ፈልግ

በቅርቡ በቺሊ የተከሰተውን ሰደድ እሳት ተከትሎ ነዋሪዎቿ መልሶ ለመቋቋም እየጣሩ ይገኛሉ በቅርቡ በቺሊ የተከሰተውን ሰደድ እሳት ተከትሎ ነዋሪዎቿ መልሶ ለመቋቋም እየጣሩ ይገኛሉ 

የቺሊ የሃይማኖት መሪዎች በሀገሪቱ ሰላም እና አንድነት እንዲሰፍን ጠየቁ

በቺሊ የሚገኙ የበርካታ ሃይማኖታዊ ቤተ እምነት ተወካዮች በቺሊ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት መሪነት የፖለቲካ መሪዎች በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ለመፍታት ትርጉም ያለው የሠላም ድርድር ላይ ገንቢ በሆነ መልኩ እንዲሳተፉ የሚያሳስብ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የበርካታ ሀይማኖት መሪዎች በጋራ ሆነው በሰጡት መግለጫ የሃገሪቱ ብሄራዊ ሚዲያ እንደገለጸው አብዛኛውን የቺሊ ዜጎችን ትልቅ ፍርሃት እና ውጥረት ውስጥ የከተተውን በሀገሪቱ እየተጋረጠ ያለውን የጸጥታ ችግር ለማሳሰብ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

በሰላም እና በአንድነት የመኖር ሀገራዊ ዕሴት ስምምነት አስተዋፅዖ ለማድረግ ባለመው በዚህ መግለጫ ላይ፥ የቺሊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሆነው የሚያገለግሉት የሳንቲያጎ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ፈርናንዶ ቾማሊ ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ ከአንግሊካን፣ ከወንጌላዊያን ህብረት እና ከሀገሪቱ የጴንጤቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛ ተወካዮች እንዲሁም ከአይሁድ እና ከሙስሊም ማህበረሰብ መሪዎች ጋር በመሆን በጋራ ፊርማቸውን አኑረውበታል።

የጸጥታ ችግር እና ሙስና

መግለጫው በቺሊ ያለውን ወቅታዊ የማህበራዊ ሁኔታን የዳሰሰ ሲሆን፥ የእርስ በርስ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመኑ በመምጣታቸው፣ የውይይት መድረኮችን እንደሚያደናቅፍ እና የላቲን አሜሪካን ሀገራትን እያጠቁ ላሉት በርካታ ፈተናዎች መፍትሄ የማግኘት አቅምን ይቀንሳል ብለዋል።

የሃይማኖት መሪዎቹ በሃገሪቱ የግድያ ወንጀሎች መበራከታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር መኖሩን በመጠቆም፥ “የሰው ልጅ ህይወትን መናቅ፣ ለግል ንብረት ዋስትና ማጣት እና ሕግን አለማክበር የተለመደ ነገር ሆኗል” ካሉ በኋላ “በቺሊ ከዚህ በፊት የማይታወቅ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መስፋፋት እና የተደራጁ ወንጀሎች መኖራቸው የሲቪሉን ማህበረሰብ ህይወትን በተለይም የአካባቢያችንን፣ ቤተሰባችንን እና ወጣቶቻችንን ዋና ዋና ነገሮችን እያጠፋ ነው” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።

ፈራሚዎቹ አያይዘውም “በሃገሪቷ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የመንግስት እና የግል አካላትን የሚጎዱ ለቁጥር የሚያታክቱ የሙስና ወንጀሎች፣ ለጋራ ጥቅም የተለየ ኃላፊነት ከተጣለባቸው አካላት ጋር የእምነት ማጉደል ምሳሌ ሆነው በመገኘታቸው ህዝባዊ እምቢተኝነትን አስነስቷል” ብለዋል።

የፖለቲካ ስርዓቱን ለመቀየር የጋራ ጥረት ያስፈልጋል

በ2013 እና በ2015 ዓ.ም. መካከል ቺሊ አዲስ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅ ሁለት ሙከራዎችን አድርጋለች፥ ነገር ግን በዲሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡ ጉባኤዎች የቀረቡት ሁለቱም ረቂቆች ሁለት ጊዜ በተካሄደ ህዝበ ውሳኔዎች ውድቅ ሆነዋል።

የጋራ መግለጫው እነዚህን እና ሌሎች ውድቀቶችን በማጉላት “ሀገራዊ ስምምነት እና እውነተኛ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መውሰድ” እንደሚያስፈልግ፣ እንዲሁም የፓርቲዎችን ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው፥ በሚገጥሙን አሳሳቢ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል” በማለት አረጋግጠዋል።

የቺሊ የሃይማኖት መሪዎች አገሪቷ ወደ "የጋራ መግባባት እና የእድገት ጎዳናዎች" እንድትመለስ ጥሪያቸውን ለሁሉም ዜጎች አቅርበዋል፥ "ለዚህም ታላቅ ግብ" የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
 

15 March 2024, 12:15