ፈልግ

2020.10.13 Gesù con dieci lebbrosi

እግዚአብሔርን ማመስገን ተገቢ ነው

ኢየሱስ ወደ አንዲት መንደር በገባ ጊዜ አሥር ለምጻሞች ወደ እርሱ መጥተው በሩቅ ቆሙ። ድምጻቸውንም ከፍ አድርገው «ኢየሱስ ሆይ መምህር ሆይ እባክህን ራራልን” እያሉ ጮኹ ለመኑትም። እርሱም ትኩር ብሎ ከተመለከታቸው በኋላ “ሂዱና ራሳችሁን ለካህን አሳዩ” አላቸው።

የእዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሲሄዱ በመንገድ እያሉ ከበሽታቸው ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ዳነ አውቆ ድምጹን ከፍ አድርጐ እግዚብሔርን እያመሰገነ ወደ ኋላ ተመልሶ በኢየሱስ እግር ሥር ወድቆ አመወሰገነው። ይህ ለምጻም ሰው ሳምራዊ ነበረ። ይህንን ካየ በኋላ ኢየሱስ “የዳኑ አሥር አልነበሩምን ታዲያ ዘጠኙ ወዴት ሄዱ፣ ከዚህ የውጭ አገር ሰው በስተቀር ሌላ እግዚአብሔርን ሊያመሰግን የተመለሰ የለም” (ሉቃስ 17፡11-19) እያለ አዝኖ ተናገረ።

ይህ የወንጌል ታሪክ እግዚአብሔር ላደረገልን መልካም ነገር ማመስገን መርሳት እንደማይገባን ያስታውሰናል። ሲያሰፈልገን እግዚአብሔርን እንለምናለን። እርሱ ደግሞ ድኻነታችንን አውቆ ራርቶልን የሚያስፈልገንን ይሰጠናል። ልመናችን ከተሳካ በኋላ ብዙ ጊዜ ሳናመሰግነው እንቀራለን። እርግጥ እርሱ ምስጋናችን አያስፈልገውም። የሚጨምርለት ነገር የለውም። ነገር ግን ተገቢ ስለሆነ እንድናመሰግነው ይፈልጋል። ብናስበውም እንደ እርሱ መልካም ነገር ስላደረገልን ማመስገን ተገቢ ነው።

“እግዚአብሔር አምላክን እናመሰግነው” ትላለች ቤተክርስቲያን ፈጣሪያችን ጌታችን፣ የሚወደን ሰማያዊ አባታችን እርሱ ነው። ስለዚህ ዘወትር ምስጋናችንን እንድናቀርብለት ይገባናል። በቸርነቱ፣ በአስተዳዳሪነቱ የሚያኖረን፣ በነፍሳችን በሥጋችን የሚረዳን፣ በመከራችንና በችግራችን ጊዜ የሚደርስልንና የሚያድነን፣ በሐዘናችን የሚያጽናናን እሱ ነው። በዚህ ምክንያት ልናመሰግነው ይገባናል። ኃጢአታችንን እያየ የሚገባንን ቅጣት በመስጠት ፈንታ ይታገሰናል።

በእርሱ ያለ ሥጋት እንድንኖር በምሕረቱ ንሰሐ ገብተን እንደንመለስ የሚጠብቀን እርሱ ነው። በዚህ ደግሞ መጨረሻ በሌለው ምስጋና ከልባችን ልንሰግድለት ይገባናል። ቅዱስ ጳውሎስ “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በማናቸውም ሁኔታ አመስግኑት” (1 ተሰሎንቄ 5፡16) ይለናል። መልካም በመልካም ሲመለስ ፍቅር በፍቅር ይካሳል። መልካም ነገር ያደረገልንን እግዚአብሔርን ማመስገን ተገቢ ነው። ለሰው ባደረገልን መልካም ነገር ትንሽ ነገርም ቢሆን እንደምናመሰግን እግዚአብሔር በይበልጥ ልናመሰግነው ይገባል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያደረገልን መልካም ይህ ነው ተብሎ ሊቆጠር አይቻልም። በሌላ አነጋገር መሳካቱ ቀላል አይደለም። ኢየሱስ እነዚያን ዘጠኙን ሳያመሰግኑት የሄዱትን ወቀሳቸው፣ ፈረደባቸው። ሊያመሰግነው የተመለሰውን ግን አመሰገነው። ባደረገልን መልካም ነገር እግዚአብሔርን ሳናመሰግነው ዝም ብንል ይፈርድብናል። ብናመሰግነው ግን ትሩፋት ይታሰብልናል፣ እንደገና ሌላ ዕርዳታ ሊሰጠን ይወስናል፣ ስለዚህ በሚሰጠን ሁሉ ዕርዳታ እርሱን ማመስገን አንርሳ።

07 March 2024, 15:30