ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ራፋኤል ታቲል ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በተገናኙበት ወቅት ሊቀ ጳጳስ ራፋኤል ታቲል ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በተገናኙበት ወቅት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ሊቀ ጳጳስ ታቲል ከሮም ጋር ኅብረት መፍጠር የሲሮ-ማላባር ማንነት ማዕከል ነው አሉ

በሲሮ-ማላባር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አዲስ የተመረጡት ሊቀ ጳጳስ ራፋኤል ታቲል ስለ ጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን በማስመልከት ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሲሮ-ማላባር ቤተክርስቲያን፣ በተጨማሪም ሲሮ-ማላባር የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመባል የሚታወቀው፣ በህንድ ሃገር ኬራላ ግዛት ውስጥ የምትገኝ የምስራቅ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ናት። በምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ቀኖናዎች ህግ ስር እራስን በራስ የምታስተዳድር፣ ከቅድስት መንበር እና ከዓለምአቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ጋር ሙሉ ግንኙነት ያላት በራሷ ደንብ የምትተዳደር ልዩ ቤተክርስቲያን ናት።

ብጹእ አቡነ ራፋኤል ታቲል የሕንድ ሲሮ-ማላባር ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ ሆነው የተመረጡት በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ነው።

በልማዱ መሰረት ተመርጠው ብዙም ሳይቆዩ ነበር ወደ ሮም ተጉዘው ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር የተገናኙት።

ሮም በነበሩበት ወቅትም የቫቲካን ዜና ዋና መሥሪያ ቤትን ጎብኝተው ቃለ ምልልስም አድርገዋል። ሊቀ ጳጳሱ በቃለ ምልልሱ ወቅት ስለ ሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በተለያዩ ሃገራት ስላደረጉት ሚስዮናዊ ሥራ፣ ስለነበረው የቤተክርስቲያናቸው ሥርዓተ አምልኮ ውዝግብ እና በቅርቡ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ስላደረጉት ግንኙነት ተናግረዋል።

ቃለ ምልልሱም እንደሚከተለው ይቀርባል፦

ጥያቄ፦ ሊቀ ጳጳስ ራፋኤል በቅድሚያ ወደዚህ ስለመጡ በጣም አመሰግናለሁ። ምናልባት ስለ ሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ትንሽ በመናገር ሊጀምሩልን ይችላሉ።

መልስ፦ የሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ከሮም ጋር ህብረት ካላቸው ከምሥራቃውያን የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በጣም ንቁ እና ከሚስዮናውያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዷ ስትሆን በሐዋርያው ቶማስ የተመሰረተች ቤተክርስቲያን ናት። እንደ አስተምህሮአች መሰረት ሃዋሪያው ቶማስ ወደ ሕንድ ሁለት ጊዜ መጥቷል። መጀመሪያ ወደ ሰሜን ህንድ፣ በጉጃራት ግዛት ውስጥ ብሃሩክ ወደሚባል ቦታ ሄደ። (በዚያ ያሉ ክርስቲያኖች) 'የቶማስ ክርስቲያኖች' ይባላሉ፥ ምክንያቱም በኩራት 'ሐዋርያችን ቶማስ ነው' ስለሚሉ ነው።

ሁለተኛው ጉብኝት በኬረላ ግዛት ውስጥ ወደምትገኘው ኮዱንጋልለር ከተማ ነበር። ኮዱንጋልለር የአይሁድ የንግድ ከተማ ነበረች። ስለዚህ፣ ቶማስም ሁሉም ደቀ መዛሙርት እንደሚያደርጉት አይሁድን ለመፈለግ ወደ ኮዱንጋልለር እና ኬራላ እንደመጣ አስባለሁ። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ቶማስ በዕብራይስጥኛ ቋንቋ ሲናገር ማን እንደተረጎመለት ይጠይቁኛል። ለኔ መልሱ በዚያን ወቅት የነበሩ ስደተኞች ናቸው የሚል ነው፥ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ተርጓሚዎች ነበሩ። ቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ የስደተኞች ቤተ ክርስቲያን ናት። ምናልባት በደም ግንኙነቶች ምክንያት በጣም በተደጋጋሚ እንጓዛለን። የሲሮ-ማላባር ቤተክርስቲያን ከኬረላ ወደ ህንድ እንዲሁም ከህንድ ውጭ ባሉ ሃገራት ተስፋፍቷል። 35 ሀገረ ስብከት ብቻ እንዳለን ስታውቅ ትገረማለህ። በኬረላ ያሉት 13 ብቻ ናቸው። 18 ሃገረ ስብከቶች በህንድ ውስጥ ነገር ግን ከኬረላ ውጭ ያሉ ናቸው። አራት ሀገረ ስብከቶች ከህንድ ውጪ በአራት አህጉራት ማለትም አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና በሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ የምትገኘው ፕሪስተን ከተማ ይገኛሉ። ስለዚህ ሚስዮናውያን ማህበረሰብ እንደሆንን ልነግርህ እፈልጋለሁ።

ጥያቄ፡- የዚህ የረጅም ዓመት ታሪክ ባለቤት የሆነችው ቤተክርስቲያን መሪ ሆነዋል። አንዳንድ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

መልስ፦ በመጀመሪያ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ ምክንያቱም ይህች ቤተክርስቲያን በጣም ጠንካራ የምስራቃዊ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ነች። ከቅዱስ ቶማስ ክርስቲያኖች መካከል አብዛኛዎቹ ካቶሊኮች ናቸው። እናም አባቶቻችን እንዳሉት ምንም እንኳ ከሚስዮናውያን የሚደርስባቸው የሃይማኖት ስደት ቢበረታም እና በብዙ ገደቦች ውስጥ ቢሆኑም ከቅዱስ አባታችን ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጥ አልፈለግንም ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያናችን በ(ምዕራባውያን) ሚስዮናውያን በርካታ ገደቦች ያደርጉብናል ብለው ያስቡ በነበረበት ወቅት ፈተና ላይ ወድቃ ነበር፥ በዚህም ምክንያት አንደኛው ቡድን የሮማ ካቶሊክ ኅብረትን ለመልቀቅ ወሰነ፣ በፈቃደኝነት ሳይሆን በሁኔታዎች ምክንያት። በዚያን ጊዜም ቢሆን አባቶቻችን በእነዚህ ሁሉ ስደቶች፣ በእነዚህ ሁሉ እገዳዎች መሃል ሆነውም ከቅዱስ አባታችን ጋር በመተባበር ካቶሊክ ለመሆን እንፈልጋለን አሉ።

ስለዚህ የሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ከቅድስት መንበር እና ከቅዱስ አባታችን ጋር ያላትን ቁርኝት እንደማታቋርጥ በኩራት ልነግራችሁ እወዳለሁ። ምኞቴ ቤተክርስቲያናችን በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሥር ሆና እንደ ኃያል የምስራቃዊ ቤተክርስቲያን፣ በካቶሊክ ህብረት ውስጥ የምታገለግል በጣም ንቁ የምስራቃዊ ቤተክርስቲያን ተልእኳችንን እንድንቀጥል ነው።

ጥያቄ፡- ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠቅሰዋል፥ እንዲያውም በቅርቡ ተገናኝታችኋል፥ ስብሰባችሁ እንዴት ነበር?

መልስ፡- ከቅዱስ አባታችን ጋር በነበረን ቆይታ በጣም አባታዊ ነበሩ። በቅዱስ አባታችን ፊት እንደሆንኩ ተሰምቶኝ አያውቅም፥ ምንም እንኳን እሳቸው ቅዱስ አባት ቢሆኑም እኔን እንደ ልጃቸው አድርገው ነበር ያቀረቡኝ። የምናገረውን ነገር ሁሉ በትኩረት ሲሰሙኝ ነበር።

ስለነበሩት ችግሮች ስናገር፣ “አትጨነቅ፣ ብዙ ግንዛቤ እና የዕውቀት አድማስ ሲኖርህ ችግሮች ምንም አይደሉም፣ ችግሮች የበለጠ ንቁ ያደርጉሃል፥ ችግሮች የበለጠ ትክክለኛ እና ታማኝ እንድትሆን ያደርጉሃል” ይሉኝ ነበር፥ ይህ ለእኔ ትልቅ ማበረታቻ ይመስለኛል። ችግሮች የዓለም መጨረሻ አይደሉም። እነሱ የበለጠ ታማኝ እና የበለጠ ዋጋ ያለው እንድትሆን ያደርጉሃል፥ ስለዚህ ለችግሮች አትጨነቅ። ምናልባት በአጋጣሚ ሊሆን ይችላል፥ ጧት 1፡45 ላይ ነው ቅዱስ አባታችንን ያገኘሁት። በዕለቱ መጀመሪያ ተቀብለው ያነጋገሩኝ እኔን ነው፥ ከእኔ ጋር የተገናኙበት ግንቦት 5 የፋጢማ እመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል ነው። በአጋጣሚ ነው ግን ለቤተክርስቲያናችን በጣም ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፣ ምክንያቱም ለቤተክርስቲያን እና ለኢየሱስ ያለን ታማኝነት፣ ለማርያምም ያለን ፍቅር ነው።

አባቶቻችን ሁል ጊዜ የመቁጠሪያ ጸሎት ያደርጉ ነበር፥ ዛሬ እንኳን የሲሮ-ማላባር ቤተሰቦች በቅድስት ድንግል ማርያም ምሥል ፊት ተንበርክከው የመቁጠሪያ ጸሎት ሲያደርጉ ሊያስገርምህ ይችላል። በእኔ ቤተሰብ ልምድ፣ የቤተሰብ ጸሎት እና መቁጠርያ ያላደረግንበት ብቸኛው ቀን የስቅለት ቀን ብቻ ነው። የመቁጠሪያ ጸሎት ለልባችን በጣም ቅርብ ነው። እናም ቤተክርስቲያናችን እና ትውፊታችን አሁንም ድረስ በመንፈሳዊነታችን ውስጥ በማሪያም ረድኤት አበክረን እናምናለን። ሁሉም የማርያም በዓላት በጾም ይከበራል። ለምሳሌ ጾመ ልደቱ የስምንት ቀን ጾም፣ ጾመ ድጓ ዐሥራ አምስት ቀን፣ ለገና ሃያ አምስት ቀናት፣ ለዓብይ ጾም ሃምሳ ቀናትን እንፆማለን።

ጥያቄ፦ የመቁጠሪያ ጸሎት የላቲን አምልኮ ሲሆን ጾም ግን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የተለመደ ነው። ታዲያ ሁለቱ ነገሮች የተደበላለቁ አይመስልም?

መልስ፦ ከምእራብ ቤተክርስቲያን የጾም እና የንስሓን ትውፊት አልተቀበልንም። ይህ የህንድ ባህል ነው። ከበዓሉ ጋር ያለው ግንኙነት ምዕራባዊ ሊሆን ይችላል፥ ነገር ግን የጾም ባህል የመጣው ከህንድ ባህል ነው። ለእያንዳንዱ ክብረ በዓል ሂንዱዎች እና ህንዶች ይፆማሉ። ከሁሉም በዓላት በፊት ይፆማል፥ የጾሙ ፍጻሜም የበዓሉ አከባበር ነው።

ጥያቄ፦ ቀደም ሲል የሲሮ-ማላባር ቤተክርስቲያን ከምስራቃዊ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በጣም ንቁ ቤተክርስቲያን ነው ብለው ነበር፥ በህንድ ውስጥ እና ከህንድ ውጭም ብዙ የሚስዮናዊ ስራ እንደሚሰሩ አውቃለሁ። ምናልባት ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ሊነግሩኝ ይችላሉ?

መልስ፦ የአውሮፓ ሚስዮናውያን ከመጡ በኋላ፣ አብዛኞቹ [የሲሮ-ማላባር] ሚስዮናውያን ህንድ ውስጥ ላለው ለላቲን ቤተክርስቲያን አገልግለዋል። የሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ለጋስ እና ቸር ስለነበረች፣ አገልግሎታችንን እና ጥሪያችንን ለሁሉም አህጉረ ስብከት እና የሃይማኖት ጉባኤዎች እናቀርባለን። በላቲን ሀገረ ስብከት የሚያገለግሉ ወደ 30 የሚጠጉ የሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ነበሩ።

እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ሳሌሲያኖች የሲሮ-ማላባር ቤተክርስትያን ግዛት አልነበራቸውም፣ ነገር ግን ሁሉም ማለት ይቻላል ሳሌሲያኖች ከሲሮ-ማላባር ቤተክርስትያን የመጡ ናቸው። ሥርዓታዊ ማንነታችን ላይ አጥብቀን አልጠየቅንም። የተልዕኮአችንን ሥራ የምንሠራበት ጥራት የመጣው ከሥርዓተ አምልኮ ማንነታችን እና ከቤተሰቦቻችን ባገኘነው ባህል ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን ሁል ጊዜ ሚሲዮናዊት ቤተክርስትያን ማንነት አላት፥ ተልእኮአችንን በራሳችን የምንፈጽም እንዲሁም የላቲን ቤተክርስቲያንን ተልእኮዎችን እናግዛለን ።

ጥያቄ፡- አሁን በሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴን አስመልክቶ ውዝግብ ተነስቷል። አሁን ያለው የክርክሩ ሁኔታ ምን ይመስላል?

መልስ፡- ውዝግብ አለ ነገር ግን ያ ውዝግብ እንደ እኔ አባባል በመገናኛ ብዙሃን በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች ትንሽ የተጋነነ ነው። ሥርዓተ ቅዳሴው የሚከበረው ከተመሳሳይ ጽሑፍ ነው። በጽሑፉ ላይ ምንም ለውጥ አልተደረገም። እንደ ምሥራቃውያን ባህላችን፣ ቅዱስ ቃሉን የምናሰማው በሕዝብ ፊት ነው፣ ምሥጢረ ሥጋዌን እና ሥርዓተ ቅዱስ ቁርባንን ደግሞ በመሠዊያው ፊት ለማክበር ወስነናል።

እኛ 35 ሃገረ ስብከቶች አሉን፣ ከነዚህ ውስጥ 34 ሃገረ ስብከቶች ይህንን ውሳኔ መከተላቸውን ማንም የጠቀሰ የለም። አንደኛው የኤርናኩላ ሃገረ ስብከት ሲሆን፥ ይህንን ውሳኔ በዚህ ሰፊ እና የኬራላ ዋና ከተማ በሆነው ሃገረስብከት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ትንሽ ችግር አለ። ነገር ግን እኔ የሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ዋና ሊቀ ጳጳስ ሆኜ እንደመመረጤ ለሁሉም ሰው መናገር የምፈልገው ነገር አለ፥ ውዝግቡን ከትክክለኛው ሁኔታ በላይ ማጋነን የለባችሁም።

ይህ ውዝግብ ሊፈታ ይችላል፥ በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈታ ተስፋ አደርጋለሁ። 34 ሃገረ ስብከት ህጉን ተከትለውት አንድ ሀገረ ስብከት ሊከተለው ስላልቻለ ብቻ እንደ ትልቅ ችግር ሊወራ አይገባም። አንዱ ችግር በአሁኑ ወቅት ይህ ሀገረ ስብከት ጳጳሳዊ ተወካይ እና ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቄርሎስ ቫሲል ሥር መሆኑ ነው። ይህ በሰላማዊ ውይይት እና በወዳጅነት አቀራረቦች እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ሊፈታ የሚችል ጊዜያዊ ውዝግብ ነው። ስለዚህ ይህንን ውዝግብ እንደ ቤተክርስቲያናችን መጨረሻ አልቆጥረውም። ይህ የቤተክርስቲያናችን ትንሳኤ ነው። አሁን እናሸንፈዋለን፣ እንደገናም እናቆጠቁጣለን። ምክንያቱም ከምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል፣ በዓለም ዙሪያ የተስፋፋ እጅግ በጣም ጠንካራ የምሥራቃውያን ቤተ ክርስቲያን የሲሮ-ማላባር ቤተ ክርስቲያን ነው። በህንድ ውስጥም ሆነ ከህንድ ውጭ ትርጉም ባለው እና ጉልህ በሆነ መልኩ የሚስዮናውያንን ስራ ለመስራት የምትችለው በምስራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለችው ቤተክርስቲያን የሲሮ-ማላባር ቤተክርስቲያን ናት። ስለዚህ የሲሮ-ማላባር ቤተክርስትያን እነዚህን አስቸጋሪ ጊዜያት ትሻገራለች፣ እኛም የራሳችንን ድርሻ እንወጣለን።

ጥያቄ፦ ቃለ መጠይቁን ከማብቃታችን በፊት የሆነ ነገር ማከል ይፈልጋሉ?

መልስ፦ በጣም አመሰግናለሁ፣ ምክንያቱም ይህ ቃለ መጠይቅ ስለ ቤተክርስቲያናችን እና ስለሀገራችን ለመናገር እድል ይሰጠኛል፣ እናም ያንን እድል ስለፈጠርክ ደግሜ አመሰግናለሁ። የቫቲካን የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት በህንድ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በሁሉም ሰው ዘንድ በጣም ይደነቃል። እኔ ተጓዥ ጳጳስ ነኝ፥ ወደ ብዙ ቦታ ተጉዣለሁ። ይህ ቃለ ምልልስ እንደእኛ ላሉ አናሳ ወገኖች የሚሰጠው ትርጉም በጣም ትልቅ ነገር እንደሆነ እገምታለሁ። ይህ መድረክ ለእኔ የሰጠኸኝ እውነታ ለአናሳ ማህበረሰብ፣ ለአናሳ ቤተ ክርስቲያን ያለህን ፍቅር ያሳያል። በትክክልም እየሰራችሁ ስለምትገኙ በካቶሊክ ህብረት ወይም ትስስር ውስጥ ትልቅ ዋጋ አላችሁ። የቫቲካን ረዲዮ እና የቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ከአንተ ስሌት ባለፈ በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች፣ በተለይም በህንድ ውስጥ በጣም ይደመጣሉ ብሎም ይታደማሉ።
 

23 May 2024, 17:21