ፈልግ

የማይናማር ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት እና የያንጎን ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ የማይናማር ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት እና የያንጎን ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ 

ብጹእ ካርዲናል ቦ በጉዳት ውስጥ ለምትገኘው ዓለማችን በአንድነት ተንበርክከን መጸለይ ይገባል አሉ

የማይናማር ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት የያንጎን ሃገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ በዚህ የተቀደሰ ሳምንት፥ ‘የጦርነት ግርግር እንዲቆም’ ምእመናን በጋራ በመሆን ለሰላም እንዲጸልዩ በማሳሰብ፥ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ውይይት እና እርቅ እንዲደረግ ያቀረቡትን ጥሪ እንዲቀበሉ አበረታተዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በማይናማር የያንጎን ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ ምዕመናን በትጋት አብረው እንዲጸልዩ እና “በዚህ በቆሰለው ዓለም” ውስጥ ለሰላም ተግተው እንዲሰሩ ተማጽነዋል።

የማይናማር ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር ለቫቲካን ዜና በላኩት መልዕክት፥ መጪው እሁድ በምናከብረው የትንሳኤ በዓል ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን የግጭቱን ጨለማ አስወግዶ አዲስ የተስፋ እና የስምምነት ጎህ እንዲያመጣ ተማጽነዋል።

“የሰላም ንጋትን መቀበል” የሚል ርዕስ ያለው የብፁዕ ካርዲናሉ መልዕክት በምድራችን ላይ በተለይም በቅድስት ሀገር ዩክሬን እና በሃገራቸው ማይናማር የተከሰቱትን ጦርነቶች በመጥቀስ፥ የሰው ልጅ በሙሉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን የውይይት እና የእርቅ ጥሪ እንደ የጋራ የሰላም ጥሪያችን መሰረት እንዲቀበል አሳስበዋል።

የማይናማሩ ብጹእ ካርዲናል ስለ ፋሲካ ምስጢር በማብራራት እንዲህ ብለዋል፡- “ዓለም ዛሬ እየተጋፈጠች ባሉት ግጭቶችና ችግሮች ወቅት “ሞትን ድል አድርጎ እውነተኛ ሕይወት በሰጠን በትንሳኤው ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በመታመን ተስፋችንን ማደስ አለብን” ብለዋል።

ይህ ተስፋ “ለሕይወት ብርሃንን ይፈጥራል፣ ተስፋ መቁረጥን ያሸንፋል፣ አንድነትን ያመነጫል” እንዲሁም “የግድየለሽነት እና የመጋጨት ባህል የፈጠሩትን በህብረተሰባችን ውስጥ የሚዘራውን እና ለጦርነትም የሚያዘጋጀውን የግጭት ዘሮችን ሁሉ ይከላከልልናል” ብለዋል።

“ሁሉም በአንድነት” ይላሉ ካርዲናሉ “ዓለም የጦር መሳሪያዎቿን ወደ ሰላም መሳሪያዎች እንድትቀይር እንዲሁም ፍርሃቶች ሁሉ ወደ ማይናወጥ መተማመን እንዲቀየሩ ቃል ይግባ” ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናሉ በመጨረሻም፥ ቃሎቻችን የወንድማማችነትን ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ያስተጋቡ፣ ተግባራችንም ሰላምን በመፈለግ ይመራ” በማለት በጸሎት አጠቃለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ለማይናማር ያላቸው ቅርበት

በ 2009 ዓ.ም. ማይናማርን እና ባንግላዲሽን የጎበኙት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሮሂንጊያ ስደተኞችን ስቃይ በመቃወም ደጋግመው ድምጻቸውን አሰምተው ነበር።

ከ 1974 ዓ.ም. ጀምሮ በማይናማር አገር አልባ ያደረጋቸውን ዜግነታቸውን የተነፈጉት ሮሂንጊያዎች፥ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ስደት ከደረሰባቸው አናሳ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ እንደሆኑ ሲገለጽ፥ ለብዙ አስርት ዓመታትም በየብስ ወይም በጀልባ ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በማይናማር የተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የበለጠ ተጋላጭነታቸውን ከፍ አድርጎታል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጥር 19 በማይናማር ላይ በማተኮር ባቀረቡት የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት፥ የሰብአዊ ዕርዳታ እንዲመቻች እና ሁሉም ሰው የውይይት ጎዳና እንዲከተል በመማፀን፥ “ለሦስት ዓመታት ያህል የህመም ጩኸቶች እና የጦር መሳሪያ ጋጋታ የማይናማርን ህዝብ ደስታ ቀምተዋል” ብለዋል። 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከበርማ ጳጳሳት ጋር በመሆን ድምፃቸውን በማሰማት “የጥፋት መሳሪያዎች በሰብአዊነት እና በፍትህ ውስጥ ማደግ እንዲቻል ወደ ልማት መሳሪያዎች እንዲቀየሩ” ጸልየዋል።

አንድ ሶስተኛው ህዝብ ተስፋ አስቆራጭ ኑሮ እየኖረ ነው

በማይናማር ያለው ሰብአዊ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እና ሲቪሉ ህዝብ በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ እየኖረ እንደሆነ ተነግሯል። በዚህም ምክንያት በአገር ውስጥ የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ መሆኑን ፊደስ ዜና ዘግቧል።

በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመላ አገሪቱ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአጠቃላይ ከሀገሪቱ ህዝብ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት 18.6 ሚሊዮን ሰዎች፥ ከፍተኛ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

በሀገሪቱ እየጨመረ ባለው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ሰዎች ምግብ፣ ማገዶ እና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦችን መግዛት አስቸጋሪ እየሆነባቸው መጥቷል።

በሀገሪቱ ያለው የጤና አጠባበቅ ስርዓት ከሞላ ጎደል የወደቀ ሲሆን፥ አንድ አራተኛው ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ በሽታን እና ረሃብን እየተጋፈጠ ይገኛል።
 

27 March 2024, 14:15