ፈልግ

በአውሮፓ ኅብረት ክልል ውስጥ የሚገኙ የካቶሊክ ጳጳሳት ፅንስ ማስወረድ መሠረታዊ መብት ሊሆን እንደማይችል ገለጹ

በአውሮፓ ኅብረት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ቻርተር ውስጥ ፅንስ የማቋረጥ መብትን ለማካተት ሚያዝያ 3/2016 ዓ. ም. በብራስልስ ድምጽ ከመስጠቱ አስቀድሞ፥ የአውሮፓ ኅብረት ካቶሊክ ጳጳሳት (COMECE) ሐሳቡን በጥብቅ ተቃውመው አስገዳጅ ርዕዮተ ዓለማዊ ሂደትን አውግዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አንድ ሰው በማንኛውም ሁኔታ እና በማንኛውም የዕድገት ደረጃ ዘወትር የተቀደሰ እና ክብሩም ሊጣስም እንደማይገባ  የገለጹት የአውሮፓ ኅብረት አገራት ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፥ ይህ እምነት አንዴ ከጠፋ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ጠንካራ እና ዘላቂ የሆኑ መሠረቶችም እንደሚጠፉ በመግለጫቸው አረጋግጠዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ (COMECE) መግለጫውን የሰጠው፥ ብራስልስ ውስጥ ሐሙስ ሚያዝያ 3/2016 ዓ. ም. በሚካሄደው ምልአተ ጉባኤ ላይ በአውሮፓ ኅብረት የመሠረታዊ መብቶች ቻርተር ውስጥ ፅንስ የማቋረጥ መብትን ለማካተት ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት እንደሆነ ታውቋል።

የብጹዓን ጳጳሳቱ መግለጫ ይፋ የሆነው፥ በቅድስት መንበር የእምነት አስተምህሮ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮዎችን መሠረት ያደረገ፥ ‘Dignitas infinita’ ወይም “ገደብ የለሽ የሰው ልጅ ክብር” የተሰኘ አዲስ ሠነድ ይፋ ባደረገበት ማግሥት ሲሆን፥ ሠነዱ ጽንስ ማስወረድ በሰው ልጅ ክብር ላይ የሚፈጸም ከባድ እና አሳፋሪ ጥሰት እንደሆነ ገልጿል።

የሴቶችን መብቶች ማስተዋወቅ ይቃወማል

ብጹዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው እናት መሆን ለሴቶች እና ለህብረተሰቡ ስጦታ እንደሆነ፣ ልጆቻቸውን በነጻነት የሚወልዱባት፣ ለማኅበራዊ እና ሙያዊ ሕይወት በምንም መልኩ ገደብ የሌለባት አውሮፓን ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ፅንስ ማስወረድ በፍፁም መሠረታዊ መብት ሊሆን አይችልም በማለት ደጋግመው የተናገሩት ጳጳሳቱ፥ ፅንስ ለማስወረድ ማበረታታት እና ማመቻቸት የሴቶችን መብቶች ከማስተዋወቅ እና ከማስከበር በተቃራኒ አቅጣጫ የሚሄድ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ለሁሉም ሰው መሠረታዊ መብት ሊኖር ይገባል

የመኖር መብት ለሌሎች ሰብዓዊ መብቶች በሙሉ መሠረታዊ ምሰሶ ነው ያሉት በአውሮፓ ኅብረት ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፥ በተለይም ተጋላጭ ለሆኑ፣ ደካማ እና መከላከያ ለሌላቸው፣ በእናት ማህፀን ውስጥ ላለ ፅንስ፣ ለስደተኛ፣ ለአዛውንት፣ ለአካል ጉዳተኛ እና ለሕሙማን በሕይወት መኖር መሠረታዊ መብት እንደሆነ ገልጸዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጉዳይ ላይ የወሰደችውን ግልጽ አቋም በማስታወስ፥ ገና ያልተወለደን ሕይወት መጠበቅ የእያንዳንዱን እና የሌላውን ሰብዓዊ መብት ከማስጠበቅ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ አስረድተዋል። አንድ ሰው ገና ስላልተወለደ ሕይወት ክብር መረዳት ካልቻለ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ማወቅ እንደማይችል “ገደብ የለሽ የሰው ልጅ ክብር” የተሰኘ አዲስ ሠነድን በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።

የአውሮፓ ኅብረት አገራት ጳጳሳት በአባል አገራቱ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ባህሎች እና ወጎች እና ብሔራዊ ብቃቶች ማክበር እንደሚገባ እና በሌሎች ሰዎች ላይ ከውስጥም ሆነ ከድንበር ውጭ ርዕዮተ-ዓለማዊ እና ጾታዊ ጫናን ማድረግ እንደማይገባ ተናግረዋል።

ቻርተሩ በሁሉም ዘንድ ያልታወቁ መብቶችን ሊያካትት አይችልም

የአውሮፓ ኅብረት የመሠረታዊ መብቶች ቻርተር በሁሉም ዘንድ የማይታወቁ እና ከፋፋይ የሆኑ መብቶችን ሊያካትት እንደማይችል የገለጹት ጳጳሳቱ፥ በአባል አገራት ሕገ-መንግሥታት እና ሕጎች ውስጥ መካተቱ እንደሚለያይ ተናግረው፥ የአውሮፓ ኅብረት ጳጳሳት፥ በቻርተሩ መግቢያው ላይ እንደተጻፈው፥ የአውሮፓ ሕዝቦች፣ ባህሎች እና ወጎች ልዩነት እንዲሁም ሕገ-መንግሥታዊ እና ዓለም አቀፍ ወጎችን ማክበር ለአባል አገራት የጋራ ግዴታዎች እንደሆነ በመጥቀስ መግለጫቸውን አጠቃልለዋል።

 

 

 

10 April 2024, 16:13