ፈልግ

የአምላክ መንገድና የሰው መንገድ የአምላክ መንገድና የሰው መንገድ 

የአምላክ መንገድና የሰው መንገድ

ግንቦት 12 ቀን

«የእኔና የእናንተ መንገድ አንድ አይደለም” (ኢሳ. 55፣8) ይለናል እግዚአብሔር፡፡ ሐሳቡና ሐሳባችን አረማመዱና አረማመዳችን አንድ አይደለም፤ የተለየ ስለሆነ ግንኙነት የለውም፡፡ ፈቃዱና ፈቃዳችን፣ አስተያየቱና አስተያየታችን አይስማሙም፡፡ እንደዚህ የምንለያየው ባሕርያችንና ባሕርዩ እጅግ የተለየ ስለሆነ ነው፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እግዚብሔር አምላክ የሁሉ ፈጣሪና አባት ጉድለት የሌለው ፍጹም ነው፡፡ ኢየሱስ ዘለዓለማዊ መንፈሳዊ ፍትሕ ዕውቀት የሞላበት ነው፡፡ በእኛ በፍጥረቶቹና በእርሱ በፈጣሪያችን መካከል እንደዚህ ያለ ልዩነትና መራራቅ የሚፈጠረው እርሱ በእውነት የሚጠቅሙ እስከ ዘለዓለም የሚኖሩ ነገሮችን ሁሉን አርቆ በጥልቀት ስለማያይ፣ በቅድስና አመለካከት ስለሚፈርድ ነው፡፡

«እግዚአብሔር በሁሉ ሂደቱ ጻድቅ ነው” (መዝ. 144) ይላል ዳዊት፡፡ በአደራረጉና በሥራው ይደነቃል፣ ፍጥረትንም ያደንቃል፡፡ ባጭሩ ለእኛ ጠቃሚና ቁም ነገር የሚመስለን አስተያየት በእርሱ ፊት ከንቱ ነው፡፡ ለእኛ አስፈላጊ መልካምና ጽድቅ የሚመስለን በእርሱ ፊት መጥፎና እርባናቢስ ሆኖ ይገኛል፡፡ እርሱ የሚጠላውን እኛ እንወዳለን፣ እርሱ የሚወደውን እኛ እንጠላለን፡፡ አረማመዱና አረማመዳችን፣ ሐሳቡና ሐሳባችን እጅግ የተለያየና የተራራቀ ስለሆነ ሁልጊዜ አይስማማም፡፡ እንደ ብርሃንና ጨለማ ስለሆነ ሊስማማ ፍጹም አይችልም፡፡ 

እኛ ሰዎች ምድራውያን ነን፤ በመሆኑም ለሥጋችን እናስባለን፡፡ ምድራዊ ሀብትና ገንዘብ በመፈለግ በሥጋዊ መንገድ እንመራለን፡፡ ጊዜያዊውን ጠቀሜታ ስናውጠነጥን በአደራረጋችን ውስጥ ስንት ሐሰትና ውሸት ማታለልና ክፋት ይገኛል; በዚህ ዓይነት እየተንደረደርን ስለምንሄድ የአምላክ ቅን አረማመድ ከእኛ ተንኰለኛ አረማመድ ጋር መስማማት ስለማይችል የእርሱን ቅን አካሄድ አሜን ብለን መቀበል ያቅተናል፡፡

እግዚአብሔር እኛ እንደምንፈልገው አይሄድም፤ በመሆኑ የምንለምነውን ቶሎ ካላደረገልን «ምን ሆኖ ነው;  የማይሰማኝ ምን ስላደረግሁት ነው; መልካም አይደለሁም; የለመንኩትስ ጥሩ አይደለምን;´ እያልን እናጉረመርማለን፤ በጣም እናዝናለን ከአንድ አደጋ ወይ ድንገተኛ ፈተና ሳይታደገን ሲቀር ለምን ይህ ይሆናል; ልመናዬ ለምንድነው ተቀባይነት ሳይኖረው ፍሬ ቢስ ሆኖ የቀረው; እያልን በጣም ስለምናዝን ሃይማኖታችን ይወድቃል ይደረመሳል፣ በማይገባ እንደፈረደብን በመቁጠር እምነታችንን እስከ መካድ እንደርሳለን፡፡

ስለማይገባን «አሁንስ እንደዚህ ተማጽኜው ካልሰማኝ ታዲያ መቼ ነው የሚሰማኝ;´ የሚል ተስፋ የመቁረጥ ሐሳብ ያሸንፈናል፡፡ አምላክ እንደሐሳባችን እንዲሄድ ስንፈልግ የሚገርም አይደለም፡፡ አስተሳሰባችን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ሕፃን አስተሳሰብ ሞኝ ነው፡፡ እኛ ብዙ ጊዜ የምንለውንና የምንጠይቀውን አናውቅም፡፡ የምንለምነውንና የምንፈልገውም በእውነት የሚጠቅም መሆኑን አናገናዝብም፡፡ «የምትለምኑትን አታውቁም” ይለናለ ጌታችን ኢየሱስ፡፡ አምላክን መንገድ እንወቅ አረማመዱንና ሐሳቡን እናክብር እንከተለው፡፡ እገዚአብሔር ጻድቅን አዋቂ በሆኑ ለእኛ የሚያስፈልገንን የሚጠቅመንን የሚያውቅ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ፈቅዱንና ውሳኔውን በትሕትና እንቀበለው፣ መንገዳችንንና ሐሳባችንን ትተን የእርሱን እንውደድ፣ እንደ ቅዱስ ውሳኔው ብንጓዝ አናዝንም፡፡

20 May 2024, 14:45