ፈልግ

የግንቦት 11/2016 ዓ.ም የሦስተኛ የፋሲካ ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌላ አስተንትኖ የግንቦት 11/2016 ዓ.ም የሦስተኛ የፋሲካ ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌላ አስተንትኖ 

የግንቦት 11/2016 ዓ.ም የሦስተኛ የፋሲካ ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌላ አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.      የሐዋ. ሥራ 3፡13-15፣ 17-19

2.     መዝሙር 4

3.     1ኛ ዮሐንስ 2፡1-5

4.    ሉቃስ 24፡35-48

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም በመንገድ ላይ የሆነውንና ኢየሱስ እንጀራውን በቈረሰ ጊዜ እንዴት እንዳወቁት ተረኩላቸው።

ይህን እየተነጋገሩ ሳሉ፣ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፣ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።

እነርሱ ግን ደንግጠው በፍርሀት ተዋጡ፤ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለምን ትጨነቃላችሁ? ለምንስ ጥርጣሬ በልባችሁ ይገባል? እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ እኔው ራሴ ነኝ። ደግሞም ንኩኝና እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና ዐጥንት የለውምና።”

ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው። እነርሱም ከመደሰትና ከመገረም የተነሣ ገና ሳያምኑ፣ “በዚያ ቦታ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቍራሽ ሰጡት፤ እርሱም ተቀብሎ በፊታቸው በላ።

እርሱም፣ “ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው።

በዚህ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሯቸውን ከፈተላቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “ ‘እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

መልካም እሑድ እንዲሆንላችሁ እመኝላችሁኋለሁ! የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ወደ ፋሲካ ምሽት ይወስደናል። ሐዋርያቱ በላይኛው ክፍል ውስጥ ተሰብስበው ሳለ ከኤማሁስ የተመለሱት ሁለት ደቀ መዛሙርት ወደ እነርሱ መጥተው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘታቸውን ነገሩ። እነዚህ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ያዩትን ታሪክ እና የተሰማቸውን ደስታ ለሐዋርያቱ እየገለጹላቸው ሳለ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ መጣ። ይህም በውስጣችን ያለንን በተለይም እምነትን ለሌሎች ማካፈል አስፈላጊ መሆኑን እንዳስብ አድርጎኛል። ይህ ታሪክ ከሞት በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ለሌሎች የማካፈል ወይም ለሌሎች የመመስከር አስፈላጊነት ላይ እንድናሰላስል ያደርገናል።

በየዕለቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ መልእክቶች ይደርሱናል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ የማይጠቅሙን ናቸው። ሌሎች ደግሞ ግልጽ ያልሆኑና የማወቅ ጉጉትን የሚቀሰቅሱ ወይም ይባስ ብለው ከሐሜት እና ከክፋት የሚመነጩ ዓላማ ቢስ እና ጎጂ ወሬዎች ናቸው። ነገር ግን ደግሞ ጥሩ የሆኑ አወንታዊ እና ገንቢ ወሬዎችም አሉ። ጥሩ ነገሮችን መስማት ምን ያህል አሰደሳች እንደሆነ እና ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ሌሎችን መርዳት እንድንችል በበጎም ሆነ በመጥፎ ገጠመኞች ሕይወታችንን የነኩ እውነታዎችን ለሰዎች ማካፈል ጥሩ ነው።

ብዙውን ጊዜ ለመናገር የማንደፍረው ነገር ግን ተገቢ እና አስደሳች ነገር አለ። ይህ ነገር ምንድነው? ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት ነው። እያንዳንዳችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንገናኛለን። ነገር ግን ከእርሱ ጋር ከተገናኘን በኋላ የሚሰማንን ደስታ ለሌሎች አንናገርም ወይም ለመናገር አንደፍራም። ይህን ጉዳይ በተመለከተ እያንዳንዳችን ብዙ ማለት እንችላለን። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት ምን ያህል መልካም እንደሆነ እና እንዴት እንደነካን ለሌሎች ለመናገር አስተማሪ ወይም ልዩ የንግግር ስጦታ ያለን ሰዎች መሆን አይጠበቅብንም። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርብ የተመለከትንበትን ልዩ አጋጣሚን፣

በልባችን ውስጥ የቀሰቀሰበትን ደስታ፣ እንባዎቻችንን ያበሰበትን፣ መተማመንን፣ መጽናናትን፣ ጥንካሬን፣ ቁርጠኝነትን፣ ይቅርታን እና ርኅራኄን ያገኘንባቸውን አጋጣሚዎች ለሌሎች ሰዎች ለማካፈል ወደ ኋላ እንላለን። እያንዳንዳችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኘንባቸውን አጋጣሚዎች ለሌሎች ማካፈል ወይም ማስተላለፍ አለብን። ይህን መልካም ገጠመኝ ከቤተሰብ፣ ከማኅበረሰብ እና ከጓደኛ ጋር መካፈል አስፈላጊ ነው። በሕይወታችን መካከል ወደፊት እንድንጓዝ ስለረዱን መልካም ሃሳቦች እና ስሜቶች እንዲሁም በእምነት እንድናድግ ያደረጉንን ምናልባትም ንስሐ ለመግባት እና ከመጥፎ አካሄድ ለመመለስ ስላደረግነው ጥረት ለሌሎች ማውራት ጥሩ ነው። ይህን ካደረግን ኢየሱስ ክርስቶስ በፋሲካ ምሽት ለኤማሁስ ደቀ መዛሙርት እንዳደረገው ሁሉ እኛንም ያስገርመናል። ግንኙነታችንን እና አካባቢያችንን የበለጠ ያማረ ያደርገዋል።

እንግዲያውስ የእምነት ሕይወታችን አስደናቂ ጊዜን እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኘንበትን ወሳኝ ጊዜን ለማስታወስ እንሞክር። ሁሉም ሰው፣ እያንዳንዳችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ተገናኝተናል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መቼ እንደተገናኘን እስቲ ትንሽ ቆም ብለን እናስብ። እርሱ ወደ እኔ የቀረበው መቼ እንደ ነበር በጸጥታ እናስብ። ይህን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘቴን ለእርሱ ክብር የሰጠሁበትን አጋጣሚ ለሌሎች ተናግሬ አውቃለሁ? ሌሎችም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንደተገናኙ ሲነግሩኝ በጽሞና አዳምጫቸዋለሁ?

ማኅበረሰባችንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይበልጥ የምንገናኝበት ቦታ ለማድረግ እና እምነትን ለሌሎች እንድንካፈል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”

 

18 May 2024, 22:12