ፈልግ

መጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቅዱስ 

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ያዘጋጀው ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ሳምንት’ ሊከበር ነው

“መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሴቶችን በህዝባችን ሕይወት እናስርጽ” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 16-21/2016 ዓ. ም. በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር አዘጋጅነት “የመጽሐፍ ቅዱስ ቀን” እና “የቅዱሳት መጽሐፍት አውደ ርእይ” አዲስ አበባ በሚገኘው ስካይ ላይት ሆቴል እንደሚከበር ተገልጿል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ይሄንን መርሃ ግብር በማስመልከት ዛሬ በሆቴሉ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በማህበሩ የቦርድ አባላት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንደተገለጸው፥ “የመጽሐፍ ቅዱስ ቀን” እና “የቅዱሳት መጻህፍት ዐውደ ርእይ” መርሃ ግብር ዋና ዓላማ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ፥ በቃሉም የመኖር ልምምዳቸውን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ መፍጠር፣ በሚቀርቡ ሴሚናሮች እና ትምህርታዊ ውይይቶች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም በዘመናችን መተኪያ የሌለው እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን መግለጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ በሃገራችንም ይሁን በዓለማችን ከዬት ተነስቶ ዬት እንደደረሰ ለአዲሱ ትውልድ ማሳወቅ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ህትመት እና ስርጭት ዘርፍ እስከ አሁን ድረስ የተከናወኑ ተግባራትን ህዝብ እንዲያውቃቸው እና እንዲያያቸው ማድረግ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሴቶችን ለእያንዳንዱ ምእመን የሕይወቱ መመሪያ እንዲሆኑ ማስተማር እና ግንዛቤ መፍጠር፣ እና አብያተ ክርስቲያናት ከማህበሩ ጋር በትብብር እንዲሠሩ ማበረታታት እንደሆነ በመግለጫው ተብራርቷል።

ከማህበሩ ምን ውጤት ይጠበቃል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሻቸውን ሲሰጡ፥ ከዚህ መርሃ ግብር በኋላ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሴቶችን መርህ ያደረገ በሥነ-ምግባር እና በሞራል የታነጸ ትውልድ ተፈጥሮ ማየት፣ አብያተ ክርስቲያናት በመጽሐፍ ቅዱስ እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው እንዲሠሩ ማድረግ እና ዛሬ በእጃችን ላይ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ተሻግሮ እንዴት እጃችን ላይ እንደደረሰ ግንዛቤ ያለው አማኝ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።  

ስለ ማህበሩ አወቃቀር በመግለጫው እንደተነገረው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በማንም የእምነት ተቋም ውስጥ ጣልቃ ሳይገባ የስላሴ አማኝ የሆኑትን አብያተ ክርስቲያናትን በጋራ አቅፎ አገልግሎት የሚሰጥ ማህበር እንደሆነ፥ በዚህም ምክንያት ማህበሩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና ከወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር በትብብር እንደሚሠራ ተገልጿል።

በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር አቢያተ ክርስቲያናት የጋራ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ በትብብር የሚሠሩበት ብቸኛ መድረክ እንደሆነም ጭምር ተብራርቷል። በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ጥላ ስር አብያተ ክርስቲያናት በጋራ የሚያከናውኗቸው ተግባራት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራዎች፣ የስርጭት ሥራዎች፣ ለቃሉ ጥብቅና መቆም፣ የማነቃቃት ሥራዎች እና የመሳሰሉት እንደሆነም ተነግሯል።

ከቅርብ ዓመታት በኋላ የማህበሩ የአገልግሎት ዘርፎች መንፈሳዊ አገልግሎት እና ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎት በመባል ሁለት ገጽታ እንዲኖራቸው እንደተደረገ እና በእነዚህም ዘርፎች ስር በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፣ ህትመት እና ስርጭት ሥራ ላይ እንደተሰማራ ተገልጿል። የመጽሐፍ ትርጉም ሲባል የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ የሰው አስተያየት ሳይጨመርበት ሰዎች በቀላሉ በሚረዱበት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማስተርጎም እንደሆነ፥ እንደዚሁም በህትመት ዘርፍ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በከፍተኛ ጥራትና ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለአያያዝ እና ለአጠቃቀም አመቺ በሆነ መልኩ በውጭ ሃገር አሳትሞ ማቅረብ እንደሆነ እንዲሁም በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመውና ታትመው የቀረቡ መጽሐፍ ቅዱሶችን ምዕመናን በቀላሉ እንዲያገኙ የስርጭት ሥራዎችን እንደሚሠራ ተገልጿል።

ስድስት ቀናትን በሚፈጀው መርሃ ግብር ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ገዳማዊያን፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ በትርጉም እና በቅዱሳት መጻህፍት ስርጭት ላይ የተሰማሩ ተባባሪ ድርጅቶች፣ ጥሪ የሚደረግላቸው ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ክርስቲያኖች፣ የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች፣ እህት መጽሐፍ ቅዱስ ማህበራት እና መላው ህዝበ ክርስቲያን እንደሚሳተፉ ተገልጿል።  

 

05 March 2024, 17:30