ፈልግ

እስራኤል በወሰደችው ጥቃት የቆሰሉ ፍልስጤማውያን በአልሺፋ ሆስፒታል አልጋ ላይ ተኝተው እስራኤል በወሰደችው ጥቃት የቆሰሉ ፍልስጤማውያን በአልሺፋ ሆስፒታል አልጋ ላይ ተኝተው 

የኢየሩሳሌም አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በጋዛ የደረሰውን ከባድ ጥቃት አጥብቀው አወገዙ

በእየሩሳሌም የሚገኙት የሃይማኖት አባቶች እና የአብያተ ክርስቲያናት ሃላፊዎች አርብ የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ባለፈው ሳምንት የእስራኤል ጦር በጋዛ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ እየተከፋፈለ ባለበት ወቅት “በንጹሐን ዜጎች ላይ ያደረሰችውን ከባድ ጥቃት” በማውገዝ፥ “አስቸኳይ እና ረዘም ላለ ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት” እንዲደረግ በመጠየቅ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ትልቁ የሕክምና ማዕከል የሆነው የአል-ቺፋ ሆስፒታል ዶክተሮች እና አንዳንድ ምስክሮች እንደተናገሩት የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕለተ ሃሙስ ላይ የእስራኤል ወታደሮች በፍልስጤም ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ጋዛ ከተማ ከእርዳታ መኪናዎች ላይ የተለያዩ የምግብ ዕርዳታዎች ለተረጅዎች እየተከፋፈለ ባለበት ወቅት የእስራኤል ወታደሮች በሲቪሎች ላይ የተኩስ ጥቃት አድርሰዋል። በደረሰውም ጥቃት የሟቾች ቁጥር 112 የደረሰ ሲሆን፥ 760ቹ ደግሞ ቆስለዋል ሲል በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ይህ በእንዲ እያለ የእስራኤል ጥብቅ አጋር የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ የቤንጃሚን ኔታንያሁ መንግሥት ሐሙስ ዕለት የፈጸመውን ግድያ ተከትሎ “ጥልቅ ምርመራ” እንዲደረግ ጠይቃለች።

ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት

በእየሩሳሌም የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች እንደተናገሩት “ተፋላሚዎቹ ወገኖች አስቸኳይ እና ረዘም ላለ ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ይህም በመላው የጋዛ ሰርጥ ላይ የእርዳታ አቅርቦቶችን በፍጥነት ለማሰራጨት እንዲሁም በሃማስ የታገቱ ሰዎች እና በእስራኤል ቁጥጥር ስር ያሉ እስረኞች በድርድር እንዲፈቱ ያስችላል ብለዋል።

በተጨማሪም “የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሃገሪቷ የፈጸመችውን የኃይል እርምጃ መካዳቸውና እና ለደረሰው ጥቃት ተጎጂዎችን ለመወንጀል መሞከራቸውንም” አውግዘዋል።

ብጹአን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው “በጦርነት ለሚሰቃዩ ንፁሀን ዜጎች” ያላቸውን ቀረቤታ በመግለጽ፥ “በካቶሊክ ቤተክርስቲያ ሃዋሪያዊ አገልግሎት ጥበቃ ስር ለሚገኙት የክርስቲያን ማህበረሰቦች ልዩ የድጋፍ ጸሎት” እንደሚደረግም አሳዉቀዋል። እነዚህም ላለፉት አምስት ወራት በጋዛ ከተማ በሚገኙት በቅዱስ ፖርፊዮስ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በ‘ሆሊ ፋሚሊ’ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙት 800 ክርስቲያኖችን ያጠቃልላል ተብሏል።

መግለጫው አክሎም “ጸሎታችን እና ቅርበታችንን በተመሳሳይ መልኩ በአንግሊካን በሚተዳደረው አህሊ ሆስፒታል ውስጥ ለሚሰሩ ትጉህ ሰራተኞች እና በጎ ፈቃደኞች እንዲሁም ለታካሚዎቻቸው እናቀርባለን” ይላል።

ስለ ሰላም ጸሎቶች

የቤተክርስቲያኑ መሪዎች ያወጡት መግለጫ በማጠቃለያው ላይ የሁለቱ ሃገራት ግጭት በአስቸኳይ እንደሚቆም፣ የታሰሩት እንደሚፈቱ እና ለተጎጂዎች አስፈላጊው ነገር ሁሉ እንደሚደረግላቸው ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፥ እነዚህም ተግባራት ሥራ ላይ ሲውሉ “ወሳኝ ለሆኑ የዲፕሎማሲያዊ የውይይት አድማስ በር እንደሚከፍቱ እና በመጨረሻም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ መስቀሉን የተሸከመበት አከባቢ ላይ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጡ አመላክተዋል።

በመጨረሻም “የዚህን ተስፋ ሰጪ የትንሳኤ ራዕይ ፍጻሜ እንድናይ እግዚአብሔር ለሁላችንም ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ እንለምናለን” በማለት አጠቃለዋል።
 

04 March 2024, 12:55