ፈልግ

በትግራይ ክልል አቢ አዲ ከተማ የሚገኘው የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች - የፋይል ፎቶ በትግራይ ክልል አቢ አዲ ከተማ የሚገኘው የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች - የፋይል ፎቶ  

ብጹእ አቡነ ተስፋሥላሴ በትግራይ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቅረፍ እንዲቻል የእርዳታ ጥሪ አቀረቡ

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የዓዲግራት ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ተስፋስላሴ በትግራይ ሰሜናዊ ክልል እየደረሰ ባለው አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ ወሳኝ የሆነ እርዳታ እንዲደረግ ተማጽነዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብጹእ አቡነ ተስፋሥላሴ መድህን በጻፉት ይፋዊ ደብዳቤ በኢትዮጵያ፣ ትግራይ ክልል ለዓመታት በዘለቀው ግጭትና ድርቅ እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት ከማዕከላዊ መንግስት ጋር ግንኙነት በመቋረጡ ምክንያት በሕዝቡ በተለይም በሴቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ፣ ተስፋ መቁረጥ እና ሞት አጉልተው አሳይተዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በግጭቱ ምክንያት ከአከባቢያቸው እንደተፈናቀሉ በመጥቀስ፥ በአሁኑ ጊዜ በትግራይ የተለያዩ ከተሞች እና በአጎራባች ክልሎች ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑን፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየጨመረ በመምጣቱ እና አንገብጋቢ የሆኑ ሰብአዊ ፍላጎቶችን ለመቅረፍ ቁርጠኝነት እንደሌለም ጭምር አስምረውበታል።

ብጹእ አቡነ ተስፋሥላሴ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በተጻፈው ደብዳቤያቸው ላይ ያቀረቡት የተግባር ጥሪ ግልፅ ነው፤ በትግራይ እና አጎራባች ክልሎች ውስጥ ያሉ ተጋላጭ የሆኑ ህዝቦችን ለመደገፍ ተጨማሪ ግብአት ያስፈልጋል።

አስቸኳይ ሰብአዊ ዕርዳታ ለመስጠት እና ክልሉ በዘላቂነት ከጉዳቱ መልሶ እንዲያገግም ብሎም ሰላም እንዲሰፍን መንገድን ለመክፈት ‘የሰብአዊ ዕርዳታ እቅድ’ (HRP) ለተባለው የዕርዳታ ኤጀንሲ ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል።

ብጹእነታቸው እንደገለጹት ከአስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ ባለፈ፥ ከአጎራባች ክልል ጋር ያለውን የወሰን ጥያቄ ተግዳሮት ገና እንዳልተፈታም አንስተዋል።

በአማራ እና አፋር ክልል የሚገኙ የትግራይ እና አጎራባች ማህበረሰቦችን እየጎዳ ያለውን ውስብስብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ቀውስ በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰው፥ በተለይም እንደ ኢሮብ እና ኩናማ ያሉ የተገለሉ ማህበረሰቦች እየደረሰ ባለው ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ ሰለባ መሆናቸውን አስምረውበታል።

ብጹእ አቡነ ተስፋሥላሴ ወደ ፊት፣ በቅርብ ጊዜ ሊገመቱ የማይችሉ ዝናብ፣ ድርቅ እና ጎርፍ ያሉ ሁኔታዎችን ሊያባብሱ የሚችሉ የአየር ንብረት ለውጦች መኖራቸውን አስጠንቅቀዋል። እነዚህን ተጽኖዎች ለመቅረፍ እና ተጨማሪ ስቃይን ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግም ጠይቀዋል።

ጳጳሱ በማጠቃለያቸው የትግራይ ህዝብና አዋሳኝ ክልሎች ይህንን ችግር ሊወጡ እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
 

19 April 2024, 17:06