ፈልግ

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ያዘጋጀው ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ሳምንት’ እና ‘የቅዱሳት መጽህፍት ዐውደ ርዕይ’ ተጀመረ! የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ያዘጋጀው ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ሳምንት’ እና ‘የቅዱሳት መጽህፍት ዐውደ ርዕይ’ ተጀመረ! 

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ያዘጋጀው ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ሳምንት’ እና ‘የቅዱሳት መጽህፍት ዐውደ ርዕይ’ ተጀመረ!

የኢትዮጵያ መጽሃፍ ቅዱስ ማህበር ያዘጋጀው “መጽሃፍ ቅዱሳዊ እሴቶችን በህዝባችን ህይወት እናስርጽ” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 16 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚቆይ “የመጽሃፍ ቅዱስ ቀን” እና “የቅዱሳት መጽሃፍት አውደ ርእይ” አዲስ አበባ በሚገኘው ስካይ ላይት ሆቴል አዳራሽ ውስጥ የተጀመረ ሲሆን፥ ይህ የቅዱሳት መጽሃፍት አውደ ርእይ እስከ መጋቢት 21 ለተከታታይ ስድስት ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ይፋ ተደርጓል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዚህ የቅዱሳት መጽሃፍት ዐውደ ርእይ ዓላማ በአሁኑ ጊዜ በቅዱሳት መጽሃፍት ህትመት ዘርፍ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለህዝብ ማስተዋወቅ፣ የቅዱሳት መጽሃፍት ህትመት ታሪካዊ አመጣጥን ለአዲሱ ትውልድ ማሳወቅ፣ ከተባባሪ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በዘመናችን ያሉ የቅዱሳት መጽሃፍት የህትመት ውጤቶችን ለህዝብ ማቅረብ፣ የቅዱሳት መጽሃፍትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ፣ ብሎም የኢትዮጵያ መጽሃፍ ቅዱስ ማህበር እና በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማትን ከህዝብ ጋር የበለጠ ማቀራረብ እንደሆነ ተነግሯል።

የመጽሃፍ ቅዱስ ማህበር የቦርድ ጸሃፊው በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ ለተገኙት እንግዶች በሰጡት መግለጫ እንደተገለጸው፥ ክርስቲያኖች መጽሃፍ ቅዱስን የማንበብ፥ በቃሉም የመኖር ልምምዳቸውን እንዲያዳብሩ ግንዛቤ መፍጠር፣ በሚቀርቡ ሴሚናሮች እና ትምህርታዊ ውይይቶች አማካኝነት መጽሃፍ ቅዱስ አሁንም በዘመናችን መተኪያ የሌለው እውነተኛ የእግዚያብሄር ቃል መሆኑን መግለጥ፣ የመጽሃፍ ቅዱስ ትርጉም ስራ በሃገራችንም ይሁን በዓለማችን ከዬት ተነስቶ ዬት እንደደረሰ ለአዲሱ ትውልድ ማሳወቅ፣ በመጽሃፍ ቅዱስ ትርጉም ህትመት እና ስርጭት ዘርፍ እስከ አሁን ድረስ የተከናወኑ ተግባራትን ህዝብ እንዲያውቃቸው እና እንዲያያቸው ማድረግ፣ መጽሃፍ ቅዱሳዊ እሴቶችን ለእያንዳንዱ ምእመን የህይወቱ መመሪያ እንዲሆኑ ማስተማር እና ግንዛቤ መፍጠር፣ እና አቢያተ ክርስቲያናት ከማህበሩ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ማበረታታት እንደሆነ በመግለጫው ተብራርቷል።

ከዚህ መርሃ ግብር በኋላ ምን እንደሚጠበቅ ሲገልጹ፥ መጽሃፍ ቅዱሳዊ እሴቶችን መርሁ ያደረገ በስነ ምግባር እና በሞራል የታነጸ ትውልድ ተፈጥሮ ማየት፣ አብያተ ክርስቲያናት በመጽሃፍ ቅዱስ እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበው እንዲሰሩ ማድረግ እና ዛሬ በእጃችን ላይ ያለው መጽሃፍ ቅዱስ ዘመን ተሻግሮ እንዴት እጃችን ላይ እንደደረሰ ግንዛቤ ያለው አማኝ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።

በዐውደ ርእዩ የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ ብጹእ አቡነ ማርቆስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የስብከተ ወንጌል እና የማህበራዊ አገልግሎት መምሪያ የበላይ ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹእ አቡነ ሉቃስ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ጸሃፊ እና የእምድብር ሃገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ፣ ብጹእ አቡነ ሙሴ በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የእምድብር ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ የተከበሩ ፓስተር ፃዲቁ አብዶ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕረዚዳንት፣ የተከበሩ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አቢያተ ክርስቲያናት ካውንስል ዋና ጸሃፊ፣ የተከበሩ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የአዲስ አበባ የሃማኖቶች ጉባኤ ዋና ጸሃፊ፣ የኢትዮጵያ መጽሃፍ ቅዱስ ማህበር የቦርድ አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ገዳማዊያን፣ የመንግስት ተወካዮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ በትርጉም እና በቅዱሳት መጻህፍት ስርጭት ላይ የተሰማሩ ተባባሪ ድርጅቶች፣ ጥሪ የተደረግላቸው ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ክርስቲያኖች፣ የማህበሩ አባላትና ደጋፊዎች፣ እህት መጽሃፍ ቅዱስ ማህበራት እና በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።  

“የእግዚያብሄርን ቃል በታላቅ አክብሮት የምናዳምጠው፣ በታላቅ እምነት የምንመሰክረው ቃል ነው” ያሉት ብጹእ አቡነ ሉቃስ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ጸሃፊ እና የእምድብር ሃገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ በመክፈቻ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት “የወንጌል አስተምህሮ የወንጌል እውነት ያነጸው ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ትግል ላይ የእምነት ተቋማትም ሆኑ የኢትዮጵያ መጽሃፍ ቅዱስ ማህበር ትልቅ ተልዕኮ ስላላቸው ይህንን ለመፈጸም ይቻል ዘንድ ነው ይሄ ጉባኤ የተዘጋጀው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በመወከል የቅዱስ ፍራንቺስኮስ ማህበር እና የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት “በአንድ ሃሳብ ተስማምታችሁ እና አንድ ፍቅር፣ አንድም ልብ፣ አንድም ሃሳብ ኖሯችሁ ደስታዬን ፈጽሙልኝ” በሚል መሪ ቃል በርካታ መጽሃፍ ቅዱሶችን፣ ታሪካዊ ቅዱሳት መጽሃፍትን፣ በቤተክርስቲያኒቷ ልሂቃን የተጻፉ መፅሃፍቶችን እና ቤተክርስቲያን ነክ ቁሳቁሶችን በመያዝ በዐውደ ርእዩ ላይ ተሳትፈዋል።

መጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. “የመጽሃፍ ቅዱስ ትርጉም ቀን” ተብሎ እንደሚከበር እና በዚህም ቀን የመጽሃፍ ቅዱስ ትርጉም ታሪካዊ ጉዞ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ትምህርታዊ ውይይት እንደሚደረግ፣ እንዲሁም መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. “የአቢያተ ክርስቲያናት የትብብር ቀን” ተብሎ እንደሚከበር እና በዚህም ቀን በቅዱሳት መጽሃፍት ትርጉም፣ ህትመት እና ስርጭት እንዲሁም በጋራ ጉዳዮች ላይ ከአብያተ ክርስቲያናት ስለሚጠበቀው ተግባር ውይይት ይደረጋል ተብሏል። በመጨረሻም መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. “የመጽሃፍ ቅዱስ ቀን በኢትዮጵያ” በሚል በእግዚያብሄር ፈቃድ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከናወኑ የቅዱሳት መጽሃፍት ትርጉም፣ ህትመት እና ስርጭት የምስጋና ጸሎት እንደሚደረግ እና በዘርፉ በቀጣይ ስለሚሰሩ ተግባራት አቅጣጫዎች ተቀምጠው የበዓሉ ማጠቃለያ ይደረጋል ተብሏል።

  

26 March 2024, 08:46