ፈልግ

ጎብኚዎች በኢስታንቡል ውስጥ በሚገኘው ሴንት ሴቪየር ቤተክርስቲያን ውስጥ በግድግዳ ላይ የተሳሉ ጥንታዊ መንፈሳዊ ምስሎችን እየጎበኙ ጎብኚዎች በኢስታንቡል ውስጥ በሚገኘው ሴንት ሴቪየር ቤተክርስቲያን ውስጥ በግድግዳ ላይ የተሳሉ ጥንታዊ መንፈሳዊ ምስሎችን እየጎበኙ 

የኢስታንቡል ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወደ መስጊድ በመቀየሩ የአውሮፓ ህብረት ጳጳሳት ማዘናቸውን ገለጹ

የአውሮፓ ህብረት ጳጳሳት ቱርኪዬ በኢስታንቡል የሚገኘውን ጥንታዊውን የባይዛንታይን ‘ሴንት ሴቪየር’ ቾራ ቤተክርስቲያን ወደ መስጊድ ለመቀየር መወሰኗ “በሀገሪቱ ውስጥ የክርስቲያን ታሪካዊ መገኘት መሰረትን ያደበዝዘዋል” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን (COMECE) በቅርቡ የቱርክ ባለስልጣናት በኢስታንቡል የሚገኘውን ሴንት ሴቪየር የሚባለውን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ወደ መስጊድ ለመቀየር ያሳለፉት ውሳኔ በመተግበሩ ማዘኑን ገልጿል።

የአውሮፓ ህብረት ጳጳሳት እርምጃው በቱርክዬ የነበረውን የክርስትናን ታሪካዊ መሰረት ያበላሻል በማለት፥ ውሳኔው ያልተጠበቀና "አሳዛኝም" ጭምር ነው ብሏል። "ቤተክርስቲያንን ወደ መስጂድነት በመቀየር የቱርክ አዎንታዊ መለያ የነበረውን ተቀባይነትና መቻቻል በመቀልበስ ወደ መከፋፋልና ማግለል ይለውጠዋል” በማለትም መግለጫው አስነብቧል።

“በቱርክ ባለስልጣናት ተነሳሽነት የሚጠራው ማንኛውም በሀይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ ውይይትን ታማኝነትን ያሳጣል” በማለት መግለጫው ከአሁን በኋላ የቱርክዬ ባለስልጣናት የሚያስተባብሩት ውይይት ተቀባይነቱ እንደሚቀንስ ገልጸዋል።

የቾራ ሴንት ሴቪየር ቤተክርስቲያን በኢስታንቡል ካሉት “ታሪካዊ” የምስራቅ ኦርቶዶክስ (የባይዛንታይን) ቤተክርስቲያን አንዱ ሲሆን፥ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በቱርክዬ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ለእስልምና አምልኮ እንዲያገለግል ተብሎ በይፋ ተከፍቷል።

ይህ ተግባር የተፈጸመው ከአራት ዓመታት በፊት የሃጊያ ሶፊያ ባዝሊካ ወደ መስጊድ መቀየሩን ተከትሎ የተደረገ ሁለተኛው ውሳኔ ነው።

ይህ ግድግዳዎቹ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት በተሰሩ የባዛንታይን ክርስቲያናዊ ሞዛይኮች እና ምስሎች የተሸፈነው ጥንታዊ ቤተክርስቲያን፣ በ4ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የተመሰረተ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን፥ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ቱርክ በኦቶማን መያዟን ተከትሎ ወደ መስጊድ ተለውጦ የነበረ ቢሆንም፥ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያየ ነው የሚሉት የዘመናዊዋ ቱርክ መስራች ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ እ.አ.አ. በ1945 ዓ.ም. ቦታው ወደ ሙዚየም እንዲቀየር ተወሰነ። የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ አባ ማኑኤል ባሪዮስ ፕሪቶ ውሳኔው የተለያዩ ሀይማኖቶች ተቻችለው አብሮ እንዳይኖሩ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ሃምሌ 2014 ዓ.ም. የሃጊያ ሶፊያ ቤተክርስቲያን ወደ መስጊድነት እንዲለወጥ በተወሰነ ጊዜም የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን ውሳኔውን በመቃወም እርምጃው “በሃይማኖቶች መካከል በሚደረገው ውይይት ላይ ጉዳት ያደርሳል” በማለት መግለጫ አውጥቶ ነበር።

የኮሚሽኑ መግለጫ ከዚህም በተጨማሪ በቱርክዬ ውስጥ ባሉ የጥላቻ ንግግሮች እንዲሁም በብሔር ብሔረሰቦች እና አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የሃይማኖት ተከታዮች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አውግዟል።
 

24 May 2024, 14:57