ፈልግ

እምቢ ሁከትን ለሚያራባ መበላለጥ እምቢ ሁከትን ለሚያራባ መበላለጥ  (ZOHRA BENSENRA)

እምቢ ሁከትን ለሚያራባ መበላለጥ

ዛሬ በብዙ ቦታዎች ለተሻለ ደህንነት ጥሪ ሲደረግ እንሰማለን። ይሁን እንጂ፣ በኅብረተሰብና በሕዝቦች መካከል ያለው መገለልና መበላለጥ ካልተቀየረ ሁከትን ማስወገድ አይቻልም። ድሆችና ይበልጥ ድሃ የሆኑ ሕዝቦች ሁከት አስነሡ ተብለው ይከሰሳሉ፤ ነገር ግን እኩል ዕድል በሌለበት የተለያዩ ጠብ የመጫርና የግጭት ዓይነቶች የሚጠነሰሱበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፣ በመጨረሻም ይፈነዳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

አንድ አካባቢያዊ፣ ብሔራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ህብረተሰብ አንዱን የራሱን ክፍል ወደ ዳር ለመግፋት ፈቃደኛ ከሆነ፣ የፖለቲካ ፕሮግራሞችም ሆኑ ለሕግ ማስከበር ወይም ለስለላ ሥርዓት የሚደረጉ ወጪዎች ለዘላቂ ሰላም ዋስትና ሊሆኑ አይችሉም። ይህም ሊሆን የቻለው መበላለጥ ከሥርዓቱ የተገለሉ ወገኖችን በሁከት የታጀበ ምላሽ ስለሚቀሰቅስ ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበረ ኢኮኖሚአዊ ሥርዓቱ ከመሠረቱ ፍትሃዊ ስላልሆነ ነው። ደግነት እንደሚስፋፋ ሁሉ፣ ኢ-ፍትህንና ክፉ ነገርን መታገሥ ደግሞ የጥፋት ተጽእኖውን ሊያሰፋና ምንም ያህል ብርቱ የሚመስለውን ማንኛውንም የፖለቲካና ማህበራዊ ሥርዓት ቀስ በቀስ ሊሸረሽረው ይችላል።

ማንኛውም ድርጊት የራሱ የሆኑ ውጤቶች ካሉት፣ በአንድ ህብረተሰብ መዋቅሮች ውስጥ ተሰግስጎ የሚገኘውን ክፉ ነገር የማፈንዳትና ለሞት የማጋለጥ ዘላቂ አቅም አለው። ኢ-ፍትሃዊ ባልሆኑ ማኅበራዊ መዋቅሮች ውስጥ የተንሰራፋ ክፋት ለተሻለ መጪ ጊዜ የተስፋ ምንጭ ሊሆን አይችልም። ለዘላቂና ሰላማዊ ዕድገት ምቹ ሁኔታዎች ገና በበቂ መጠን ባለመገለጻቸውና ባለመገኘታቸው ‹‹የታሪክ መጨረሻ›› ወደሚባለው ደረጃ ገና አልደረስንም።

የዛሬ የኢኮኖሚ አሠራሮች ገደብ የለሽ ፍጆታን ያበረታታሉ፤ ነገር ግን ያልተገታ የፍጆታ ሥርዓት ከመበላለጥ ጋር ተደምሮ ማኅበራዊ አቋምን በእጥፍ ይጎዳል። መበላለጥ የኋላ ኋላ በመሣሪያ ኃይል ከቶ ሊፈታ የማይችል ሁከትን ይወልዳል። ዛሬ የጦር መሣሪያዎችና ሁከት መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ አዲስና የተባባሱ ግጭቶችን እንደሚፈጥሩ ብናውቅም፣ ይህ ሁኔታ የተጠናከረ ደህንነት እንዲኖር ለሚጮሁ ወገኖች ባዶ ተስፋ ብቻ ይሰጣቸዋል። አንዳንዶች ለችግሮቻቸው ራሳቸውን ድሆችንና እጅግ ድሃ አገሮችን በመውቀስ ብቻ ይረካሉ፤ አግባብ ባልሆኑ ጥቅል ሃሳቦች ላይ በማተኮር መፍትሄው ጸጥ የሚያሰኛቸው፣ ለማዳና ገራገር የሚያደርጋቸው ‹‹ትምህርት›› ነው ይላሉ። ይህ ሁሉ የመሪዎቻቸው የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም ምንም ዓይነት ቢሆን፣ በብዙ አገሮች፣ በመንግሥቶቻቸው፣ በንግድ ድርጅቶቻቸውና ተቋሞቻቸው ውስጥ ተስፋፍቶና ሥር ሰድዶ የሚያዩ ግፉአንን ይበልጥ የሚያበሳጭ ነው።

ምንጭ፡ የወንጌል ደስታ በተሰኘ አርዕስት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዓለም ወንጌልን ስለ መስበክ ለጳጳሳት፣ ለካህናት፣ ለደናግልና ለምእመናን ያስተላለፉት ሐዋርያዊ  ምክር ከአንቀጽ 55-62 ላይ የተወሰደ!

25 April 2024, 18:08