ፈልግ

የኬንያ የልዑካን ቡድን የጸጥታ ሃይሉን ለመገምገም ከሄይቲ ፖሊስ አዛዥ ጋር ተገናኘ የኬንያ የልዑካን ቡድን የጸጥታ ሃይሉን ለመገምገም ከሄይቲ ፖሊስ አዛዥ ጋር ተገናኘ 

ወሮበሎች በሄይቲ በሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ የሚያገለግሉ ሦስት መነኮሳትን አገቱ

የታጠቁ ወሮበሎች በሄይቲ መዲና ፖርት ኦ ፕሪንስ ውስጥ የሚገኘውን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል በመውረር ሦስት የቅዱስ ዮሴፍ ደ ክሉኒ ማኅበር መነኮሳትን አግተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሄይቲ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መነኮሳት በአፈና እና በማስለቀቂያ ገንዘብ ጥያቄ የተነሳ አገልግሎታቸውን ለማበርከት እንደተቸገሩ በካሬፎር-ፊዩልስ የሚገኘው የቅዱስ ጄራርድ ቁምስና የቀድሞ መሪ ካኅን አባ ጂልበርት ፔልትሮፕ ማክሰኞ ዕለት ገልጸዋል።

ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ወሮበሎች በመዲናይቱ ፖርት ኦ ፕሪንስ የቅዱስ ዮሴፍ ደ ክሉኒ ማኅበር መነኮሳት በሚኖሩበት የ ላ ማዴሊን ወላጅ አልባ ሕጻናት ማሳደጊያ ቅጥር ግቢ በመግባት ወረራ ማካሄዳቸውን አባ ጂልበርት ተናግረዋል። አጋቾቹ እስከ ረቡዕ የካቲት 27/2016 ዓ. ም. ድረስ ከገዳሙ አለቆች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳላደረጉ እና የማስለቀቂያ ገንዘብ ጥያቄ አላቀረቡም ተብሏል። ጥቃቱ የተፈጸመበት የፖርት ኦ-ፕሪንስ አካባቢ በ '400 ማዎዞ' በተባለ የወሮበላ ቡድን ቁጥጥር ሥር የሚገኝ እንደሆነ ታውቋል።

የደህንነት እጦት እየጨመረ መጥቷል

በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት ኦ-ፕሪንስ ውስጥ የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፥ ወሮበሎቹ በፖሊስ ተቋማት እና ማረሚያ ቤቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። የታጠቁ ወሮበሎቹ በብሔራዊ ማረሚያ ቤት እና በሲቪል ማረሚያ ቤት ላይ የካቲት 23/2016 ዓ. ም. የፈፀሙትን ጥቃት ተከትሎ ከ5,000 በላይ ታራሚዎች ነፃ መውጣታቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም የቦን-ሬፖስ፣ የካዛው እና የካርፎር ዴ ኤሮፖርት ንዑስ የፖሊስ ኮሚሽኖችን ጨምሮ በርካታ የሄይቲ ብሔራዊ ፖሊስ ኮሚሽን ጣቢያዎች በወሮበላ ቡድኖች ጥምረት አባላት ጥቃት ደርሶባቸው በእሳት መጋየታቸው ታውቋል። “ቪቭ አንሳም” ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ የወሮበሎች ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ስልጣን እንዲለቁ ይጠይቃል።

መንግሥትን ለመጣል የሚሹ ወሮበሎች

ሁከቱ በተለያዩ ተቋማት ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፥ በዋና ከተማይቱ የሚገኙ በርካታ የወሮበላ ቡድኖች መንግሥትን የመገልበጥ ዓላማ እንዳላቸው ይገልጻሉ። የቀድሞው የሄይቲ ፕሬዝደንት ጆቬኔል ሞይስ ከተገደሉበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2021 ወዲህ የወቅቱ ፕሬዝደንት የአሪየል ሄንሪ ስልጣን ሕጋዊነት ክርክሮችን ሲያስነሳ የቆየ ሲሆን፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

ከፖለቲካ ስልጣን ባሻገር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ብዙ ተቋማት የጸጥታ ችግር እና የቡድን ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። የ "ቪቭ አንሳም" የወሮበላ ቡድን ቃል አቀባይ እና የቀድሞው የፖሊስ መኰንን ጂሚ ቼሪዚየር፥ በቅጽል ስሙ "ባርቤኪው" የሚባለው ማክሰኞ በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ባስተላለፈው መልዕክት በወሮበላ ቡድን የታገቱት በሙሉ ያለ ማስለቀቂያ ገንዘብ በነጻ እንደሚለቀቁ አስታውቋል።

የታጠቁ ወሮበሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥስልጣን ለማውረድ የሚያደረጉትን ትግል ለማጠናከር ሲሉ በሲቪሉ ማኅበረሰብ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማቆም ማሰባቸውን "ባርቤኪው" አስረድቷል። ይሁን እንጂ የካቲት 15/2016 ዓ. ም. ከቢሴንቴነየር ታፍነው የተወሰዱ አምስት ገዳማዊ ወንድሞችን ጨምሮ ስድስት የቅዱስ ልብ ኢየሱስ ማኅበር አባላት እስከ ዛሬ ነጻ አልተለቀቁም።

07 March 2024, 13:31