ፈልግ

Papa: lasciamoci 'misericordiare' da Dio

ቂም በቀል

መጋቢት 9

መንግሥተ ሰማያት ከገልጋዮች ጋር የሚተሳሰብ ንጉሥ ትመስላለች፡፡ ንጉሡ መተሳሰብ በጀመረ ጊዜ አሥር ሺህ ብር ያለበት አንድ ሰውዬ ተይዞ መጣና በፊቱ ቆመ፡፡ ይህ አገልጋይ ዕዳውን መክፈል ስላልቻለ እርሱም ሚስቱም ልጆቹም ያለውን ንብረት ተሽጦ ዕዳውን አንዲከፍል ጌታው አዘዘ፡፡ አገልጋዩ ግን በጌታው እግር ሥር ተንበርክኮ በግባሩ ተደፍቶ «ጌታ ሆይ! እባክህን ታገሠኝ ሁሉንም እከፍልሃለሁ” (ማቴ. 18፣22-35) እያለ እያለቀሰና እንባውን እያፈሰሰ አጥብቆ ለመነው፡፡ ጌታውም ራራለትና ነጻ ለቀቀው፣ ዕዳውን በሙሉ ስለተወለት ተደስቶ እጅ ነሥቶ አመስግኖ ሄደ፡፡ ነገር ግን አገልጋዩ ከዚያ ከንጉሥ ግቢ ወጥቶ ሲሄድ መቶ ብር ያበደረውን የሥራ ጓደኛውን አገኘና አንገቱን አንቆ ይዞ “ያበደርኩህን ገንዘብ ቶሎ ክፈለኝ” በማለት አፋጠጠው፡፡

ተበዳሪው ጓደኛውም በእግሩ ሥር ተንበርክኮ ወድቆ እባክህ ታገሠኝ እከፍልሃለሁ ሲል አበክሮ ለመነው፤ አበዳሪው ግን እምቢ አለው፡፡ እንዲያውም ይዞት ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ ወህኒ ቤት አሳሰረው፡፡ ሌሎች የሥራ ጓደኞቹ ይህንን አስከፊ ግፍ አይተው እጅግ አዘኑ፡፡ ሄደውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ነገሩት፡፡ ጌታውም ያን ግፈኛ አገለጋይ አስጠርቶ እንዲህ ሲል ተቆጥቶ ገሠጸው “አንተ ክፉና ግፈኛ አገልጋይ ስለ ለመንከኝ ያን ያለብህን ዕደ ተውኩልህ፣ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው አገልጋይ ዕዳውን ልትተውለት አይገባህም ነበርን? ስለዚህ ጌታው ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ ለሚያሰቃዩት አሳልፎ ሰጠው”፡፡ እነርሱም በስቃይ ሥፍራ አስገቡት፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ለአገልጋዮቹ ለሚበድል ይቅር ለማይል ሰው እንደዚህ ይደረጋል አላቸው፡፡ ኢየሱስ በዚህ ቁልጭ ባለ ምሳሌ እግዚአብሔር እኛ ስንበድለው ምን እንደሚያደርገን እኛም ሌላውን ሰው ሲበድለን ምን ማድረግ እንደሚገባን ያሳስበናል፡፡ በአንድ በኩልም እግዚአበሔር ከሰው  በሌላ በኩልም ደግሞ ሰው ከሰው ጋር ሲኖር የሚያሳየውን ችሮታ ያስረዳናል፡፡ እግዚብሔርንና ታላቅ ምሕረቱን የሰውንም ጭካኔና ቂም ይገለጥልናል፡፡

እግዚአብሔር እኛን የሆነ ኃጢአት ቢኖርብን ይምረናል ፈጽሞ ይተውልናል፡፡ እኛ ግን ባልንጀሮቻችን ቢበድሉን በልባችን ውስጥ ቂምና በቀል ይዘን ምሕረትና ይቅርታ እንከለክላለን፡፡ እግዚአብሔር በኃጢአታችን ተጸጽተን ስንቀርበው እጆቹን ዘርግቶ ልቡን ከፍቶ ይቀበለናል፣ ብዙ ካሣ ሳይሰጠው ሙሉ ምሕረት ይሰጠናል፣ በደላችንን ሁሉ ይረሳዋል፡፡ እኛ ግን ባልንጀራችን ተጸጽቶ ሲመጣ ይቅርታ መስጠት እያለብን አይሆንም እምቢ እንለዋለን።በቁጣና በዘለፋ ፊቱን አዙሮ እንዲሸሽ እናደርገዋለን፣ ቂማችንን ይዘን አጋጣሚ ስናገኝ እንቀበለዋለን፡፡

ንጉሡ አሥር ሺህ ብር ዕዳ ሊከፍለው ይገባው ለነበረ አገልጋይ በአግሩ ሥር ወድቆ ስለለመነው ተወለት ሙሉ ምሕረትም አደረገለት፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለብን ዕዳ ከባድና በያይነቱም ሞልቶ የተረፈ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ሆነን እግዚአብሔር ሳይጠላንና ሳይቀየመን በትዕግሥት ይጠባበቀናል፣ በምሕረቱ ብዛት ኃጢአታችንን ሁሉ ይረሳዋል፡፡ ሰው እኛን ጥቂተ ቢያሳዝነን ግን ተቀይመን አንጠላዋለን፡፡ እርሱ እኮ ክፉኛ ሰደበኝ፣ ክፉ አደረገብኝ፣ ምንም ሳላደርገው ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ እኔን ለማጥፋትና ለመጉዳት ብዙ ተንኮል አልሞአል፣ አልተሳካለትም እንጂ በቃልም ሆነ በምግባር እኔን ለመጉዳት ያላደረገው ፈተናና ሙከራ የለም፤ ታዲያ እርሱ እንዳደረገብኝ አኔም አደርግበታለሁ በድሎኛልና እኔም እንደ እርሱ አጸፋውን እመልስለታለሁ፡፡ «ዓይንን ስለ ዓይን፣ ጥርስን ስለ ጥርስ ብድር መመለስ ያስፈልጋል” ይህን ሰውዬ ከእንግዲህ ላየው አልፈልግም ጠላቴ ነው፡፡ ሰድቦኛል፣ አዋርዶኛል፣ በድሎኛል ልሰማውም አልፈልግም የሚል መጥፎ ሐሳብ በልባችን ውስጥ እናሳድራለን።ቂም ከባልንጀራችን በፍጹም ያጣላናል፡፡ ባልንጀራችን ሲጐዳ ወይም ሲያዝን እንደሰታለን፣ በአንጻሩ ደግሞ ቢደሰት እናዝናል፣ መጥፎውን ክፉውን እንመኝለታለን፣ ብድር ለመመለስ አመቺ ጊዜ እንጠብቃን፣ ልባችን በቂም ተመርዞ ክፉ እንጂ መልካም አናስብለትም፡፡ ከቂማችን ጋር ስንኖር በሕሊናችን ከእግዚአብሔር ጋር በሰላም ያለን ይመስለናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን «በደላችንን ይቅር በለን ልንለው እንደፍራለን፣ በልባችን ቂም ይዘን ጸሎት እናደርጋለን፣ ማን ያውቃል ምስጢራትን እንቀበል ይሆናል፡፡ በሕሊናችን ውስጥ ቅር ያለው እንደሆነ «እኔ ምን አደረግሁት; እርሱ ነው እኔን የበደለኝ ስለዚህ እርሱ ነው ሊሰጋና ይቅርታ ሊለምነኝ የሚገባው እያልን ሕሊናችንን እናሳርፋለን፡፡

ያ ንጉሥ የማረው አገልጋይ ባልንጀራውን እንዳሳሰረው ባወቀ ጊዜ አዝኖና ተቆጥቶ እርሱም ለግፈኛውን አገልጋይ ምሕረቱን በመንሣት ዕዳውን እስኪከፈል ድረስ አሳሰረው፡፡ “እናንተ ባልንጀራችሁን ብትምሩ ሰማያዊ አባታችሁ ደግሞ እንደዚሁ ያደርግላችኋል” ይለናል ኢየሱስ፡፡ ንግግሩን በማያያዝ ቀጥሎም “በምትሠፍሩበት መሥፈሪያ ይሰፈርባችኋል” እያለ በጥብቅ ያሳስበናል፡፡ እኛ ባልንጀራችንን ብንምር እርሱም ይምረናል፡፡ እኛ በበኩላችን ምሕረት ለማድረግ እምቢ ብንል በልባችን ቂም ብንይዝ ግን እርሱም ምሕረት ሊከለክለን ሊቀየመን ነው፡፡ ቂም የስንፍና የድክመት ሥራ ያዘቀጠ ውጤት ነው፣ የሰይጣን ባቡር ነው፡፡ ምሕረት ግን የጀግንነተ አምላክ ሥራ ስለሆነ ስለዚህ ቂምን ጠልተን ምሕረትን እንውደድ፡፡

መልካም ቀን ለሁላችን

 

18 March 2024, 10:47