ፈልግ

በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ   (REUTERS)

ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስቸኳይ እንደሆነ ገለጹ

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ ሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ከምንጊዜውም በላይ አስቸኳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ፓትርያርክ ፒዛባላ ለቫቲካን የዜና ወኪል እንደተናገሩት፥ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊኖር እንደሚችል አጽንኦት ሰጥተው እንደ ነበር እና እውን ለማድረግ የጎደለው ፍላጎት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። ፓትርያርኩ በቃለ መጠይቃቸው ወቅት የጋዛ ክርስቲያኖች የአቅመ ደካማነት ሁኔታ እና ቤተ ክርስቲያን በሰላም ድርድር ውስጥ ልትጫወት የሚችለውን ሚና ጠቅሰዋል።

በጋዛ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ጦርነት እንዲቆም ስንጠይቅ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ያሉት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ከሌሎች በርካታ የሃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን ጥሪ ማድረጋቸውን እና ከመካከላቸውም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንባር ቀደም እንደሆኑ ገልጸዋል። የቅርብ ጊዜ ጥሪያችን ጋዛ ውስጥ ከሚገኙት ሕዝባችን መካከል ስለምንገናኝ እና ሁኔታው በየቀኑ ​​ምን ያህል የበለጠ አስከፊ እየሆነ እንደመጣ ስለምናውቅ ነው ብለዋል።

ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ነጥቦች አልጥፉም ያሉት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥  የጠፋው ፍላጎት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። ተኩስ ለማቆም ሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ ለመድረስ ፈቃደኝነታቸውን እንዲያሳዩ እንደሚጠይቅ ተናግረው፥ በሁለቱም በኩል ድርድር መደረግ እንዳለበት ግልጽ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በቅርቡ ከጋዛ የተሰማ ዜና ዓለምን ያናወጠ እና እንደማንኛውም ሰው በጣም ያዘኑበት እንደሆነ ገልጸው፥ በመላው የጋዛ ሰርጥ ያለው ትርምስ እና በተለይም በሰሜናዊ ክፍል የተስፋፋው ረሃብ የሚያሳዝን መሆኑን አስረድተዋል።

ምስሎች እንደሚያሳዩት ምግብ እና ጋዝ ወደ ጋዛ ሰርጥ ማድረስ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ በግሌ አውቃለሁ ያሉት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ ለምሳሌ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም ቢበዛ ሁለት ጊዜ ብቻ ምግብ እንደሚያበስሉ፥ አንድ ጊዜ የሚያበስሉት ምግብ ሳምንት የሚያቆያቸው መሆን እንዳለበት ገልጸው፥ ይህ የሚያሳየው ያለንበትን ሁኔታ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የውሃ እጥረት መኖሩን የገለጹት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ የሚገኘውም ንጹህ ካለመሆኑ የተነሳ ለበሽታዎች እንደሚዳርግ ገልጸዋል። መድሃኒቶችም እንደሚጎድሉ እና በተግባር ሁሉም ነገር በመጥፋቱ በዚህ መንገድ መቀጠል እንደማይቻል ሁሉም የሚገነዘበው ይመስለኛል ብለዋል። ከአየር ላይ የታሸጉ ምግቦች መጣል መጀመራቸውን ቢያዩም ነገር ግን ሌሎች የተቀናጁ ስልታዊ መፍትሄዎች ካልተገኙ ዝም ብሎ ትርምስ ይሆናል ብለዋል።

በበኩላቸው ዘወትር ተስፋ አለ ያሉት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ ይህ ስቃይ እንዲቆም ሁል ጊዜ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፥ በተቻለ መጠን ወደ መደበኛው ሕይወት የመመለስ ተስፋ እና እምነት ቢኖርም ፈተናው ብዙ እንደሆነ አስረድተዋል።

የጋዛ ማኅበረሰብ ጸሎት ላይ እንደሚገኝ፣ እምነት እንዳለው እና ከሁሉም በላይ እራሱን ለማደራጀት እና ጎረቤቱን ለመርዳት ሲሞክር ተመልክቻለሁ ብለዋል። አንድን ነገር ለማድረግ፣ ለማስተባበር እና ለመርዳት ፍላጎት እስካለ ድረስ ሁሉም ነገር እንደሚቻል ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያን በዲፕሎማሲያዊ ድርድር ውስጥ ምን ሚና እንዳላት፣ በዚህ ውስብስብ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ ጣልቃ የምትገባበት መንገድ እና ተጽእኖን የምትፈጥርበት አጋጣሚ እንዳለ የተጠየቁት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሚና መጫወት ትችል እንደሆነ አላውቅም ብለው፥ ምክንያቱን ሲገልጹ ጉዳዩ በጣም ሰፊ እና ውስብስብ እንደሆነ በመግለጽ፥ ቤተ ክርስቲያን ፈጣን ሃይል ባይኖራትም ነገር ግን በሁሉም የመገናኛ መንገዶች፣ ከሁሉም አካላት ጋር በመወያየት መግባባትን ለማመቻቸት ጥረት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ምንም ዓይነት አዎንታዊ ነገር ይመጣል ብዬ አላምንም ያሉት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ ነገር ግን በእርግጠኝነት የማውቀው ካለፉት 70-80 ዓመታት እጅግ አሳሳቢ ቀውስ በኋላ እስራኤላውያንም ሆኑ ፍልስጤማውያን ማንም ሰው ጊዜያዊ መፍትሄዎችን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል። ስለዚህ ለአሳሳቢ ቀውሱ ፈጣን ምላሽ ባይገኝለትም አሳሳቢ ቀውሱ ሁሉም ሰው ለእስራኤል እና ፍልስጤም ግጭት የረዥም ጊዜ መፍትሄዎችን እንዲያገኝ ያስገድዳል ብለዋል።

ሁለት-ግዛት የሚል የመፍትሄ ሃሳብ ተግባራዊ ይሆን እንደሆነ አላውቅም ያሉት ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ ምናልባት ሁለት መንግሥታት የሚል ካልሆነም ሌላ መፍትሄ ሊኖር እንደሚችል ገልጸው፥ ምንም እንኳን በተጨባጭ ብቸኛው እና የሚቻል ቢመስልም ሁለት መንግሥታት የሚለውን የመፍትሄ ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ ቀላል እንደማይሆን ገልጸው፥ ነገር ግን ለሁለቱም ማለትም ለፍልስጤማውያን እና ለእስራኤላውያን መረጋጋትን በማምጣት ነፃነታቸውን እና ክብራቸውን የሚያረጋግጡ መፍትሄዎች ሊገኙ እንደሚገባ ግልጽ ነው በማለት ተናግረዋል።

 

05 March 2024, 16:54