ፈልግ

2022.05.09 Oberammergau Passionsspiele 2022

የመጋቢት 15/2016 ዓ.ም ሰንበት ዘምኩራብ ዕለተ ሰንበት መልዕክቶች እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የእለቱ ንባባት

1.    ቆላ 2፥16-23

2.    ያዕ 2፥14-26

3.    ሐ.ሥ. 10፥1-8

4.    ዮሐ 2፥12-25

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጠራ

ከዚህ በኋላ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀን ተቀመጡ። የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በቤተ መቅደሱ አደባባይ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምንዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ። የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አባረረ፤ የመንዛሪዎችን ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዞቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው።

ደቀ መዛሙርቱም፣ “ለቤትህ ያለኝ ቅናት ያቃጥለኛል” ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው። አይሁድም፣ “ይህን ሁሉ ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ታምራዊ ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቷል፤ ታዲያ አንተ እንዴት በሦስት ቀን መልሰህ ታነሣዋለህ?” አሉት። ቤተ መቅደስ ሲል ግን፣ ስለ ገዛ ሰውነቱ መናገሩ ነበር። ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ ያለውንም ቃል አመኑ።

በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ታምራት አይተው በስሙ አመኑ፤ ኢየሱስ ግን ሰውን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ አይታመንባቸውም ነበር፤ በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አላስፈለገውም። (ዮሐ 2፥12-25)

የእለቱ አስተንትኖ

 

“የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላይ ወድቋልና” (መዝ 69፥9)።

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦችና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ደንብ መሰረት ዘሙኩራብ የሚለውን ሰንበት እናከብራለን። ይህ ሦስተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት ምኩራብ ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በእዚሁ እለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በእለት ሰንበት “ቦኦ ኢየሱስ ምኩራብ አይሁድ” (ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ሙኩራብ ገባ) እያለ ኢየሱስ በአይሁድ ሙኩራብ ማስተማሩን እየጠቃቀሰና እያነሣሣ ስለሚዘመር፣ በሙኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ለማስወጣቱ፣ ቤተ መቅደሱን ለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ስለተሰጠ ይህ ሰንበት “ሰንበት ዘ ሙኩራብ” ተብሎ ተጠርቷል። በዚህ ዕለት በተለይም በሦስተኛው የዐብይ ጾም ሰንበት የእግዚአብሔር ቃል ሊያስተምረን የሕይወትን መንገድ ሊያመላክተን በተነበቡት ንባባት አማካኝነት ወደ እያንዳንዳችን መጥቶ የልባችንን በር ያንኳኳል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆላስያስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የአይሁድ ሕግ ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት ይለናል፤ የመጀመሪያው “ሞራላዊ ሕግ” ይህም ዐሥርቱ ትእዛዛትና የመሳሰሉት ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ግን ስለ መሥዋዕት ማቅረብ፣ ስለ መንጻት ሥርዓትና ስለ አይሁድ በዓሎች አከባበርን ያካተተው ሕግ ነው። ይህ ሕግ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደንብና ሥነ ሥርዓቶችን ያካትታል (ማር 7፥1-4 እና ኤፌ 2፥15)።

በቆላስያስ የነበሩ አንዳንድ አማኞች ለእነዚህ ደንቦችና ሥነ ሥርዓቶች እየተገዙ ነበር። ይህን ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህን ደንቦችና ሥነ ሥርዓቶች የማያከብሩ ክርስቲያኖችን ያወግዙ ነበር። እነዚህን ሥነ ሥርዓቶችና ደንቦችን በሚገባ  ካልጠበቁ መዳን የለም ያስተምሩ ነበር።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ስህተት የሚያስተምሩትን ሰዎች በፍጹም አትስሟቸው ይላል። ምክንያቱም ሰው የሚድነው በጸጋ አማካይነት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ባስተማረውና በኖረው ሕይወት ውስጥ በመሳተፍ ብቻ ነው ይለናል። “መንገዱ እኔ ነኝ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” (ዮሐ 14፥6)  ይለናል።

ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በዛሬው መልእክቱ ስለ እምነትና ሥራ ይናገራል ይህም “ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን?” (ያዕቆብ 2፡14) ብሎ በጥያቄ ይጀምራል።

አምናለሁ ማለት ቀላል ነገር ነው፤ ነገር ግን እንዲህ ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም ወይም ትርጉም አይሰጥም። ምክንያቱም እምነታችን እውነተኛ ስለመሆኑ እራሳችንን በየዕለቱ መጠየቅ ይኖርብናል። እምነታችን እውነተኛ ይሁን ወይም ሐሰተኛ፤ ጠንካራ ይሁን ደካማ በምን ልናውቅ እንችላለን? ይህ የሚታወቀው በሥራችን ነው። ይህም የፍቅር ሥራችን፣ የመታዘዝ ተግባራችን የእምነታችን ማረጋገጫ ነው። እምነታችንን የሚገልጽ ሥራ ከሌለን እንዲህ ያለው እምነት አያድነንም ወይም እርሱ ለሰጠን ክብር አያበቃንም።

ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ በ 2፡15-16 ስለ ሐሰተኛ እምነት ሲናገር ይህ በቃላት ብቻ እንጂ በሥራ እንደማይገለጽ ፍቅር ነው ይለናል። ለተቸገሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደምንወዳቸው እየተናገርን በችግሮቻቸው የማንረዳቸው እና የማንደርስላቸው ከሆንን እምነታችን ሐሰተኛ እና ጥቅም የለሽ ነው። “ማንም ሀብት እያለው ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል? ልጆች ሆይ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ”  (1ዮሐ 3፥17-18) በማለት የያዕቆብን መልእክት ያጠናክርልናል። እንዲህ ዓይነቱ እምነት ማንንም አይጠቅምም፤ በተመሳሳይ መልኩ እምነታችን በሥራ ካልተገለጸ ዋጋ የለውም።

እውነተኛ እምነት ሁል ጊዜ በሥራ የሚገለጽ ነው፤ ሥራ ሁል ጊዜ ከእምነት ጋር የሚሄድ ነው፤ ያለሥራ የሚገለጽ እውነተኛ እምነት የለም፣ ይህም እምነት ወደ ፍቅርና መልካም ሥራ ይመራናል።

መልካም ሥራ ሁል ጊዜ ከመታዘዝና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመውደድ ጋር የተገናኘ ነው፣ ይህንንም  “ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ” (ዮሐ 14፥15) በማለት ያሳስበናል። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ እኛ እንድናደርግ የሚፈልገው ነገር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ እንድንፈጽም ዘንድ ነው። ይህም ትእዛዝ  “ትእዛዜ ይህች ናት፣ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” (ዮሐ 15፥12) እንደተገለጸው የሚል ነው። ስለዚህ እውነተኛ እምነት እራሱን የሚገልጸው በፍቅር ነው፤ ምክንያቱም አንድ ሰው እራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሌላውንም ሰው ቢወድ እና መውደዱንም ቢያሳይ ይህ ሰው እውነተኛ እምነት እንዳለው ማሳያ ምልክት ነው።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! በዛሬው እለት ሲነበብ በሰማነው ቅዱስ ወንጌል (ዮሐ. 2: 13-25) ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በቤተመቅደስ ውስጥ ሆነው ይገበያዩ የነበሩ ነጋዴዎችን ከቤተመቅደስ እንዲወጡ ያደረገበትን ትዕይንት ያሳየናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሻጮችን ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በማስወጣት፣ ገንዘባቸውንም በመበተን እና ጠረጴዛዎቻቸውንም  በመገለባበጥ እንዲህ ሲል ገሰጻቸው፥ ‘የአባቴን ቤት የንግድ ቤተ አታድርጉት’ አላቸው (ዮሐ. 2:16)። በቤት እና በገበያ መካከል ባለው ልዩነት ላይ እናተኩር። በእርግጥ እነዚህ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብባቸው ሁለት የተለያዩ መንገዶች ናቸው።

ቤተ መቅደስን እንደ ገበያ ሥፍራነት ስንመለከተው አንድ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ትክክል ለመሆን በቤተ መቅደስ ውስጥ የበግ ጠቦትን ገዝቶ በመሠዊያው እሳት ከጠበሰው በኋላ መብላት ነበረበት። ከዚያም በኋላ ሁሉም ሰው ወደ ቤቱ ይሄዳል። በዚህ ሁኔታ ቤተመቅደስ እንደ ቤት ይቆጠራል። በሌላ በኩል በተቃራኒው ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ ወደ እሱ፣ ወደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለመቅረብ፣ ደስታን እና ሐዘንን ለመካፈል ወደ ቤተመቅደስ እንሄዳለን። ከዚህም በላይ ሁሉም ሰው ወደ ገበያ ሲሄድ ስለሚገዛው ነገር ዋጋ ይደራደራል። በቤት ውስጥ ግን ለሚደረግለት መስተንግዶ ምን ያህል ልክፈል ብሎ ማንም አያስብም። ነገር ግን አንድ ሰው ወደ ገበያ ሲሄድ የራሱን ፍላጎት ወይም ትርፍ ይፈልጋል። በቤት ውስጥ ግን ሁሉንም ነገር በነጻ ያገኛል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ሻጮችን ከቤተ መቅደሱ እንዲወጥ ያደረገበት፣ ጠረጴዛዎቻቸውን ገለባብጦ ገንዘባቸውን የበተነባቸው፥ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚቀርቡበት ቤተ መቅደስ ወደ ገበያ ማዕከልነት እንዲለወጥ ባለመፈለጉ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲበላሽ ወይም እንዲቋረጥ አይፈልግልም። የጠበቀ እና እምነት የተጣለበት እንጂ የራቀ እና ከንግድ ጋር የተያያዘ እንዲሆን ኢየሱስ አይፈልግም። የቤተሰብ ገበታን የዕቃ መሸጫ ቦታ እንዲሆን፣ የዋጋ ድርድሮች የወዳጅነት ስሜትን፣ ሳንቲሞችም የሰዎችን መቀራረብ እንዲተኩ ኢየሱስ አፈልግም። ኢየሱስ ይህን የማይፈልገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር እና በሰዎች መካከል ኅብረትን፣ ምሕረትን እና መቀራረብን ለማምጣት የመጣ በመሆኑ በወንድሞች መካከል ልዩነትን እንዲፈጠር አይፈልግም።

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የዐብይ ፆም ወቅትን ጨምሮ በራሳችን እና በአካባቢያችን ውስጥ ከገበያ ሥፍራነት ይልቅ የላቀ የቤተሰብነት ስሜት መገንባት እንደሚገባን ከሁሉ አስቀድሞ እንደ ስግብግቦች እና እምነት እንደሌላቸው ነጋዴዎች ሳንሆን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ አብዝተን እንድንጸልይ፣ ወደ ደጁ በልበ ሙሉነት ቀርበን ሳንሰለች በሩን እንድናንኳኳ ይጋብዘናል። ስለዚህ በቅድሚያ በጸሎት ከዚያም ወንድማማችነት ከምን ጊዜውም የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ወንድማማችነትን ማስፋፋት ይኖርብናል።

ስለዚህ በቅድሚያ ጸሎታችን ምን ይመስላል? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። ጸሎታችን እንደ አንድ ዕቃ ዋጋ የተተመነነው ወይስ ጊዜን ሳንሰጥ በብቸንነት ወቅት የእግዚአብሔርን ዕገዛ የምንለምንበት ነው? ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ምን ይመስላል? ከሰዎች ምንም ሳልጠብቅ መልካም ነገርን ላደርግላቸው እችላለሁን? ዝምታን እና ልዩነትን ለማስወገድ በቅድሚያ እርምጃን መውሰድ እችላለሁ? እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

በመካከላችን እና በዙሪያችን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የምንሆንበትን መሠረት ለመገንባት የሚያስችለንን ኃይል በመስጠት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን።

 

23 March 2024, 14:30