ፈልግ

የታንዛኒያ ከተማ በሆነችው ሞሮጎሮ የሚገኙ የቅዱስ ቪንሰንት ማህበር የክህነት ተማሪዎች የታንዛኒያ ከተማ በሆነችው ሞሮጎሮ የሚገኙ የቅዱስ ቪንሰንት ማህበር የክህነት ተማሪዎች 

ታንዛኒያ የሚገኙ የቅዱስ ቪንሴንት ተማሪዎች ምቹ ቦታ ባይኖራቸውም ‘ለእግዚአብሔር ግን ቦታ ሰጥተዋል'

ታንዛኒያ ውስጥ በምትገኘው ሞሮጎሮ ከተማ የሚገኙ የክህነት ተማሪዎች የቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖልን ርኅራኄ እና ልግስና ፈለግ በመከተል የእምነት ጉዟቸውን ለማጠናቀቅ ያላቸውን ነገር ሁሉ ይጠቀማሉ። (የቫቲካን ዜና ጋዜጠኛ የክህነት ትምህርት ቤቱን ጎብኝታ የፃፈችውን እንደሚከተለው እናቀርባለን)

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የመጀመሪያዎቹ የቅዱስ ቪንሴንት ማህበር ሚስዮናውያን እ.አ.አ. በ1993 ወደ ታንዛኒያ የገቡ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተልዕኮቻቸውን ያለማቋረጥ ከጊዜ ወደጊዜ እያሳደጉት አሁን ላይ ደርሰዋል። “የጌታን ቃል ማወጅ” የሃይማኖታዊ ሥርዓት አንዱ መስዋዕትነት ነው፥ በታንዛኒያ የሚገኙት የዚህ ማህበር አባላት ይህንን በትክክል እያደረጉት ይገኛሉ።

ከዳሬሰላም ወደ ሞሮጎሮ የአምስት ሰዓት ጉዞ ስንጓዝ ምን እንደሚጠብቀን እርግጠኛ አልነበርንም። በመጨረሻ ወደ ቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖል የክህነት ት/ቤት ቅጥር ጊቢ ስንደርስ 41 ተማሪዎች የመኪና ማቆሚያው ቦታ ላይ በፈገግታ ተሞልተው እየዘመሩ ሲቀበሉን ያልጠበቅነው ነገር ነበር። 

“መምጣታችሁ ለሁላችን በረከት ነው” ብለው ይዘምሩ ነበር፥ ያዘጋጁትን የአበባ ጉንጉን አንገቶቻችን ላይ አስገብተው እየዘመሩ ወደ መመገቢያ አዳራሻቸው ካስገቡን በኋላ አብረን ምግብ በልተናል።

ችግር ሊኖር እንደሚችል ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋልነው ተማሪዎቹ በትናንሽ ጠረጴዛዎቻቸው ዙሪያ ተጨናንቀው ሲቀመጡ ባየን ጊዜ ነው። እኛ የምንበላበት ጠረጴዛ እንዲኖረን እነሱ በማይመች ሁኔታ ተጨናንቀው ነበር የተቀመጡት። በመመገቢያ አዳራሹ ውስጥ ለሁሉም ሰው የሚሆን በቂ ቦታ አልነበረም።

ጨለማም ቢሆን፥ ከእራት በኋላ በጊቢው ውስጥ ፈጣን የእግር ጉዞ ስናደርግ በደማቅ ቀለም የተቀቡት ግድግዳዎቹ በደስታ እና አዝናኝ በሆነ ሁኔታ ልክ ተማሪዎቹ እንደተቀበሉን በስዋሂሊ “ካሪቡ” ብለው ነበር የተቀበሉን።

ተማሪዎቹ በመዝናኛ ክፍል ውስጥ የታንዛኒያ ፕሪሚየር ሊግን ለመመልከት ሁሉም ተሰብስበው ነበር። የሲምባ ክለብ ከ'ሲንጊታ ፋውንቴን ጌት' ጋር ነበር የሚጫወቱት። እድለኛ የሆኑት መቀመጫ አግኝተዋል፥ ሌሎቹ ግን ቆመው ነበር የሚከታተሉት።

በመተላለፊያ መንገዱ በኩል አርገን ወደ ቤተመቅደሱ ስንደርስ እያንዳንዱ ተማሪ በተመደበለት በተማሪዎች መጽሐፍት እና እስክብሪቶ ታጭቆ ወደ ነበረው አግዳሚ ወንበር ሄዶ ሲቀመጥ፥ መጨረሻ የሚደርስ ሰው ከኋላ በኩል ካሉት ወንበሮች ይቀመጣል። የቦታ እጥረት እንዳለ የሚያውቁት የተማሪዎቹ አለቃ የሆኑት አባ ሙሺ “ሁሉንም ሰው ለማስቀመጥ ወንበሮቹ በቂ አይደሉም” በማለት በቤተ መቅደሱ ግርጌ ያሉትን ወንበሮች አመለከቱን። በመቀጠልም “እነዚህ ቦታዎች ሞልተዋል፥ አዲስ ሰው ከመጣ ግን የምናስተናግድበት ቦታ አይኖረንም” አሉ።

“በእውነቱ” ይላሉ በታንዛኒያ የሚገኘው የቅዱስ ቪንሴንት ማህበር የክልል የበላይ አለቃ የሆኑት አባ ዩዳ፥ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጉባኤው አባል ለመሆን የሚፈልጉ ብዙ ሰዎችን መቀበል አልቻልንም፥ በሃዋሪያዊ ሥራ ላይ ችግር የለብንም፥ ነገር ግን የአቅም ችግር አለብን” ሲሉ አስረድተዋል።

ተማሪዎቹ ቀድሞውንም ክፍሎቹን ይጋራሉ፥ አብዛኛዎቹ አንድ ክፍል ውስጥ ለሁለት ይኖራሉ፥ ሌሎቹ ደግሞ አራት ሆነው አንድ ክፍል ይጋራሉ። በትህትና መኖርን እና ብዙ አለመፈለግን ከመስራች አባታቸው የቅዱስ ቪንሴንት ፈለግ በመከተል ጥሩ ቤተሰብን እና እውነተኛ ማህበረሰብን ፈጥረዋል።

ምንም እንኳን እነዚህ ወጣቶች እምብዛም ለምቾት ቦታ ባይኖራቸውም፥ ተጨማሪ ነገሮች ግን እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው። በዝናባማ ወቅት ብስክሌቶቻቸው ጭቃማውን መንገድ አሻግሮ ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ሊወስዷቸው አይችሉም፥ በደረቁ ወቅት ደግሞ የውሃ እጦት የአትክልታቸው ማሳ ምድረ በዳ ያስመስላሉ። ዶሮዎቻቸው እና ዳክዬዎቻቸው ለልዩ እንግዶች ብቻ የሚሆኑ ናቸው። ምክንያቱም ደግሞ ይላሉ አባ ሙሺ “ለእነዚህ ልጆች እንስጥ ብንል በግማሽ ቀን ውስጥ ያጠፏቸዋል!” በማለት አዋዝተው ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ የማብሰያ ዘይታቸውን ለማዘጋጀት በአትክልቱ ውስጥ ያሉትን የደረቁ የሱፍ አበቦችን እየቀጠቀጡ ዘሩን ለማውጣት ደፋ ቀና ይላሉ። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች አቅማቸው በሚፈቅድላቸው መጠን እራሳቸውን ለመቻል ጥረት እንደሚያደርጉ ግልፅ ነው።

የሶስተኛ ዓመት የፍልስፍና ተማሪ የሆነው ሃምፍሬይ በፈገግታ ተቀብሎን ስለ እምነት ጉዞው እና ድሆችን ለመርዳት በትህትና ለመሰጠት ስላለው ፍላጎት እያፈረም ቢሆን በሙሉ ልብ ነግሮናል። ሃምፍሬይ ዓለማዊውን መንገድ በመተው የቅዱስ ቪንሴንት ደ ፖልን ፈለግ በመከተሉ የትህትና ጥሩ ተምሳሌት ሆኗል። ሁሉም ተማሪዎች እንደዚሁ ናቸው።

ክፍሎቻቸውንም ጎብኝተናል፥ በግድግዳዎቻቸው ላይ ያሉትን ፖስተሮች እና መጽሃፎቻቸውን አይተናል። አርባ አንዱ ተማሪዎች ስምንት ኮምፒውተሮችን እና አንድ ፕሪንተር በጋራ ይጋራሉ፥ ሁሉም ተማሪዎች ስለሆኑ ወደ ከተማ ሄደው ለህትመት የሚሆን ገንዘብ መክፈል ስለማይችሉ አንድ ፕሪንተር አዘጋጅተንላቸዋል ብለዋል የተማሪዎቹ አለቃ የሆኑት ካህን።

በመሆኑም አለቃቸው በሆኑት ካህን በመመራት፣ ካህኑ ደግሞ በክልሉ የበላይ በሆኑ መሪ በመመራት፣ ተማሪዎቹም አንዱ ሌላውን በመንከባከብ ሁሉም ነገር የሚቻል እንዲመስል ሁሉንም ነገር አብቃቅተው እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ በግልጽ ይታያል።

ከዚያም ያለንን ቆይታ ጨርሰን የመሰነባበቻ ጊዜው ስለደረሰ ተማሪዎቹ ወደ አንድ ወንበሮቹ ወደ ጥግ ወደ ተሰበሰቡ ክፍል አንድ በአንድ መግባት ጀመሩ፥ ሁሉም ባህላዊ ልብሶቻቸውን ለብሰዋል፥ ከደማቅ ፈገግታ ጋር ባህላዊ ዘፈን እየዘፈኑ እና እየተወዛወዙ ደማቅ አሸኛኘት አድርገውልናል።

ተማሪዎቹ ለእኛ እንዲህ በማድረጋቸው ደስተኞች ናቸው። እኛም ይሄንን በማየታችን በጣም ተዝናንተናል። በቅርቡ ከተሾሙት ዲያቆናት አንዱ የምስጋና ንግግር አደረገልን፥ ቡድኑ በሌላ ጎራ ፍጹም ማራኪ የሆነ የመቁጠሪያ ጸሎት መርሃ ግብር በማዘጋጀት ሁለት ውብ ባህሎችን ወደ አንድ ጠንካራ ጥሪ አዋህደዋል።

ቤተ ክርስቲያን፣ ታንዛኒያ እና መላው ዓለም እንደነዚህ አይነት ብዙ የዘርአ ክህነት ተማሪዎች ያስፈልጋቸዋል፥ እነዚህ ወጣት ወንዶች ደግሞ ወደፊት ድንቅ መሪዎች እንዲሆኑ የሚኖሩበት እና የሚማሩበት ቦታ ይገባቸዋል።
 

18 March 2024, 16:06