ፈልግ

መልካም ሥነ ምግባር መልካም ሥነ ምግባር  (©khanchit - stock.adobe.com)

መልካም ሥነ ምግባር

መልካም ሥራ ምንድነው?

መልካም ሥነ ምግባር ጥሩ ነገር የማድረግ የተለመደና ጽኑ አቋም ነው፡፡ «የጥሩ ሕይወት ዓላማ እንደ እግዚአብሔር ለመሆን ነው» (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኒሳ)፡፡ ሰብአዊ በጎ ሥራዎችና ነገረ መለኮታዊ በጎ ሥራዎች አሉ።ሰብአዊ መልካም ሥነ ምግባሮች ምንድናቸው? ሰብአዊ መልካም ሥነ ምግባሮች ሥራዎቻችንን የሚቆጣጠሩ፣ ስሜቶቻችንን የሚገዙና ድርጊታችንን በአእምሮና በእምነት መሠረት የሚመሩ የተለመዱና የረጉ የአእምሮና የፈቃድ ፍጽምናዎች ናቸው፡፡ የሚገኙትና የሚጠነክሩትም በግብረ ገብ ረገድ ጥሩ የሆኑ ሥራዎችን በመደጋገም ሲሆን፣ የሚጠሩትና የሚዳብሩት በመለኮታዊ ጸጋ ነው፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ዋና ዋና ሰብአዊ መልካም ሥነ ምግባሮች ምንድናቸው?

ዋና ዋና ሰብአዊ መልካም ሥነ ምግባሮች ህብረተሰቡ የሚያከብራቸው መልካም ባህርያት በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነርሱም ሌሎች መልካም ሥራዎች ሁሉ ተሰባስበው የሚገኙባቸውና የደግነትና የሕይወት መሠረቶች ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ የሚያከብራቸው መልካም ባህርያት አስተዋይነት፣ ፍትህ፣ ፅናት፣ እና መጠንን ማወቅ ናቸው፡፡ አስተዋይነት ምንድ ነው?

አስተዋይነት በማናቸውም ሁኔታ በእውነት የሚጠቅመንን ነገር ለይቶ ለማወቅና እርሱንም ለማግኘት የምንጠቀምበትን መንገድ ለመምረጥ አእምሮን የሚገፋፋ ነው፡፡ አስተዋይነት ሕጋቸውንና መጠናቸውን በማሳየት ሌሎች መልካም ሥነ ምግባሮችን ይመራል፡፡

ፍትህ ምንድነው?

ፍትህ ለሌሎች ሰዎች የሚገባቸውን ነገር የመስጠት ጽኑና ያልተቆጠበ ፈቃድን ያመለክታል፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ ፍትህ «የሃይማኖት በጎ ሥራ» ይባላል፡፡

ፅናት ምንድነው?

ፅናት በችግሮች ውስጥ ጥብቅ መሆንን እና መልካም ነገርን በመሻት ረገድ ቅንነትን ያረጋግጣል፡፡ ለተገቢው ዓላማ የራስን ሕይወት እስከመሠዋት ያደርሳል፡፡

መጠንን ማወቅ ምንድነው?

መጠንን ማወቅ የደስታን ፍላጎት ያለዝባል፣ ፈቃደ ተፈጥሮአዊ ግፊትን እንዲገዛ ያደርጋል፣ የተፈጠሩ ነገሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ያስችላል፡፡

ነገረ መለኮታዊ መልካም ሥነ ምግባሮች ምንድናቸው?

የነገረ መለኮታዊ መልካም መልካም ሥነ ምግባሮች መሠረታቸው፣ ዓላማቸውና ቀጥታ ግባቸው እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ በሚቀድስ ጸጋ የተነቃቁ ስለሆኑ ሰውን ከቅድስት ሥላሴ ጋር በመልካም ግንኙነት እንዲኖር ያስችሉታል፡፡ የክርስቲያን ግብረገባዊ ሥራ መሠረትና አነቃቂ ኃይል ናቸው፤ ለሰብአዊ መልካም ሥነ ምግባሮች ሕይወት ይሰጣሉ፡፡ በሰው ልጅ የተፈጥሮ ችሎታዎች ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ መገኘትና ሥራ ማረጋገጫ ናቸው፡፡ ነገረ መለኮታዊ መልካም ሥነ ምግባሮች የትኞቹ ናቸው?

ነገረ መለኮታዊ መልካም ሥነ ምግባሮች እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ናቸው፡፡

የእምነት መልካም ሥነ ምግባር ምንድነው?

እምነት በእግዚአብሔርና እርሱ በገለጸልን ነገር ሁሉ እንዲሁም እግዚአብሔር ራሱ እውነት በመሆኑ ቤተክርስቲያን ስለእምነታችን የምትነግረንን ነገር የምናምንበት ነገር መልኮታዊ መልካም ሥነ ምግባር ነው፡፡ በእምነት ሰው ራሱን በፈቃዱ ለእግዚአብሔር አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ፣ አማኙ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅና ለመፈጸም ይፈልጋል፣ ምክንያቱም «እምነት የሚሠራወ በፍቅር ነው» (ገላ 5፡6)፡፡

ተስፋ ምንድነው?

ተስፋ ክርስቶስ በሰጠን በተስፋ ቃላት በመተማመንና እርሱንም በሚሰጠውና እስከምድራዊ ሕይወታችን መጨረሻ ድረስ በሚጠብቀው በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በመታገዝ ከእግዚአብሔር የዘላለማዊ ሕይወት ደስታን ለማግኘት የምንመኝበትና የምንጠባበቅበት ነገር መለኮታዊ መልካም ሥራ ነው፡፡

ፍቅር ምንድነው?

ፍቅር እግዚአብሔርን ከሁሉም ነገር አብልጠን፣ ባልንጀራችንን ደግሞ ስለእግዚአብሔር ፍቅር ብለን እንደራሳችን የምንወድበት ነገር መለኮታዊ መልካም ሥነ ምግባር ነው፡፡ ኢየሱስ ፍቅርን አዲሱ ትዕዛዝና የሕግ ፍጻሜ አደረገው፡፡ «ፍቅር የፍጻሜ ማሠሪያ ነው» (ቆላ 3፡14)፡፡ እንደዚሁም ሕይወት፣ እንቅስቃሴና ሥርዓት ለሚሰጣቸው ለሌሎች መልካም ሥራዎች መሠረት ነው፡፡ ፍቅር ከሌለኝ «ከንቱ ነኝ»፣ «ምንም አይጠቅመኝም» (1ኛ ቆሮ 13፡ 1-3)፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ምንድናቸው?

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች መለኮታዊ ቅስቀሳዎችን ለመከተል ታዛዦች የሚያደርጉን ቋሚ ባህርያት ናቸው፡፡ እነርሱም ሰባት ናቸው፡- ጥበብ፣ ብልህነት፣ ምክር፣ ፅናት፣ ዕውቀት፣ መንፈሳዊነት እና እግዚአብሔርን መፍራት ናቸው፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ምንድናቸው?

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የዘላለማዊ ክብር የመጀመሪያ ፍሬዎች የሆኑና በውስጣችን የተፈጠሩ ፍጽምናዎች ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያን ትውፊት የሚዘረዝራቸው አስራ ሁለት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አሉ፡፡ እነርሱም፡- ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትእግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ለጋስነት፣ ጨዋነት፣ ታማኝነት፣ ትሕትና፣ ራስን መግዛትና ንጽሕና ናቸው (ገላ. 5፡22-23)፡፡

03 April 2024, 13:28