ፈልግ

ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ እምነት ነው! ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ እምነት ነው! 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 3፡28 ላይ እንደሚናገረው በእምነት ብቻ ድነን የለምን?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲፀድቅ እንቆጥራለንና›› ብሎ የሚያስተምረው በብሉይ ኪዳን ዘመን የተሰጡትን የሙሴ ሕግጋት፣ የግዝረትን ሥርዐት ወ.ዘ.ተ. በመፈጸም መዳን እንደማይቻል ለማስተማር ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን መዳን የሚመጣው በማመን ወይም በእምነት ነው፤ እምነት ደግሞ ሕያው የሚሆነው በመልካም ሥራ ሲገለጥ ነው፡፡ የመዳን እምነት በሥራ የሚገለጥ እና ‹‹በፍቅር የሚሠራ እምነት ነው›› (ገላ 5፡6)፡፡

በ1ቆሮ 13፡2 ላይ እምነት ያለ ፍቅር ከንቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በፍቅር ሥራ የማይገለጥ እምነት አያድንም፡፡ መልካም ሥራ ማለት የእግዚአብሔር ፍቅር ማለት ነው፤ ኢየሱስን የምንወደው ከሆነ ትዕዛዛቱን እንደምንጠብቅ ይናገራል (ዮሐ14፡21)፡፡ ሐብታሙ ሰው ይድን ዘንድ ምን ማድረግ እንደሚገባው ኢየሱስን በጠየቀው ጊዜ ጌታ እንዲህ የሚል መልስ ሰጠው ‹‹ትዕዛዛቱን ጠብቅ›› (ማቴ19፡16-17) እንግዲህ ለመዳን ማመን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡ ፍቅር መኖር አለበት፤ እምነታችን በፍቅር ሥራ እና ትዕዛዛቱን በመጠበቅ መገለጥ ይኖርበታል፡፡

 ቅዱስ ያዕቆብ ያለ ሥራ በእምነት ብቻ ድነናል የሚለውን ሐሳብ ይቃወማል ‹‹ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ... ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ ሁሉ ከሥራ የተለየ እምነት እንዲሁ የሞተ ነው››(ያዕ2፡24-26)፡፡

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መዳናችን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ መሆኑን ታስተምረናለች፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ በፍቅር የሚሠራውን የመዳናችንን እምነት እንድንጨብጥ የሚያስችለን ሥጦታ ነው (ኤፌ 2፡8-10)፡፡ መልካም ሥራ ሁሉ መልዕልተ ባሕርያዊ የሆነ ፍሬ እንዲኖረው በእግዚአብሔር ጸጋ መፈጸም አለበት፡፡

የክርስቶስ የማዳን ሥራ ሁሉን የሚጠቀልል እና ዕዳችንንም ሁሉ የከፈለ ሆኖ ሳለ ካቶሊካውያን የፍቅር ሥራዎችን መፈጸም እና ንስሐ መግባት ያስፈልጋል የሚሉት ለምንድ ነው?

 ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መዳን በእምነት እና በፍቅር ሥራ የተደገፈ እንደሆነ ስታስተምር በክርስቶስ የመዳን ተግባር ምሉእነት ላይ ጥርጣሬ አላት ማለት አይደለም፡፡ ፕሮቴስታንቶች ይህ ዓይነቱን አመለካከት ልክ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት አድርገው ያቀርቡታል፡፡ ለእነርሱ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ፈፅሞ ስለዳነን የፍቅር ሥራዎች፣ ንስሐ፣ የንስሐ ቦታ፣ ወደ ቅዱሳን መጸለይ እና ምሥጢራት ወ.ዘ.ተ. አላስፈላጊ ቅጥያዎች ናቸው፡፡ ፕሮቴስታንቶች ይህ አይነት የግንዛቤ ችግር የሚፈጠርባቸው የክርስቶስን የማማዳን ስራ ከመዳን ጥሪ ጋር ስለሚቀላቅሉት ነው፡፡

 ካቶሊካውያን የክርስቶስ አዳኝ ተግባር ምሉእ እና ምንም ነገር ያልጎደለበት ፍጹም መሆኑን እናምናለን፡፡ ኢየሱስ በሕማማቱ፣ በሞቱ እና በትንሣኤው ሁላችንንም አድኖናል፡፡ ስለ ኃጢአታችንም ሁሉ የደም ዋጋ ከፍሎ ለእያንዳንዳችን የመዳን በር ከፍቶልናል፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ ድነናል ማለት አይደለም።የሰው ልጅ የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለው ሁሉም ክርስቲያኖች ይስማማሉ፤ ሰው በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ አሻፈረኝ ያለ እንደሆነ ወይም በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ለእግዚአብሔር ጸጋ የማይታዘዝ ከሆነ ከመዳን ይጎድላል፡፡ ምንም እንኳን የክርስቶስ የማዳን ሥራ ፍጹም ቢሆንም የዚህ ማዳን ፍሬ በእያንዳንዱ ክርስቲያን የመዳን ጥሪ ውስጥ ተገቢውን ፍሬ እንዲያፈራ በሥራ ሊገለጥ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ሰው ልቡን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ አለበት (ማቴ 4፡17)፣ በኢየሱስ ማመን አለበት(ሐ.ሥ 16፡31)፣ ትዕዛዛቱን መጠበቅ አለበት(ማቴ 19፡16-17)፣ የፍቅር ሥራ መሥራት አለበት (1ቆሮ 13፡1-3) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሥክርነት ይህ ነው፡፡ በክርስቶስ፣ ስለ ክርስቶስ እና ከክርስቶስ ጋር የፍቅር ሥራ የሚሠራ ካቶሊክ የክርስቶስን የማዳን ተግባር ምሉእነት እየተገዳደረ ሳይሆን በክርስቶስ የማዳን ሥራ ያገኘውን የጸጋ ሥጦታ እየተጠቀመበት ነው፡፡

ሰው አንድ ጊዜ እንደ ጌታ እና የግል አዳኝ አድርጎ ኢየሱስን ከተቀበለ በኃላ መዳኑን ሊያጣ ወይም ከመዳን ሊጎድል ይችላልን?

በርካታ ፕሮቴስታንቶች አንድ ጊዜ ኢየሱስን ጌታ እና የግል አዳኝህ አድርገህ ከተቀበልክ ድነሃል፣ ከዚያ በኋላ በምንም መልኩ በፍጹም ልትኮነን አትችልም ብለው ያምናሉ፡፡ ይህ ትምህርት ‹‹ ሰው አንድ ጊዜ ከዳነ መዳኑ ለዘላለም ነው›› የሚል ነው፡፡ ልክ እንደ በርካታዎቹ የፕሮቴስታንት ሐሳቦች ይህኛውም እነ ሉተር እስከተነሱበት ጊዜ ድረስ ተሰምቶ የማይታወቅ ነው፡፡

ማቴ 24፡13 እንደሚናገረው ለመዳን እስከ መጨረሻ መፅናት አለብን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በ2ጢሞ 2፡12 ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ ይሰነዝራል፡- ‹‹ከክርስቶስ ጋር ለመንገስ ከፈለግን መፅናት አለብን››፡፡ በሮሜ 11፡22 እንደተገለጸው ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ቸርነት ጸንተው ካልኖሩ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ሕብረት ይቋረጣል፡፡ ወደ ዕብራውያን የተላከው መልዕክት 6፡4-6 ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሕብረት የነበራቸው፣ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እና የሰማያዊ ብርሃን ተካፋዮች የነበሩ ክርስቲያኖች የኋላ ኋላ ከእግዚአብሔር መንገድ እንደወጡ እና ከእነርሱም ጋር የነበራቸው ኅብረት እንደጠፋ ይናገራል፡፡

 የቅዱስ ጳውሎስን ምክር አስታውስ ‹‹በፍርሃት እና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈፅሙ››(ፊል 2፡12)፤ ስለ መዳን ከቅዱስ ጳውሎስ የበለጠ ማን አረጋግጦ ሊነግረን ይችላል? እርሱም ደግሞ እንዲህ ይላል ‹‹ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ›› (1ቆሮ 9፡27)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል፡፡ ክርስቲያኖች ከመዳን የጸጋ ሥጦታ ሊጎድሉ ይችላሉ፡፡

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለመዳን ዘወትር በሚቀድስ ጸጋ ውስጥ መኖር እንዳለብን ታስተምራለች፡፡ ገዳይ ኃጢአት ከነፍስ ላይ የሚቀድስ ጸጋን ሕልውና ያጠፋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ሳለን ብንሞት የገሃነም እሳት ፍርድ የማይቀር ነው፡፡

14 March 2024, 09:20