዜ እንደነበር ይቆጥሩታል።

ብጹእ አቡነ መኮ ስለተፈናቃዮቹ ሲናገሩ “ሁኔታው ይለወጥ እንደሆን አናውቅም፥ ዛሬ ብዙዎቹ ተሰደው ያሉት ክርስቲያኖች በሚኖሩበት የኤርቢል አውራጃ በሆነው በአንካዋ ከተማ ነው” ካሉ በኋላ፥ “እዚያ የበለጠ ደህንነት ይሰማቸዋል፣ ሥራ ለማግኝት የተሻሉ እድሎች አሉ፥ በዘመናቸው ከሚያውቋት ብዙ ወደተለወጠችው ከተማ ለመመለስ አይፈልጉም። ይህ ይመጣል ብለውም አያስቡም ነበር” በማለት አጠቃለዋል።
 

12 June 2024, 12:47