ፈልግ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የ10 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ የአፈፃፀም ምክክር እየተካሄደ ይገኛል የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የ10 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ የአፈፃፀም ምክክር እየተካሄደ ይገኛል 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የ10 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ የአፈፃፀም ምክክር እየተካሄደ ይገኛል

እንደሚታወቀው ታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአስር ዓመት ዕቅድ ትግበራ በርካታ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ማስጀመርዋ ይታወቃል። እነሆ ከአራት ወራት በኋላ በትግበራው አካሄድ ላይ ለመወያየት ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ከሚያዚያ 8 እስከ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የሚካሄድ ጉባኤ በካፑቺን ፍራንቸስካዊ የፍልስፍና እና የነገረ መለኮት ተቋም መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለአስር ዓመት ባዘጋጀችው ስልታዊ ዕቅድ ላይ በመመርኮዝ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ዓመታት የትግበራ ዕቅድ ላይ ለመወያየት ነው ጉባኤው የተዘጋጀው።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዚህ ጉባኤ ላይ ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንትን ጨምሮ የየሃገረ ስብከቱ ብጹአን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግላን፣ የጠቅላይ ጽ/ቤት የሥራ ሃላፊዎች፣ የካህናት ማኅበር ተወካይ፣ ከምእመናን፣ ከወጣቶች ቢሮ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል። 

የአስር ዓመት የቤተክርስቲያን አቀፍ ስልታዊ ዕቅድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጥረቶችን ለመምራት እና ለማስተባበር የተዘጋጀ ዋቢ ሰነድ ነው። ይህ ሰነድ በሁሉም የቤተክርስቲያኒቷ ባለድርሻ አካላት ሲካሄድ የነበረ ተከታታይ የአንድ ዓመት የውይይት ውጤት እንደሆነም ይታወቃል።

ይህ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአስር ዓመት ዕቅድ በአራት መሰረታዊ ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን እነዚህም የቤተክርስቲያን ቀኖናዊ መዋቅር፣ የሃዋሪያዊ አገልግሎት፣ የልግስና አገልግሎት እና የቤተክርስቲያን አስተዳደር ሲሆኑ፥ ከነዚህም በተጨማሪ ሥርዓታዊ አቅምን ማረጋገጫ የሆኑትን ከለላ እና ጥበቃ ማድረግ፣ ክትትል፣ ግምገማ፣ ተጠያቂነት እና መማማርን ማጎልበት እንዲሁም አካታችነት፣ ተግባቦት እና ዋቢነትን አካቶ የያዘ ሰነድ እንደሆነ ተገልጿል።

በመሆኑም እነዚህን የ10 ዓመት ዕቅዶች ለታለመላቸው ግቦች መሰረት ተፈፃሚ እንዲሆኑ ለማረጋገጥ በየተወሰነ ጊዜያት ትግበራው ላይ ክትትል ማድረግ ስለሚያስፈልግ በመላው ኢትዮጵያ የምትገኘውን ቤተክርስቲያን ጥረቶችን በጋራ አምጥቶ ለመወያየት ይህ የአራት ቀናት የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል።

እንደሚታወቀው ታህሳስ ወር ላይ የዕቅድ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ፣ የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴውም ሥራውን በማጠናቀቁ ይህንንም መሠረት በማድረግ በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያ የአስር ዓመት ዕቅድ ትግበራ አፈፃጸም ለመከታተል ኃላፊነት በመውሰድ፣ ባለቤትነትን ለመገንባት እና ስልታዊ ዕቅዱን ለመምራትና ለመከታተል አዲስ ብሔራዊ የስትራቴጂ ዕቅድ አስፈጻሚ ኮሚቴ መቋቋሙ ተገልጿል።

ይሄንን መርሃ ግብር ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፡ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት በጸሎት እና ቡራኬ ያስጀመሩ ሲሆን፥ ብጹእ አቡነ ሉቃስ የእምድብር ሃገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ በቤተክርስቲያን ቀኖናዊ አስተዳደር ላይ ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል።

“የቤተክርስቲያን አስተዳደር ብለን የምንጠራው የቤተክርስቲያን ሃዋሪያዊ አገልግሎት መስመር ማስያዣ መዋቅራዊ አደረጃጀትን የሚመለከት ነው” ያሉት ብጹእ አቡነ ሉቃስ፥ ይህ ደግሞ ከጳጳሳት ከተሰጠ ተልዕኮ የሚመነጭ ነው ብለዋል።

‘አንዲት ቤተክርስቲያ በሙላት አለች ብለን የምናስባት ቤተክርስቲያን በአንድ ጳጳስ የምትመራ ሃገረ ስብከት ውስጥ ስትገኝ ነው’ ካሉ በኋላ፥ ስለ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ስናወራ መሰረታችን ቀኖና ቤተክርስቲያን ነው፣ ስለቤተክርስቲያን አስተዳደር ስናወራ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሚያስተምሩበት መንገድ በአብሮነት፣ በተሳትፎ እና በተልዕኮ ቤተክርስቲያን እንዴት መቆም ትችላለች የሚለውን መሰረታዊ ጉዳይ የሚይዝ መሰረተ ሃሳብ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የአስር ዓመት እቅድ በየሶስት ዓመታት የተከፋፈለ እና ቀሪው የመጨረሻ አንድ ዓመት የተከናወኑት ሥራዎች የሚገመገሙበት እና ለቀጣይ አስር ዓመት ዕቅድ ግብዓቶች የሚለዩበት ዓመት እንደሆነም ተገልጿል።   

 ጉባኤው በሚቀጥሉት ቀናት በሃዋሪያዊ ሥራዎች እና በተለያዩ የቤተክርስቲያኒቷ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚወያይም ተነግሯል።

 

 

16 April 2024, 13:04