ፈልግ

ካሪታስ ኢትዮጵያ አባል የሆነበት የካሪታስ ኢንተርናሽናሊ ዓርማ ካሪታስ ኢትዮጵያ አባል የሆነበት የካሪታስ ኢንተርናሽናሊ ዓርማ 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን 24ኛ ዓመታዊ ጉባኤውን አካሄደ

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን 24ኛ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤውን መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሰላም አዳራሽ ውስጥ ያካሄደ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ካቶሊካዊት ቤተከርስቲያን ካቋቋመቻቸው ተቋማት አንዱ እንደሆነ እና በበጎ አድራጎት ማህበራትና ድርጅቶች ኤጀንሲ ተመዝግቦ ለአለፉት ዓመታት በበርካታ የልማት ሥራዎች ሲሳተፍ የቆየ ድርጅት ነው።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ኮሚሽኑ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ፣ ብፁዓን ጳጳሳት፣ የማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን የቦርድ አባላት፣ የጠቅላይ ጉባኤው አባላት እና የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽ/ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች፣ የሀገረስብከት የማህበራዊ እና ልማት ሥራ ኃላፊዎች ተግኝተዋል።

ጉባኤው በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስትያን የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት በጸሎት እና በቡራኬ የተከፈተ ሲሆን፥ ብፁዕነታቸው አዲስ የተሾሙትን የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ዋና ጸሃፊ ክቡር አባ ከተማን ለጉባኤተኞቹ ካስተዋወቁ በኋላ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ፥ “የኢትዮጵያ ካትሊካዊት ቤተክርስቲያ ምንም እንኳን የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሟትም፥ በሃገሪቷ ሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የምታከናውናቸውን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች አጠናክራ ቀጥላለች” ብለዋል።

ጉባኤው በመቀጠል በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ማህበራዊ እና ልማት ቦርድ የተዘጋጀውን እ.አ.አ የ2023 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻፀም እና የ2024 የስራ ዕቅድ በአቶ በቀለ ሞገስ ፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን ኃላፊ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የቀረበው የ2023 ዓመት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን 4.5 ቢሊዮን ብር በመመደብ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ከሚገኙ አጠቃላይ 530 ወረዳዎች ውስጥ 432 ወረዳዎችን ተደራሽ በማድረግ 5.7 ሚሊዮን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፥ 178 የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ለማከናወን ታቅዶ ፥ በዓመቱ መጨረሻ ከታቀደው በላይ በመከወን 214 ፕሮጄክቶችን ተግባራዊ አድርጓል።

በቀረበውም የ2023 ዓመት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት በኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ውስጥ ባለው የደህንነት ችግሮች ምክንያት የታሰበውን ያክል ሥራዎች እንዳልተሰሩ የሃገረስብከቶቹ ተወካዮች ለጉባኤው ያሳወቁ ሲሆን፥ በሚቀጥለው የበጀት ክፍለ ጊዜ ላይ እነዚህን ችግሮች ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ከዚህም በመቀጠል የ2024 የበጀት ዓመትን የዕቅድና የሥራ አፈፃጸምን በተመለከተ ገለፃ እና ማብራሪያ የተደረገ ሲሆን፥ በዚህም ዓመት ተደራሽነቱን ለ 4.3 ሚሊዮን ህዝብ በማድረግ 3.7 ቢሊዮን ብር በመመደብ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ፕሮጀክቶች ነድፎ የተሻለ ሥራ ለመስራት መታቀዱ ለጉባኤው ተገልጿል። በዚህም መልኩ የተጠቃሚዎች የጾታ ስብጥር የተብራራ ሲሆን፥በዚህም መሰረት በበጀት ዓመቱ 2,320,321 እንስቶችን እንዲሁም 1,999,834 ወንዶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል ተብሏል።

ይህ የግማሽ ቀን ጉባኤ የ2023 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻፀም እና የ2024 የሥራ ዓመት ዕቅድ እና ትግበራ ላይ ተመካክሮ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ውሳኔውን አሳልፏል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን በአጠቃላይ የሃገሪቱ ክልሎች የሚያደርጋቸው የልማት እና የዕርዳታ ሥራዎች ውስጥ በጤናው ዘርፍ፣ በትምህርት ዘርፍ፣ በሴቶች እና በቤተሰብ ልማት፣ በውሃ እና በአከባቢ ልማት፣ በስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች መልሶ ማቋቋም ላይ፣ የተሳለጠ ልማት፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት እና በአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ላይ እንደሚሰራ ይታወቃል።

በመጨረሻም የክቡር አቶ በቀለ ሞገስ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን ኃላፊ የሥራ ዘመን ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት እንደሚቀጥል ከተገለጸ በኋላ ጉባኤው ተጠናቋል።
 

29 March 2024, 13:42