ፈልግ

የዛሬው ዓለም አንዳንድ ተግዳሮቶች የዛሬው ዓለም አንዳንድ ተግዳሮቶች  (AFP or licensors)

በጋራ ስምምነት መሐል ያለ ቀውስ

ከስብከተ ወንጌል ሥራ ጋር የተያያዙ አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ከማንሣቴ በፊት፣ መኖርና መሥራት ስላለብን በአጭሩ መጥቀሱ ሊጠቅም ይችላል። ዛሬ፣ ሁል ጊዜ እየተሻሻሉ ከመጡና በትክክል ሥራ ላይ ከሚውሉ የሕክምና ዘዴዎች ጋር ስለማይገናኘው ‹‹የምርመራ ጫና›› ዘወትር እንሰማለን። ገለልተኛና የምርመራ ዘዴን የሚከተል የሚመስለውና ሁሉንም እውነታ የማካተት ዓላማ ያለው ኅብረተሰባዊ ትንተናም ቢሆን በሚገባ ሊያገለግለን አይችልም። እኔ ለማቅረብ የምፈልገው ሃሳብ ይበልጥ ከወንጌላዊ ምክር ጋር የተያያዘ ነው። ‹‹በመንፈስ ቅዱስ ብርሃንና ብርታት የተሞላ›› የወንጌል መልእክተኛን አቀራረብ ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ስለ ዘመኑ እውነታ ዝርዝርና የተሟላ ትንታኔ መስጠት የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ተግባር አይደለም። ይሁን እንጂ፣ ‹‹የዘመኑን ምልክቶች በጥንቃቄ እንዲያስተውሉ›› ማኅበረሰቦችን ሁሉ አደራ እላለሁ። ይህ በመሠረቱ ከባድ ኃላፊነት ነው፤ ምክንያቱም፣ አንዳንድ እውነታዎች በሚገባ ካልተያዙ የኋላ ኋላ ለመመለስ ከባድ የሚሆኑ የሰውን ልጅ ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ሂደቶችን ሊያስነሡ ይችላሉና። የመንግሥተ ሰማይ ፍሬን የእግዚአብሔርን ዕቅድ ከሚቃወም ነገር በሚገባ መለየት ያስፈልገናል። ይህም መናፍስትን ማወቅና መለየትን ብቻ ሳይሆን ወሳኝ በሆነ መልኩ የመልካም መንፈስ እንቅስቃሴዎችን መምረጥንና ክፉ መንፈስን ደግሞ መጥላትን ያካትታል። የኩላዊት ቤተክርስቲያን የማስተማር ሥልጣን ያቀረባቸው ሌሎች ሰነዶች እንዲሁም በአካባቢና በብሔራዊ የጳጳሳት ጉባኤዎች የቀረቡ ሰነዶች የያዙአቸውን የተለያዩ ትንተናዎች እንዳሉ ተቀብያለሁ። በዚህ የማበረታቻ መልእክት ውስጥ በአጭሩና ከሐዋርያዊ ሥራ አኳያ ብቻ የምመለከታቸው አንዳንድ ጉዳዮች አሉ፣ እነርሱም የሕዝበ እግዚአብሔርን ሕይወትና ክብር የሚጎዱ ወይም በቤተክርስቲያን ተቋማትና በእርስዋም የስብከተ ወንጌል ሥራ ቀጥታ ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች የሚነኩ በመሆናቸው በቤተክርስቲያን ውስጥ የስብከተ ወንጌል ተሐድሶን ስሜት የሚገቱ ወይም የሚያዳክሙ ናቸው።

የዛሬው ዓለም አንዳንድ ተግዳሮቶች

በዘመናችን የሰው ዘር በታሪኩ ልዩ ምእራፍ ላይ ይገኛል፤ ይህንንም በብዙ መስኮች ከተደረጉ መሻሻሎች መረዳት እንችላለን። በጤና፣ በትምህርትና በመገናኛ ዘርፎች የተገኙና የሕዝብን ደህንነት ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎችን እናደንቃለን። በአንፃሩም በዘመናችን ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን በችግር እየገፉ መሆናቸውን መርሳት የለብንም። አያሌ በሽታዎች እየተስፋፉ ናቸው። የብዙ ሰዎች ልብ ሀብታም በሚባሉ አገሮች ጭምር በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ተሞልቶአል። የመኖር ደስታ ብዙ ጊዜ ይደበዝዛል፣ ሌሎችን ያለማክበር ሁኔታና ሁከት እየጨመረ ነው፤ የኑሮ አለመጣጣምም በገሃድ እየታየ መጥቷል። ለመኖር ትግል አለ። ለዚህ  የዘመኑ ለውጥ መነሻ የሆነው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጥራት፣ በመጠን፣ በፍጥነትና በጅምላ እየተፈጸሙ የሚገኙ መሻሻሎች መኖራቸውና እነርሱም በተለያዩ የተፈጥሮና የሕይወት አካባቢዎች ተግባራዊ መደረጋቸው ነው።  እኛ ወደ አዲስና ብዙውን ጊዜ ወዳልታወቁ የሥልጣኔ ዓይነቶች በሚመራ የዕውቀትና የመረጃ ዘመን ላይ እንገኛለን።

እምቢ ለአግላይ ኢኮኖሚ

የሰውን ሕይወት ክብር ለመጠበቅ ሲባል ‹‹አትግደል›› የሚለው ትዕዛዝ ግልጽ ገደብ እንደሚያስቀምጥ ሁሉ ዛሬ አግላይና አበላላጭ ኢኮኖሚ ‹‹አይኑር›› ማለት አለብን። እንዲህ ዓይነቱ ኢኮኖሚ ይገድላል። አንድ በረንዳ አዳሪ ሽማግሌ በችግር ሲሞት ዜና አይሆንም፣ የፋይናንስ ገበያ በሁለት ነጥብ ሲወድቅ ግን ዜና የሚሆነው እንዴት ነው? ይህ የአግላይነት ማሳያ ነው። ሰዎች ተርበው ሳለ ምግብ ሲጣል እያየን በዝምታን እንቀጥል ወይ? ይህ የማበላለጥ ማሳያ ነው። ዛሬ ሁሉም ነገር በውድድር ሕግና ኃያላን አቅመ ቢሶችን መጠቀሚያ በሚያደርጉበት ‹የቻለ ይኑር› በሚያሰኝ ሥርዓት ሥር ወድቋል። ከዚህም የተነሣ ብዙሃን ተገልለዋል፣ ርቀዋል፤ ያለ ሥራ፣ ያለ ተስፋና ያለ አንዳች ማምለጫ ቀርተዋል። ሰዎች እንደሸቀጥ ተቆጥረዋል። አሁን እየሰፋ የመጣ ‹‹የመጣል›› ባህል ፈጥረናል። ጉዳዩ የብዝበዛና የጭቆና ብቻ መሆኑ ቀርቶ አዲስ ነገር ሆኖአል።  በመጨረሻም መገለል የምንኖርበት ህብረተሰብ አካል የመሆን ትርጉም  እንደሆነ ያሳያል። የተገለሉ ሰዎች የህብረተሰብ አካል እንኳ አይደሉም። የተገለሉ ሰዎች ‹‹የተጨቆኑ›› ሳይሆኑ የተጠሉ፣ ‹‹የተጣለ ፍርፋሪ›› ሆነዋል።

በዚህ አገባብ፣ አንዳንድ ሰዎች “በነጻ ገበያ የተደገፈ የኢኮኖሚ ዕድገት በዓለም ውስጥ የተሻለ ፍትህና አሳታፊነትን ማምጣቱ አይቀርም” የሚለውን የመንጠባጠብ ንድፈ ሀሳብ መደገፋቸውን ቀጥለዋል። በእውነታዎች ከቶ ያልተረጋገጠው ይህ አስተሳሰብ የኢኮኖሚ ሥልጣን በጨበጡ ወገኖች ቸርነትና ተንሰራፍቶ በሚገኘው የኢኮኖሚ ሥርዓት አሠራር ላይ ያለውን ያልተስተካከለና ገራገር እምነት ያንፀባርቃል። የተገለሉ ወገኖች ግን አሁንም በተስፋ እየጠበቁ ነው። ሌሎችን የሚያገልል የአኗኗር ዘዴ ለመከተል ወይም ያንን የራስ ወዳድነት ዓላማ ለማሳካት የሚረዳ የግድ የለሽነት ዓለም ተፈጥሮአል። ከዚህም የተነሣ ሳናስተውለው የድሆችን ጩኸት ሰምቶ የመራራት፣ የሌሎች ሰዎችን ሕመም አይቶ የማልቀስና እነርሱንም የመርዳት ስሜት እናጣለን። ይህ ሁሉ የራሳችን ሳይሆን የሌላ ሰው ኃላፊነት እንደሆነ አድርገን እንቆጥራለን። የብልጽግና ባህል ይገድለናል፤ ገበያ የምንገዛውን አዲስ ነገር ሲሰጠን እንደነቃለን፤ ተስፋ አጥተው የቀጨጩ እነዚያ ሕይወቶች አያሳስቡንም።

ምንጭ፡ የወንጌል ደስታ በተሰኘ አርዕስት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ያስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ከአንቀጽ 50-54 ላይ የተወሰደ!

22 April 2024, 16:53