ፈልግ

ክርስቲያናዊ ጋብቻ ክርስቲያናዊ ጋብቻ  

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ፤ አካልን ለይቶ ማወቅ

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ ብዙውን ጊዜ ከአገባቡ ውጭ ወይም ጠቅለል ባለ መልኩ የሚተረጎመውንና ማኅበራዊ የሆነውን ቀጥታ ትርጉሙን ችላ ወደ ማለት የሚያደርሰውን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በአትኩሮት ብንመለከት መልካም ነው። እዚህ ላይ ለመናገር የምፈልገው፣ ቅዱስ ጳውሎስ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስላጋጠመው አሳፋሪ ሁኔታ በ1 ቆሮ. 11፡ 17 ላይ ስላነሣው ጉዳይ ነው። ሀብታም የማኅበረሰቡ አባላት ድሆችን የማግለል አዝማሚያ ያሳዩና ይህም ሁኔታ ከቁርባን ሥነ-ሥርዓት ጋር ወደሚካሄደው  የጌታ እራት መታሰቢያ ጭምር ይዘልቅ ነበር።  ሀብታሞች ምግባቸውን ሲበሉ፣ ድሆች ግን እየተራቡ የሚበሉ ሰዎች ተመልካች ሆኑ።  ስለሆነም ቅዱስ ጳውሎስ “አንዱ እየተራበ ሌላው ይሰክራል። ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በመናቅ፣ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን?” ይላል።

መሥዋዕተ ቅዳሴ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን አካል አባላት እንድንሆን ይጠይቃል። ስለዚህ የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚቀበሉ በአባላቱ መካከል አሳፋሪ ልዩነቶችንና ክፍፍሎችን በመፍጠር ያንን አካል ማቁሰል የለባቸውም። የጌታን ሥጋ “ለይቶ ማወቅ” ፣ እርሱንም በምሥጢራት ምልክቶችና በማኅበረሰቡ ውስጥ በእምነትና በፍቅር መመስከር ማለት ትርጉሙ ይህ ነው። ይህን የማያደርጉ በራሳቸው ላይ ፍርድ የሚያመጣባቸውን ይበላሉ፣ ይጠጣሉ (1ኛ ቆሮ. 11፡ 29)። ስለዚህ፣ መሥዋዕተ ቅዳሴ ማንኛውም ሰው “ራሱን ወይም ራስዋን እንዲመረምር ወይም እንድትመረምር” ፣ የቤተሰብ በሮችን ከድሆች ጋር የበለጠ ወዳጅነት ለመመሥረት ስለ መክፈትና በዚህም አኳኋን አንድ አካል የሚያደርገንን የዚያን ቁርባናዊ ፍቅር ምሥጢር ስለ መቀበል የቀረበ የዘወትር ጥሪ ነው። “የምሥጢሩ ‘መንፈሳዊነት’ ማኅበራዊ ባሕርይ እንዳለው” መዘንጋት የለብንም። ሰዎች ይህን ምሥጢር ሲቀበሉ ለድሆች ሥቃይ ትኩረት የማይሰጡ ወይም የተለያዩ የመለያየት፣ የንቀትና የመበላለጥ ዓይነቶችን የሚደግፉ ከሆነ፣ ቁርባንን የሚቀበሉት ሳይገባቸው ነው። በአንጻሩ፣ በሚገባ የተዘጋጁና ቁርባንን አዘውትረው የሚቀበሉ ቤተሰቦች ለወንድማማችነትና ለእህትማማችነት ያላቸውን ምኞት ፣ ማኅበራዊ ንቃተ ኅሊናቸውንና ለችግረኞች ያላቸውን ዝግጁነት ያጠነክራሉ።

ሕይወት በሰፊ ቤተሰብ ውስጥ

ትንሹ ቤተሰብ በወላጆች፣ በአክስቶችና በአጎቶች፣ በአጎት ልጆችና በጎረቤቶች ጭምር ከተገነባ ሰፊ ቤተሰብ ጋር መስተጋብር መፍጠር ያስፈልገዋል። ይህ ሰፋ ያለ ቤተሰብ እርዳታ ወይም ቢያንስ ቅርርብና ክብካቤ ወይም በመከራቸው መሃል ማጽናናትን የሚሹ አባላት ያሉት ሊሆን ይችላል። ዛሬ ተንሰራፍቶ የሚታየው ግለኝነት ሌሎች ሰዎች እንደ አሳሳቢ ወይም እንደ ስጋት የሚታዩባቸውን ትናንሽ የደህንነት መረቦች  ወደ መፍጠር ሊያመራ ይችላል። ይህን የመለሰ የማግለል ሁኔታ የተሻለ ሰላምን ወይም ደስታን በማምጣት ፈንታ የቤተሰብን ልብ አጣብቂኝ ውስጥ ሊከትና ሕይወቱን በሙሉ ይበልጥ ጠባብ ሊያደርገው ይችላል።

ወንድና ሴት ልጆች ስለ መሆን

1ኛ ስለ ወላጆቻችን እናስብ። ኢየሱስ ወላጆችን መተው የወንጌልን ሕግ መጻረር እንደ ሆነ ለፈሪሳዊያን ነገራቸው (ማር. 7፡ 8-13)። እያንዳንዳችን ወንድ ወይም ሴት ልጅ መሆናችንን በሚገባ እናስታውሳለን። “አንድ ሰው ጎልማሳ ወይም አረጋዊ፣ ወላጅ ወይም ባለሥልጣን ቢሆን እንኳ፣ ከዚህ ሁሉ ሥር የልጅ ማንነት አሁንም አለ። ሁላችን ወንድ ወይም ሴት ልጆች ነን። ይህም ሁልጊዜ ሕይወትን ተቀበልነው እንጂ  ለራሳችን አልሰጠነውም ወደሚለው እውነታ ይመልሰናል። ታላቁ የሕይወት ስጦታ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው የመጀመሪያው ስጦታ ነው”።

ስለዚህ፣ “አራተኛው ትእዛዝ ልጆች… አባታቸውንና እናታቸውን እንዲያከብሩ ያዛል (ዘፀ. 20፡12)፡፡ ይህ ትእዛዝ የመጣው ራሱን እግዚአብሔርን ከሚመለከቱ ትእዛዛት ቀጥሎ ነው። በእርግጥ ይህ ትእዛዝ የተቀደሰ፣ መለኮታዊ፣ ለሌላ ሰብዓዊ ክብር ሁሉ መሠረት የሆነ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጸው አራተኛው ትእዛዝ ‘እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም’ በማለት ይቀጥላል። በትውልዶች መካከል ያለው መልካም ትስስር ለወደፊት ዋስትና ነው፤ ለእውነተኛ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ዋስትና ነው። ወላጆችን የማያከብሩ ልጆች ያሉት ኅብረተሰብ ክብር የሌለው ኅብረተሰብ ነው። …. የወደፊት ዕጣ ፈንታው በአኩራፊና በስግብግብ ወጣቶች የተሞላ ኅብረተሰብ መሆን ነው”።

ይሁን እንጂ፣ ሌላም የሳንቲም ገጽታ አለ። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚነግረን፡- “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል” (ዘፍጥ. 2፡ 24)፡፡ ይህ ሁልጊዜ አይፈጸምም፤ ጋብቻም ይህን አስፈላጊ መሥዋዕትነት ባለመክፈልና ራስን አሳልፎ ባለመስጠት ምክንያት ሊደናቀፍ ይችላል። ወላጆችን ብቻቸውን መተው ወይም ችላ ማለት አይገባም፤ ነገር ግን አዲሱ ቤት እውነተኛ ማሞቂያ ምድጃ፣ የደህንነት፣ የተስፋና የወደፊት ዕቅድ ማስፈጸሚያ እንዲሁም ባልና ሚስት ሁለቱም “አንድ ሥጋ” የሚሆኑበት ሥፍራ ይሆን ዘንድ ወላጆችን “መተውን” ጋብቻ ራሱ ይጠይቃል። በአንዳንድ ትዳሮች ውስጥ አንዱ የትዳር አጋር ከሌላው ምሥጢሩን ደብቆ ለወላጆቹ ይናገራል። ከዚህም የተነሣ የወላጆቻቸው አስተያየት ከትዳር አጋራቸው ስሜትና አስተያየት የበለጠ ዋጋ ያለው ይሆናል። ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ አይዘልቅም፤ ጊዜ ቢወስድ እንኳ ሁለቱም ባልና ሚስት በመተማመንና በመግባባት ለማደግ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።ጋብቻ ባሎችና ሚስቶች ወንድና ሴት ልጆች የሚሆኑባቸውን አዳዲስ መንገዶች እንዲቀይሱ ይጠይቃል።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 185-190 ላይ የተወሰደመሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

አዘጋጅ፥ ክቡር አባ ዳንኤል ኃይለ

 

06 April 2024, 08:05