ፈልግ

አባ ኢብራሂም ፋልታስ፣ የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን አባ ኢብራሂም ፋልታስ፣ የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን  

አባ ፋልታስ ‘ክርስቲያኖች ባላቸው እምነት እና ተስፋ በቅድስት ሀገር ያለውን ጦርነት ተቋቁመዋል’ አሉ

በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ በቅድስት ሀገር ውስጥ ያሉ ክርስቲያን ማህበረሰቦች የሚያጋጥሟቸውን መከራዎች በመግለጽ፥ በችግር ጊዜ የአብሮነት፣ የጸሎት እና የማይናወጥ እምነት አስፈላጊነትን አስምረውበታል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅድስት ሀገር ተንከባካቢ ካህን አባ ኢብራሂም ፋልታስ ከቫቲካን የፊደስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በቅድስት ሀገር የሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት  የሚያጋጥሟቸውን በርካታ ፈተናዎች ጠቁመዋል።

የጉዳዩን አሳሳቢነት በማጉላት የጀመሩት አባ ፋልታስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሁል ጊዜ የሚናገሩትን በመጥቀስ “ጦርነት ምንጊዜም ሽንፈት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የክርስቲያኑ ማህበረሰብ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች

አባ ፋልታስ በጋዛ ውስጥ የሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በማብራራት፥ “በቁጥር አነስተኛ የሆኑ በቅድስቲቱ ምድር ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖች ይሄንን ሁኔታ መጋፈጥ በጣም ከባድ ነው” ብለዋል።

አባ ፋልታስ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት አንድ የደብር ካህን ከስድስት ወራት ግጭት በኋላ የተገኘች አንዲት ቀይ አፕል ከምዕመናን ጋር የተካፈሉበትን አንድ ልብ የሚነካ ክስተት በማስታወስ ተናግረዋል።

ዌስት ባንክ እና እስራኤል

አባ ፋልታስ ስለዌስት ባንክ እና እስራኤልን ጉዳይ በማንሳት፥ ግጭቱ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርሳቸውን ችግሮች ጎላ አድርገው ገልጸዋል። ይሄንንም በማስመልከት ሲያብራሩ፥ “ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ወደ ዌስት ባንክ መንፈሳዊ ጉዞ ያደርጉ የነበሩ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት ስላቋረጡ በዚህም የተነሳ በዌስት ባንክ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ገቢያቸው ስለቀነሰ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፥ ቤተሰቦቻቸውም ተስፋ ቆርጠዋል፣ ብዙዎች ቅድስቲቱን ምድር ለቀው መውጣት ይፈልጋሉ” ካሉ በኋላ፥ “በተመሳሳይ መልኩ በእስራኤል የሚገኙ በርካታ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ጦርነቱ ባስከተለው ችግር ምክንያት እየተሰቃዩ ይገኛሉ” ብለዋል።

አባ ፋልታስ በመቀጠል፣ በዌስት ባንክ እና በጋዛ ውስጥ ያሉ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ተገናኝተው የሚያጋጥሟቸው ችግሮች በጋራ ለመቅረፍ የማይቻል መሆኑን በመግለጽ፥ “እንደ አለመታደል ሆኖ በቅድስት ሀገር ውስጥ የሚኖሩ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ምንም እንኳ እነዚህ አከባቢዎች በመልክአ ምድራዊ አቀማመጣቸው የሚቀራረቡ ቢሆንም፥ ባለው ችግር ምክንያት ማህበረሰቡ በአካል እርስ በርስ ሊገናኙ አይችሉም፥ ሆኖም ግን እግዚአብሔር ይመስገን ቴክኖሎጂ እርስ በርስ እንድንነጋገር እና እርስ በርሳችሁ በጸሎት እንድንደጋገፍ አስችሎናል” ብለዋል።

በሰው ህይወት ላይ የሚደርስ አስከፊ ጉዳት

አባ ፋልታስ የግጭቱን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲያብራሩ ተጠይቀው “እኔ የፖለቲካ ተንታኝ አይደለሁም” በማለት ከመተንተን ተቆጥበዋል። ሆኖም ግን “ሰላም በሚያስፈልገው በዚህ የዓለማችን ክፍል ሰላም እንዲመጣ ለማስቻል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ መግባት እንዳለበት የብዙ ዓመታት እምነቴ ነው” በማለት በተለይ በንጹሐን ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሞት አደጋ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

“በአከባቢው ላይ የሚገኙ ህፃናት፣ በዓለም ላይ እንዳሉት ሁሉም ህፃናት፣ የዚህ አስከፊ ጦርነት የመጀመሪያ ሰለባዎች ናቸው፥ ዜግነታቸው ወይም ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን በልጆች ላይ የሚደርሰውን የስነ ልቦና ጉዳት ማን ሊያክመው ይችላል?” በማለት በመገረም ጠይቀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፡ የሰላም አጋር

አባ ፋልታስ በማጠቃለያቸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለሰላም ሲሉ ላደረጉት ማለቂያ የሌለው ድጋፍ በማመስገን፥ “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሰላም ጥሪ በቅድስት ሀገር ለሚገኙ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ድጋፍ እና ጥንካሬ ይሆናቸዋል፥ እመነኝ፣ ይህ ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ይሆናል” ካሉ በኋላ፥ “ብጹእነታቸው የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በተደጋጋሚ እና ለረጅም ጊዜያት ጥሪ ሲያደርጉ የነበሩ የመጀመሪያው እና ብቸኛው ሰው ናቸው” በማለት ገልጸዋል።
 

11 April 2024, 16:21