ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ጆርጂዮ ማሬንጎ የትንሳኤውን ሻማ ሲያበሩ ብፁዕ ካርዲናል ጆርጂዮ ማሬንጎ የትንሳኤውን ሻማ ሲያበሩ  

በሞንጎሊያ ውስጥ የሚከበረው የትንሳኤ በዓል አከባበር የነዋሪዎቹን የሰከነ ደስታ ያሳያል ተባለ

የኡላንባታር ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ጆርጂዮ ማሬንጎ በሞንጎሊያ የሚገኘውን አነስተኛ የካቶሊክ ማኅበረሰብ ሥርዓትና ወግ ሲገልጹ ‘‘ትሪዱም’ (ከስቅለት እስከ ትንሳኤ ያሉት ሶስቱ ቀናት) ተብለው በካቶሊካዊያን በሚከበሩት ቀናት ምዕመኑ ክርስቲያናዊ ደስታቸውን ለመግለጽ በሰከነ መንፈስ አንድ ላይ ይሰበሰባሉ’ በማለት ያካፈሉት ጽሁፍ እንደሚከተለው ይቀርባል፦

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሞንጎሊያ ውስጥ የሚከበረው የህማማት ሳምንት ወይም ቅዱስ ሳምንት እንደ እውነተኛ ጥንካሬ፣ አይነተኛ እና ልዩ ጊዜ ተደርጎ ይከበራል። ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ትምህርተ ክርስቶስን ሲከታተሉ የነበሩ ጎልማሶች ይሄንን ወቅት የሕይወታቸው መሠረታዊ የለውጥ ጎዳና አድርገው ለዚህ ጊዜ ይዘጋጃሉ።

በዚህ ጉዞ ከእነርሱ ጋር መሆናችን እኛ ሚስዮናውያን የዚህን ምስጢር ድንቅ እና ሥር ነቀል ተፈጥሮ እንድናስታውስ ይረዳናል።

ከዚህ አንጻር የክርስቶስን ሞት እና ትንሳኤ ወደ ሕይወታቸው ለመቀበል ከሚፈልጉ ወንድሞች እና እህቶች ጋር እዚህ መገኘታችን በዓሉን የራሳችን አድርገን በጥንካሬ እና በአዲስ ግንዛቤ እንድንኖር ያበረታታናል።

በህማማት እሁድ ወይም በሆሳዕና ማህበረሰቦቻችን ቀጫጭን የሾላ ቅርንጫፎችን ሲያውለበልቡ (ምክንያቱም የዘንባባ እና የወይራ ዛፎች በአከባቢው ስለማይበቅሉ) ከሃይማኖታዊ ተምሳሌትነቱ በተጨማሪ ረዥሙን የክረምት ወቅት ማገባደዳቸውንም የሚገልጹበት መንገድ ነው።

በባለሥልጣናት እውቅና በተሰጣቸው ቦታዎች ውስጥ ብቻ የሚካሄዱት እነዚህ መጠነኛ ትእይንቶች ብዙውን ጊዜ በብርድ እና አቧራማ ነፋሶች የታጀቡ ናቸው።

እዚህ የፀደይ ወቅት በጣም ፈታኝ ጊዜ ነው፥ ድንገተኛ የአየር ሙቀት መጨመር፣ የተዳከሙ መንጋዎች እና ሰውነታቸው የመነመነ ሰዎች በብዛት የሚታይበት ወቅት ነው። የመታደሳችን ምስጢር በጣም ወሳኝ በሆነው የተፈጥሮ ኡደት ወቅት ይገለፃል፥ ጌታችን ይህንን ወቅት የመረጠው ከድሃው የሰው ልጅ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ለመድረስ በሚመስል መልኩ ነው።

ወደ ማክሰኞ የተሸጋገረው የጸሎተ ሃሙስ ክብረ በዓል ከሩቅ ቦታዎች ለሚመጡ ካህናት ጭምር በጣም ልዩ ቀጠሮ ተደርጎ ይጠበቃል።  ካህናቱ ከጥቂት ምዕመናን እና ከበርካታ ገዳማዊያት እህቶች ጋር ሆነው በካቴድራል የክህነት ቃል ኪዳናቸውን ያድሳሉ። ከዚያም ስለ ክህነት ምስጢር ለአጭር ጊዜ ቆም ብለን ካሰላሰልን በኋላ ምሳችንን በደስታ አብረን እንካፈላለን።

በረዷማ መንገዶች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለማስቀረት ወደ ደብሮቻችን በጊዜ መመለስ አለብን።  እያንዳንዱ ደብር ቢያንስ በዋና ከተማው ውስጥ የሚገኙ ማህበረሰቦች ውስጥ ለመገኘት የሚሞክሩትን ጳጳስ በማስተናገድ እንዲሁም የአምልኮ ሥርዓቶችን በጥንቃቄ በማዘጋጀት የቅዱስ ትሪዱም በዓሉን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።

ከዚያም ቅዱሱ ሌሊት ይደርሳል፥ እሳቱ የቤተሰቡ ምልክት በሆነው ባህላዊ መሠዊያ ውስጥ ይቀጣጠላል። በዙሪያው የሚገኙት ሰዎች በተጨናነቀው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እና ብልጭ ድርግም በሚሉ የከተማዋ መብራቶች ሳቢያ በአብዛኛው ምን እየተካሄደ እንዳለ አያውቁም።

የጌር (የሞንጎሊያ ድንኳን) ቅርጽ ያለው ካቴድራሉ በጨለማ የተሸፈነ ሲሆን፥ በምዕመናኑ መግቢያ ዳር እና ዳር ላይ በመስመር የፋሲካ ሻማዎች እንዲሁም የምእመናን ሻማዎች ይቀመጣሉ። የትንሳኤ ዝማሬዎች በሞንጎሊያኛ ይዘመራል፥ የአካባቢውን ወግ እና ባህል በሚያሳይ ሁኔታ በምስላዊ ግጥሞች ታጅቦ ይዘመራል።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ለሚስጥረ ጥምቀት ሲዘጋጁ የነበሩ ሰዎች ወደ ጥምቀት ቦታው የአዲስ ህይወት ምልክት የሆነውን ነጭ ልብስ ለብሰው ይቀርባሉ። በተለይ ለዝግጅቱ ተብሎ የተሰራውን ዲል (ባህላዊ ልብስ) ለብሰው ይቀርባሉ። ምንም እንኳን የሚታይ ውጫዊ መገለጫዎች ባይኖሩም፥ ጥቂት የስሜት እንባዎችን፣ ብዙ መረጋጋትን እና ብዙ ደስታን ይጋራሉ።
በዚህ መንገድ የሚያሳልፉት የትንሳኤ ቅዱሳን ቀናት በእምነት ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ላሳለፉት እንኳን እውነተኛ በረከት ናቸው። እንዲሁም እምነትህን ለማደስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ትንሳኤ ሊከበር ሳምንት ሲቀረው ሰኞ ዕለት፣ እኛ ሚስዮናውያን ካንድጋይት በሚባል ከኡላንባታር ወጣ ብሎ ባለው ጫካ ውስጥ እንሰበሰባለን፣ እዛ የሐዋርያዊ አስተዳደሩ የሚኖርበት ቤት አለ። በአንድ ከእንጨት በተሰራ አነስተኛ ጸሎት ቤት ውስጥ ቅድመ በዓሉን እናከብራለን።

አንዳንድ ዓመታት በረዶው በብዛት ይወርዳል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የፀደይ ፀሐይ ታበራለች። እያንዳንዳችን በቀደሙት ቀናት ባገኘናቸው ልምምዶች ጥልቅ የሆነ ለውጥ ይሰማናል፥ በጥምቀት ውሃ አማካይነት ወደ አዲስ ህይወት ለመጡት አዲስ የማህበረሰብ አባላት የትንሳኤውን ጌታ እናወድሳለን፣ እናመሰግናለን።

ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበ በኋላ “ያደረግሁላችሁን ታውቃላችሁን?” ሲል ያቀረበው ጥያቄ በጆሮአችንና በልባችን ውስጥ አለ። (የዮሐ. ወ. 13፡12)
በፍፁም ሙሉ በሙሉ አንረዳውም፣ ነገር ግን እነዚህ የትንሳኤ ቀናት ኢየሱስ የጠየቃቸውን ጥያቄ በትክክል እንድንረዳ ያግዙናል፥ ሁልጊዜ ወደ እምነታችን ትክክለኛ ገጽታ እንድንመለስ ይረዱናል። እናም ያ በኤማሁስ ደቀ መዛሙርት ልብ ውስጥ የተቀጣጠለውን እሳት እንደገና በእኛ ውስጥ እንዲቀጣጠል ይረዱናል፥ አሁን በደስታ ወደ ዓለም ለማምራት ዝግጁ ናቸው፥ ታሪክን የለወጠውን አዋጅ እየጠበቁ ነው።
 

01 April 2024, 16:30