ፈልግ

2023.03.27 via crucis

የፍኖተ መስቀል ሦስተኛ ምዕራፍ

መድኃኒታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮን ሲሄድ ሳለ ለጀመሪያ ጊዜ ከመስቀሉ ጋር እንደወደቀ ያሳስበናል፡፡ ኢየሱስ ሞት ከተፈረደበት በኋላ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ አመራ፡፡ በቀደመው ስቃይና ግርፋት ደክሞ ስለነበር ከባድ መስቀል ተሸክሞ ሲሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከከባድ ሸክሙ የተነሳ በመንገድ ላይ ወደቀ፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

አይሁዳውያን በርኀራኄ መንፈስ ተመልክተው እንዲነሳ መርዳት ሲገባቸው በስድብ፣ በድብደባና በበትር በመምታት እንዲነሳ አስገደዱት፡፡ ጌተችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እነርሱን ፍራቻ ሳይሆን በመስቀልና በደኀንነታችን ተገዶ ብድግ ብሎ ተነሳ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት የከበደውና ያደከመው በመንገድ የጣለው የመስቀሉ ክብደት ብቻ ሳይሆን በአንጻሩ የኃጢአታችንን ክብደት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለፈውንና የሚመጣውን ሥፍራ ቁጥር የሌለውን የሁላችንም የአዳም ልጆች ኃጢአት በማስታወስ ነው፡፡ የሁላችንም የአዳም ልጆች ኃጢአት ብዛት እንደ አንድ ትልቅና በጣም ከባድ የድንጋይ ቋጥኝ ተጫነው በክብደቱም ብርታት መራራ ሐዘን ተሰማው፡፡

ኃጢያት ስናደርግ ኢየሱስን እናሰቃየዋለን እናዋርደዋለን፣ እንደገና በመስቀል እንሰቅለዋለን፣ በኃጢአታችን ከባድ ሸክም ክፋኛ እንጥለዋለን፣ አምርረን እንበድለዋለን፣ ከጣልነው በኋላ ራርተን ማንሳትና መርዳት ሲገባን በዚህ ፈንታ እንደ አይሁዳውያን እንጨክንበታለን፣ በደል አብዝተን እየጨመርን መውደቁንና መቁሰሉን እናባብስበታለን፣ በዚሁ አኳኋን እንደ ባዕድና ባይተዋር አድርገን እንመለከተዋለንም፡፡ የሰው ልጅ ጭካኔ ገጽታ እንደ መስተዋት በመስቀል ልንመለከተው እንችላለን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአታችን ከብደት ምክንያት ከወደቀ በኋላ አባቱ እግዚአብሔር አብ የወሰነለትን የመከራና የስቃይ ጉዞ ይፈጽም ዘንድ ብድግ አለ፡፡ መስቀሉን ተሸክሞ የስቃይና የመከራ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ እኛ በዚህ ዓለም ስንመላለስ ብዙ ጊዜ በኃጢአት ላይ እንወድቃለን፣ በገዛ ራሳችንም ነፍሳችንን እንጐዳለን፡፡ እግዚያአብሔር ግን ከኃጢአታችን እንድንፈወስና በምስጢረ ንስሐ አማካይነት ተጸጽተን ወደ እርሱ እንድንመለስ ይጠራናል፣ በናፍቆት ይጠብቀናል፡፡ እኛ ግን ጥሪውን ሰምተንና ተረድተን በፍጥነት መነሳት ሲገባን በሞኝነትና በግድየለሽነት በኃጢአት ውድቀት እንዘገያለን፣ አለአንዳች ፍራቻና ስጋት በኃጢአት አልጋ ላይ እንጋደማለን፡፡ ኃጢአት ማድረግ ከሰለቸን በኋላ ቀስ ብለን እንነሳለን፡፡ ብዙ ጊዜ ኃጢአት ከማድረግ ስንቆጠብና ስንጠነቀቅ በእግዚአብሔር ፍቅርና በነፍሳችን ጥቅም ተገፋፍተን መነሳት ሲገባን የእግዚአብሔር ቅጣትና መቅሰፍት በላያችን ላይ እንዳይወርድ በመፍራት እንውተረተራለን፡፡ኃጢአታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ ከባድ ሸክም ነው፡፡ ይህን እያወቅን እንዴት ብለን ኃጢአትን ለማድረግ እንደፍራለን? በኃጢአት ላይ ወድቀን ሳንነሳ እንዴት ልንቀር እንችላለን? በጣም እንሳሳታለን፡፡ በዚህ ምከንያት ከእንግዲህ ወዲህ ኃጢአትን እንዳናደርግ ቁረጥ ፍቃድ እናድርግ፡፡ ምናልባትም ያደረግነው ቁርጥ ፈቃድ አፍርሰንና ጥሰን እንደሆን ሳንዘገይ ቶሎ ብለን በፍጥነት እንድንጸጸትና ንስሐ እንድንገባ ይሁን፡፡ ከዚህ አስከፊ የኃጢያት ውድቀት በፍጥነት ብድግ እንበል፣ ወደ እግዚአብሔር ጸጋና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንመለስ ወደ እመቤታችንም እንማጸን፡፡

22 March 2024, 13:26