ፈልግ

የመጋቢት 29/2016 ዓ.ም የሦስተኛው የዓብይ ጾም ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የመጋቢት 29/2016 ዓ.ም የሦስተኛው የዓብይ ጾም ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የመጋቢት 29/2016 ዓ.ም የሦስተኛው የዓብይ ጾም ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ከእግዚአብሔር ጋር የማይለዋወጥ ጽኑ ግንኝነት መመሥረት ይገባል!”

የእለቱ ንባባት

1.    ዘጸሃት 20፡1-17

2.    መዝሙር 18

3.    1ቆሮንጦስ 1፡22-25

4.    ዩሐንስ 2፡13-25

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በመቅደስም በሬዎችንም በጎችን ግንቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም፦ ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፦ የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ። ስለዚህ አይሁድ መልሰው፦ ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ፦ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። 21እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር። ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ።

በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳሉ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ፤ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው የሦስተኛው የዓብይ ጾም ሳምንት ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ. 2: 13-25) ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በቤተመቅደስ ውስጥ ሆነው ይገበያዩ የነበሩ ነጋዴዎችን ከቤተመቅደስ እንዲወጡ ያደረገበትን ትዕይንት ያሳየናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሻጮችን ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በማስወጣት፣ ገንዘባቸውንም በመበተን እና ገበታዎቻቸውንም በመገለባበጥ እንዲህ ሲል ገሰጻቸው፥ ‘የአባቴን ቤት የንግድ ቤተ አታድርጉት’ አላቸው (ዮሐ. 2:16) ። በቤት እና በገበያ መካከል ባለው ልዩነት ላይ እናተኩር። በእርግጥ እነዚህ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብባቸው ሁለት የተለያዩ መንገዶች ናቸው።

ቤተ መቅደስን እንደ ገበያ ሥፍራነት ስንመለከተው አንድ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ትክክል ለመሆን በቤተ መቅደስ ውስጥ የበግ ጠቦትን ገዝቶ በመሠዊያው እሳት ከጠበሰው በኋላ መብላት ነበረበት። ከዚያም በኋላ ሁሉም ሰው ወደ ቤቱ ይሄዳል። በዚህ ሁኔታ ቤተመቅደስ እንደ ቤት ይቆጠራል። በሌላ በኩል በተቃራኒው ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ ወደ እሱ፣ ወደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለመቅረብ፣ ደስታን እና ሐዘንን ለመካፈል ወደ ቤተመቅደስ እንሄዳለን። ከዚህም በላይ ሁሉም ሰው ወደ ገበያ ሲሄድ ስለሚገዛው ነገር ዋጋ ይደራደራል። በቤት ውስጥ ግን ለሚደረግለት መስተንግዶ ምን ያህል ልክፈል ብሎ ማንም አያስብም። ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ገበያ ሲሄድ የራሱን ፍላጎት ወይም ትርፍ ይፈልጋል። በቤት ውስጥ ግን ሁሉንም ነገር በነጻ ያገኛል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሻጮችን ከቤተ መቅደሱ እንዲወጥ ያደረገበት፣ ገበታዎቻቸውን ገለባብጦ ገንዘባቸውን የበተነባቸው፥ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚቀርቡበት ቤተ መቅደስ ወደ ገበያ ማዕከልነት እንዲለወጥ ባለመፈለጉ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲበላሽ ወይም እንዲቋረጥ አይፈልግልም። የጠበቀ እና እምነት የተጣለበት እንጂ የራቀ እና ከንግድ ጋር የተያያዘ እንዲሆን ኢየሱስ አይፈልግም። የቤተሰብ ገበታን የዕቃ መሸጫ ቦታ እንዲሁን፣ የዋጋ ድርድሮች የወዳጅነት ስሜትን፣ ሳንቲሞችም የሰዎችን መቀራረብ እንዲተኩ ኢየሱስ አፈልግም። ኢየሱስ ይህን የማይፈልገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር እና በሰዎች መካከል ኅብረትን፣ ምሕረትን እና መቀራረብን ለማምጣት የመጣ በመሆኑ በወንድሞች መካከል ልዩነትን እንዲፈጠር አይፈልግም።

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የዐብይ ፆም ወቅትን ጨምሮ በራሳችን እና በአካባቢያችን ውስጥ ከገበያ ሥፍራነት ይልቅ የላቀ የቤተሰብነት ስሜት መገንባት እንደሚገባን ከሁሉ አስቀድሞ እንደ ስግብግቦች እና እምነት እንደሌላቸው ነጋዴዎች ሳንሆን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ አብዝተን እንድንጸልይ፣ ወደ ደጁ በልበ ሙሉነት ቀርበን ሳንሰለች በሩን እንድናንኳኳ ይጋብዘናል። ስለዚህ በቅድሚያ በጸሎት ከዚያም ወንድማማችነት ከምን ጊዜውም የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ወንድማማችነትን ማስፋፋት ይኖርብናል።

ስለዚህ በቅድሚያ ጸሎታችን ምን ይመስላል? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። ጸሎታችን እንደ አንድ ዕቃ ዋጋ የተተመነነው ወይስ ጊዜን ሳንሰጥ በብቸንነት ወቅት የእግዚአብሔርን ዕገዛ የምንለምንበት ነው? ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ምን ይመስላል? ከሰዎች ምንም ሳልጠብቅ መልካም ነገርን ላደርግላቸው እችላለሁን? ዝምታን እና ልዩነትን ለማስወገድ በቅድሚያ እርምጃን መውሰድ እችላለሁ? እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

በመካከላችን እና በዙሪያችን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበትን መሠረት ለመገንባት የሚያስችለንን ኃይል በመስጠት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።”

 

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካቲት 24/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ካደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ!

 

06 April 2024, 12:54