ፈልግ

በኤልኒኖ ምክንያት በዚምባብዌ ለተከሰተው ድርቅ ሰብአዊ ዕርዳታ እየተሰጠ ይገኛል በኤልኒኖ ምክንያት በዚምባብዌ ለተከሰተው ድርቅ ሰብአዊ ዕርዳታ እየተሰጠ ይገኛል 

በዚምባብዌ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ የሃገሪቱ ብጹአን ጳጳሳት እርዳታ እንዲደረግ ጠየቁ

የዚምባብዌ የካቶሊክ ጳጳሳት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በዘንድሮው ዓመት የግብርና ወቅት ላይ የደረሰውን ብሄራዊ የድርቅ አደጋ ይፋ ካደረጉ በኋላ የካቶሊክ ኤጀንሲዎች በረሃብ የተጎዱ ሰዎችን እንዲያግዙ ተማጽነዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ መጋቢት 24 በሰጡት መግለጫ በዘንድሮው የግብርና ወቅት በደረሰው ድርቅ ምክንያት ሃገሪቷ ለብሔራዊ አደጋ መጋለጧን መታወጁን ተከትሎ፥ የዚምባብዌ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ሀገሪቱ ላይ የተከሰተው አሰቃቂ ድርቅ በድሆች እና በገጠር አካባቢዎች ያሉ በርካታ ሰዎች ህይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ መቋቋም ከሚቻለው በላይ እንደሆነ በመግለጽ፣ ሃገሪቷ  ለከባድ የረሃብ አደጋ የተጋረጠች መሆኗን ባወጣው ሃዋሪያዊ መግለጫ አሳይቷል።

ይህም ማለት በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋስትና እጦት እንዳለ የሚጠቁም ሲሆን፥ መንግስት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ህዝቡ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት እንዳይራብ እና እንዳይሞት በጋራ መስራት እንዳለባቸው ያመላክታል ተብሏል።

በኤልኒኖ ምክንያት የተከሰተው ድርቅ

ብጹአን ጳጳሳቱ እንዳስታወቁት በኤልኒኖ ምክንያት የተከሰተው ድርቅ ወትሮውኑ በከባድ የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ ድህነት እና የወጣቶች ስራ አጥነት ምክንያት ሲሰቃዩ በነበሩ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት ነው ብለዋል።

“በተደጋጋሚ ሲወራለት የነበረው የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ገጽታውን በድጋሚ አሳይቷል፥ የትኛውም ድርቅ የሚያስከትለው መዘዝ አስከፊ ነው፥ ነገር ግን ቀድሞውንም ስቃይ ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ሲያጠቃ፣ የሚያደርሰው ጥፋት ከሚታሰበው በላይ ነው። አብዛኛው በገጠር የሚኖሩትን እና በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በድርቁ ምክንያት የደረቁ የግጦሽ መሬቶች በከብቶቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። እንደ ሀገር ለኑሮአችን ስጋት እና የምግብ ዋስትና እጦት ተጋርጦብናል” ሲሉ ጳጳሳቱ በሃዋሪያዊ መግለጫው ላይ ገልጸዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ ሁሉም በጎ ፈቃድ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ለመደገፍ ሀብታቸውን እንዲያሰባስቡ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ፥  ሁሉም በአንድነት የተቸገሩትን የመንከባከብ ግዴታ እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተዋል።

“ለመላው ካቶሊኮች፣ በጎ ፈቃድ ላላቸው ወንዶችና ሴቶች፣ የሰብዓዊ ተቋማትና ኤጀንሲዎች ሀብታችንን እንድናሰባስብ እና በድርቁ ምክንያት የሚደርሰውን የብዙዎችን ሞት እንድንታደግ እንማፀናለን፥ ሁላችንም በድርቁ ምክንያት የተቸገሩትን የመንከባከብ ግዴታና ኃላፊነት አለብን። አንድ ላይ ተነስተን ፈተናውን የምንጋፈጥበት ጊዜ አሁን ነው። አንድ ላይ ስንሆን እንጠነክራለን፥ ብዙሃኑንም መመገብ እንችላለን። ያለንን ትንሽ ነገር በጌታ ፍቅር ስንሰጥ እርሱ ያበዛዋል፤ ያኔም ሁሉም ይጠግባል” ሲሉ የካቶሊክ ጳጳሳቱ ተናግረዋል።

የምግብ ጉዳዮችን ፖለቲካ አታድርጉ

መግለጫው ድሆች ብዙውን ጊዜ በችግሮች ምክንያት እንግልት እንደሚደርስባቸው በመግለጽ፥ “ረሃብ የፖለቲካ ልዩነትን አያውቅም፥ የተቸገሩት የዚህች ሀገር ዜጎች ናቸው፥ በተመሣሣይ ሁኔታ አጋጣሚውን ተጠቅመው ትርፍ ለማግኘት ለሚፈልጉ፣ ጊዜው እንዳልሆነ ልናሳስባቸው እንወዳለን” በማለት በየደረጃው የሚታዩ የምግብ ፍላጎትን ፖለቲካ የማድረግ አዝማሚያዎችንም ተችተዋል።

ሆኖም እንደ ካሪታስ ያሉ የካቶሊክ ግብረሰናይ ኤጀንሲዎች ቀውሱን ለመቅረፍ ሀብት ማሰባሰብ ጀምረዋል። ኮሚሽኑ ከዚህን በፊት ሃገሪቷ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ሃገረ ስብከቶች ውስጥ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቢቆይም፣ አሁን ላይ በተለያዩ መዋቅሮቹ አማካይነት የአደጋውን ሁኔታ በመከታተል ምላሽ የመስጠት ተግባሩን አሳድጓል።

‘ካሪታስ ሁዋንጌ’ ቅድመ ትግበራዎችን እያካሄደ ነው

የሁዋንጌ ሀገረ ስብከት የካሪታስ አስተባባሪ አቶ ሱፐር ዱቤ ለህብረተሰቡ የሚከፋፈል ምግብ ለማግኘት እና ግብአቶችን በማሰባሰብ ድጋፍ ለማድረግ በገንዘብ መርዳት የሚችሉ የተለያዩ አጋሮችን ማነጋገር መጀመራቸውን ተናግረዋል። ይህንንም በማስመልከት “ምግብ፣ በተለይም የእህል ዱቄት፣ ቦሎቄ እና የአትክልት ዘይት በየወሩ ለበርካታ ቤተሰቦች ይከፋፈላሉ። የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በቅርቡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ይጀምራል። የዘር ስርጭትን በአዲስ መልክ ማከፋፈልም የፕሮግራሙ አካል ይሆናል” ብለዋል አቶ ዱቤ።

ካሪታስ በጣም የተጎዱ ማህበረሰቦችን እና አባወራዎችን ለመለየት የማጣራት ሥራውን እንደሚያካሂድ እና የተቸገሩትን ለመርዳት እና የከፋ ጉዳትን ለመከላከል ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚተባበር አቶ ዱቤ ተናግረዋል።

ካሪታስ ሁዋንጌ ድርቁን ለመቅረፍ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈርና የነበሩትን በማደስ እንዲሁም አነስተኛ የአትክልት ማሳዎችን በማቋቋም ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። አክለውም ቤተሰቦቻቸውን የመመገብ ሃላፊነት ተጥሎባቸው በነበሩ ሴቶች ላይ ትኩረት እንደተሰጠ በመጠቆም፥ በተጨማሪም ግብአት ከተገኘ ማንም ሰው በረሃብ እንዳይሞት በሴት የሚመሩ አባወራዎች፣ ባልቴቶች እና ህጻናት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አቶ ዱቤ ተናግረዋል።

‘ካሪታስ ቺንሆይ’ የእርዳታ ሥራዎቹን ከፍ አድርጓል

ከዚህም በተጨማሪ ቺንሆይ ውስጥ በምትገኘው ምቢሬ ወረዳ ለሚገኙ 506 ሰዎች ካሪታስ ቺንሆይ በቆሎ፣ የማብሰያ ዘይት እና በሎቄ እያከፋፈለ ሲሆን፥ ሳሙና እና የውሃ መቅጃ ባልዲ ተሰጥቷቸው የኮሌራ በሽታ ስጋትን ለመቀነስ እየጣረ ይገኛል።

በተጨማሪም በዚያው ወረዳ በሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ 1000 ተማሪዎች የበቆሎና አኩሪ አተር ቅልቅል (CSB) ገንፎ እንዲመገቡ ማድረግ ተችሏል። 

የበቆሎና አኩሪ አተር ቅልቅሉ በሰፊው ከተለመዱት ዱቄቶች ይበልጥ በተለያዩ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ተዋህዶ የዳበረ የምግብ አይነት ሲሆን፥ የበቆሎ እና አኩሪ አተር ዱቄት ላይ የተለያዩ ቪታሚኖች እና ማዕድናትን በመደባለቅ የሚዘጋጅ ነው።

የቺንሆይ ሀገረ ስብከት የካሪታስ አስተባባሪ የሆኑት አባ ዮሃንስ ዘቭሂቶ እንዳሉት ካሪታስ የድርቁን ተፅእኖ ለመቀነስ እንደ አሳ እርባታ እና የአትክልት ስፍራዎችን በማዘጋጀት ተጎጂዎቹ እንዲተዳደሩበት ከፍተኛ ድጋፍ እያረገ ይገኛል። እደ ትምህርት ቤቶችና ክሊኒኮች በመሳሰሉ በተለያዩ ተቋማት አነስተኛ መስኖ ለማልማት እንዲቻል ድርጅታቸው በሶላር የሚሰራ የውሃ ፓምፖችን በመትከል እያገዘ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ የቻፒንዱካ እና ሙብውንዱሲ ግድቦች ግንባታም ከድርጅቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አክለው ተናግረዋል።

አባ ዘቭሂቶ በመጨረቻም ካሪታስ ቺንሆይ በኤልኒኖ ምክንያት ለተፈጠረው ድርቅ ምላሽ እንዲሰጡ የተለያዩ አጋር ተቋማትን በማሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
 

08 April 2024, 15:45