ፈልግ

UKRAINE-RUSSIA-CONFLICT-WAR-RELIGION-EASTER

በአንዲት ቅድስት ካቶሊካዊትና ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን እናምናለን

የዓለም አቀፍ ካቶሊክ ቤተሰብ አባል በመሆናችን ደስታ ይሰማናል

ለምን ቤተ ክርስቲያናችንን ካቶሊክ እንላለን?

“ካቶሊክ” ማለት አጠቃላይ፤ ዓለም አቀፋዊ፤ ለሁሉም ሰውና ለሁሉም ዓለም የሚሆን ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉንም ዓለም፤ ሁሉንም አገር፤ ሁሉንም ዘር፤ ሁሉንም ባህልና፤ ሁሉንም ትውልድ የምታቅፍ ስለሆነች ካቶሊክ ቤተክርስቲያን እንላታለን፡፡

ለምን ቤተ ክርስቲያናችንን ሮማዊት እንላለን?

ቤተ ክርስቲያናችን ሮማዊት ነች፤ ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያናችን የመጀመርያ እረኛ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮማ ስለኖረ፤ ስለሞተና እዛውም ስለተቀበረ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ የመጀመርያው ርእሰ ሊቃነ ጳጳስ ነው፡፡ አሁንም ታዲያ የሮሙ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ የመላዋ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበላይ እረኛ ነው፡፡ እሱ የክርስቶስ ተከታዮችን በአንድ ላይ የሚጠብቅና የመላዋ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ምሳሌ ነው፡፡ በሮም ያለው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳችን ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተበት የጴጥሮስ አለት ነው፡፡ ከዚህ እረኛዋ ጋር ሆና በምታደርገው ትግል ቤተ ክርስቲያን ምን ጊዜም የዓለም ኃይላት ሊያሸንፉዋት አይችሉም “እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” (ማቴ. 16፡18) በማለት  ክርስቶስ ራሱ የገባላት ቃል ነው፡፡

ለምን ቤተ ክርስቲያናችን አንዲት ናት እንላለን?

ቤተክርስቲያናችንን አንዲት ናት የምንልባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ።

1.    ከሰው ዘር ሁሉ የተወጣጡ በሁሉም ሀገሮች የሚገኙ ካቶሊካዊያን ሁሉ እኩል የሚያከብሩትና የሚጋሩት አንድ ቅዱስ ቁርባን ያላት በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ እጅግ ቅዱስ በሆነው ምሥጢር አማካይነት ክርስቶስ  በዚህ ማዕዱ ዙሪያ እንደ አንድ ቤተሰብ ሰብስቦን በግልጽ የሚያስተሳስረን እርሱ ነው፡፡

2.    እኛ ካቶሊኮች በዓለም ዙሪያ ሁሉ ተመሳሳይ የአምልኮ ስርዐት ያለን ሲሆን  ካቶሊኮች ሁሉ ከሮማው ጳጳስ ጋር በጠበቀ ኅብረት ሲኖሩ ምን ጊዜም በማንኛውም ስህተት ሳይነቃነቁ ከጴጥሮስ አለት ጋር በፍጹም አንድነት ይኖራሉ፡፡

3.    በሮም ያሉት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመላይቱ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ተምሳሌት(ቋጠሮ) ናቸው። እሳቸው  እንዲያው በቀላሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ራስ ወይም የበላይ ሳይሆኑ ክርስቶስን ወክሎ በቅዱስ ቁርባን ምሥጢር ከክርስቶስ ጋር ለሚኖረን ፍጹም አንድነት የሚመሩ ሊቀ ካህን ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ክርስቶስ የተመኘው አንድነት በተከታዮቹ ዘንድ በሙላት ያለመኖሩ በጣም ያሳዝነናል፡፡ ለዚህ አንድነት ማጣት ካቶሊክ ቤተ ክርሰቲያን በቱርክ ውስጥ ያደረገችው አስተዎጽዖ አለ።በመሆኑም ር.ሊ.ጳ ጳውሎስ 6ኛ እና ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በዘመናት ጉዞዋ ለክርስቶስ ተከታዮች መልካም የፍቅርና የእምነት ምሳሌ ያልሆነችባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ አምነው በዚህ ምክንያት በክርስቲያኖች መካከል ስለተፈጠረው መከፋፈል ሁሉ እኛም እኩል ተጠያቂዎች ነን በማለት በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ የሆነ ሆኖ “ሁሉም አንድ እንዲሆኑ” ከጌታ ጋር እኛም በጸሎት እንተጋለን፡፡ (ዮሐ.17፡21)

ቤተክርስቲያናችንን ለምን “ሐዋርያዊት” እንላታለን?

ቤተ ክርስቲያናችንን በትክክል “ሐዋርያዊት” የምንልበት ሁለት ምክንያቶች አሉ፡-

አንደኛው ባልተቆራረጠ ሰንሰለት ከሐዋርያት ጀምሮ በጳጳሳትና አቡናት መተካካት እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀች በመሆኗ ሲሆን ሁለተኛው ቤተክርስቲያናችን በር.ሊ.ጳጳሳት እና በአቡናት አመራር ሥር ሆና የሐዋርያትን ትምህርትና እምነት የምትኖር፤ የምታስተምርና የምትጠብቅ በመሆኗ ነው፡፡

ቤተክርስቲያናችንን “ቅድስት” የምንለውስ ለምንድነው?

ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስብስብ ማለት ነው፤የጌታ የሆኑ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን “ቅድስት” የሚያደርጋት ጌታ ራሱ ነው፡፡ እሱ ሙሽራው ሙሽሪትን እንደሚወድ ቤተ ክርስቲያንን ይወዳታልና፡፡ እኛ ካቶሊኮች ሐጥያተኞች መሆናችንን እንናዘዛለን፤ ነገር ግን የክርስቶስ ፍቅር እንደሚቀድሰንና የቅድስት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አካል እንደሚያደርገን እንናገራለን/እናውጃለን፡፡

ክርስቶስ ስለቤተ ክርስቲያኑ ሞቷል፤እኛን ሐጥያተኞቹን ይቅር ብሎን እንደገና ይቀድሰናል፡፡ ለዘለዓለም ከኛ ጋር ሆኖ ሊቀድሰንና ሊያጠነክረን ስለፈለገ ቅዱስ ቃሉንና ሰባቱን ምሥጢራት ሰጥቶናል፡፡ ራሱ ክርስቶስ በመካከላችን ሆኖ ከኛ ምስኪን ባህሪያችንና አሳፋሪ ውድቀታችን ባሻገር ሮማዊት ካቶሊካዊት ሐዋርያዊትና ቅድስት ቤተ ክርሰቲያናችንን ሁሌም ይቀድሳታል፡፡ ይህ ሁሌም በደስታና በኩራት የምንናገረውና የምናበስረው ካቶሊካዊ እምነታችን ነው፡፡

ምንጭ፡ የካቶሊክ እምነትና ምንነት፥ ካቶሊካዊ ደስታ፥ በሚል አርእስት ክቡር አባ አበራ ማኬቦ የካፑቺን ማሕበር አባል ከጻፉት መጽሐፍ የተወሰደ።

 

 

 

 

04 April 2024, 15:41