ፈልግ

ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ 

ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ

የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል፣ በምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ጊምቢቹ ወረዳ ስር በሚግኙ ቱሉ ፈራ፣ ሃማ፣ ጎሮ-ትግሬ እና ቢሻን ጢኖ ከዲዳ ቀበሌዎች ላይ ‘በቦይንግ ኢንቨስትመንት ፈንድ’ የገንዘብ ድጋፍ በኢትቶጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን የተሰሩ “ኢቲ302” የተሰኘ ስያሜ የተሰጣቸው ከ10 ሺህ በላይ የአከባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተመርቀዋል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እነዚህ የልማት ሥራዎች የተሰሩት፥ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 787 ማክስ 8 የበረራ ቁጥር ET 302 አውሮፕላን ላይ በደረሰ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ 157 ሰዎች መካከል ለ18 ሰዎች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የቦይንግ ኮሚኒቲ ኢንቨስትመንት ፈንድ በሰጠው የ100 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ነው።

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ከደቡብ አፍሪካ ቆይታው በሠላም ወደ አዲስ አበባ የገባው ቦይንግ 737-ማክስ 8 ለሚቀጥለው ግዳጁ ዝግጁ ለመሆን የሦስት ሰዓታት እረፍትና የሞተር ምርመራ አድርጎ ጨርሶ የበረራ ቁጥር ኢቲ302 ተሰጥቶታል።

ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ
ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ

149 መንገደኞቹን በጉያው ሸክፎ ፤ ለደንበኞቹ ያስለመደውን እንክብካቤ ሊከውን ደግሞ 8 የበረራ ሠራተኞቹን ጨምሮ ጉዞውን ወደ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ናይሮቢ፥ ኬንያ አድርጓል። ከጥዋቱ 2 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ሲል የተጀመረው ጉዞ ግን ከ6 ደቂቃ በላይ መዝለቅ አልቻለም።

አየር መንገዱ በወቅቱ ከቦይንግ ካዘዛቸው አዳዲስ ማክስ 8 አውሮፕላኖች ውስጥ በአራተኝነት የገባው እና ሥራ ላይ ከዋለ አራት ወራትን ብቻ ያስቆጠረው ይህ አውሮፕላን 1200 ሰዓታትን ብቻ ነበር የበረረው።

ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ
ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ

ከአዲስ አበባ 62 ኪ.ሜ. በምትርቀዋ በኦሮሚያ ክልል ፥ ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ጊምቢቹ ወረዳ፣ ቱሉ ፈራ እና ሀማ ቁንጥሽሌ ቀበሌዎች አዋሳኝ ላይ ተከሰክሶ አንድም ሰው ሳይቀር የ35 አገራት ዜጎችን የህይወት ቀጥፏል። አውሮፕላኑም ወድቆ ሲከሰከስ በአከባቢው 27 ሜ. ስፋት ፣ 37 ሜ. ርዝመት እና 9.1 ሜ. ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ተፈጥሯል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ከደረሰው አደጋ ቀደም ብሎ አምነው የተሳፈሩትን መንገደኞች አደራ በመብላት የሚታወቀው ቅንጡው አውሮፕላን በኢንዶኔዢያው ‘ላየን ኤየር’ አየር መንገድ ተመሳሳይ ቦይንግ አውሮፕላን ላይ አደጋ አጋጥሞ የ181 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።

ስለ ፕሮጄክቶቹ

ይህ በእንዲህ እያለ ነው የቦይንግ ኩባኒያ ለተጎጂ ቤተሰቦች የሚሆን ገንዘብ መድቦ እያንዳንዱ የተጎጂ ቤተሰብ በሚፈልገው እና በሚመርጠው ነገር ላይ እንዲያውለው ብሎ መመሪያ ያወጣው።

በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በቀለ ሞገስ አጠቃላይ ስለዚህ ፕሮጄክት አጀማመር እና አተገባበር ሲገልጹ ፥ የቦይንግ ኩባኒያ አደጋው በደረሰ ከሁለት ዓመት በኋላ ‘ቦይንግ ኮሚኒቲ ኢንቨስትመንት ፈንድ’ (Boing Community Investment Fund) የተባለ የተጎጂ ቤተሰቦችን ለማገዝ የሚውል ብር መድቦ እያንዳንዱ የተጎጂ ቤተሰብ በሚፈልገው ቦታ እና ዘርፍ ተጎጂዎችን ለማስታወስ የሚረዳ እና የአከባቢውን ማህበረሰብ ሊጠቅም የሚችል ፕሮጀክት ቀርፀው እንዲያመጡ ይጠይቃል፥

ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ
ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጄክቶች ተመረቁ

በዚህም መሰረት ከ18ቱ የተጎጂ ቤተሰቦች መሃል 4ቱ የካቶሊክ ዕርዳታ ድርጅት (CRS) ባልደረባ ስለነበሩ እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በምትሰራቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ምክንያት የካቶሊክ የዕርዳታ ተቋም የሆነውን ሲ አር ኤስን ይመርጣሉ፥ ሲ አር ኤስ ደግሞ ለትግበራው በአቶ በቀለ ሞገስ የሚመራውን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማህበራዊ ልማት ኮምሽንን ይመርጣል።

ይህም ኮሚሽን አደጋው በደረሰበት አከባቢ ማህበረሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ ሥራዎችን ለመስራት ምን ምን ያስፈልጋል የሚሉትን ነጥቦች በመያዝ ጥናት ሲያካሂድ ፥ አከባቢው ምንም እንኳ ለም ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ በልማት እንዳልጎለበተ ፣ ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳለ ፣ ልጆቻቸው የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች ከጭቃ የተሰሩ እና ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ ስላልነበረ እና ልጆቹ ከሚኖሩበት አከባቢ በጣም ስለሚርቅ ፣ የአከባቢው ማህበረሰብ ሲታመምም ሆነ ለወሊድ የሚሆን ምንም አይነት የጤና ተቋም በአከባቢው አለመኖሩን እና የመሳሰሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉ ከአከባቢው ማህበረሰብ ፣ ከተጎጂው ቤተሰብ ፣ ከከተማው እና ከወረዳው አስተዳዳሪዎች ጋር በመሆን በተገኘው ፈንድ ምን መስራት ይቻላል የሚለዉን በጋራ በመወያየት ሁለት ትምህርት ቤቶችን፣ አንድ ዘመናዊ የጤና ኬላ፣ ሶስት የመጠጥ ዉሃ ቦኖዎችን እንዲሁም መለስተኛ የመሸጋገሪያ ድልድዮችን በመስራት ለአገልግሎት ዝግጁ አድርገዋል።   የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመጀመሪያ ደረጃ ለዚህ ሥራ የተመረጠችበት ዋና ምክንያት እንደሚታወቀው ቤተክርስቲያኒቷ በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች በትምህርት ፣ በጤና ፣ በምግብ ዋስትና ፣ በሴቶች እና ህፃናት እንዲሁም በስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች እና በተያያዙ ዘርፎች ላይ ተሰማርታ የብዙዎችን ህይወት እየቀየረች እንደሆነ እሙን ነው ፥ በዚህም ምክንያት ይላሉ አቶ በቀለ ቤተክርስቲያኒቷ የእምነቷ መሰረቶች አንዱ በሆነው በልግስና ስራ ላይ በመሰማራቷ ፣ ፕሮጄክቶችን በታቀደው እና በታለመው ዕቅድ መሰረት ፈጥና ስለምትጨርስ ፣ ሰፊ የሆነ ህዝብ በዓመት ውስጥ ስለምትዳረስ (በ2015 ዓ.ም. ብቻ 7.9 ሚሊዮን ህዝብ ተደራሽ አድርጋለች) እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።

እነዚህ ምክኒያቶች ናቸው እንግዲህ በ 18ቱ ተጎጂ ቤተሰቦች ዘንድ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን ተቀዳሚ ተመራጭ እንድትሆን በአንድ ልብ ያስመረጣቸው እና የልማት ሥራዎቹን እንድትሠራ ያስደረገው።

በምርቃቱ መርሃ ግብር ላይ ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕረዚዳንት፣ ብጹእ አቡነ ሉቃስ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ እና የእምድብር ሃገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች፣ የአደጋው ሰለባ ቤተሰቦች፣ አቶ በቀለ ሞገስ የኢትቶጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የማህበራዊ እና ልማት ኮሚሽን ሃላፊ፣ የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት ‘ሲ አር ኤስ’ ተወካዮች፣ ከተለያዩ ሃገረስብከቶች የመጡ ካህናት እና ገዳማዊያት፣ የፌዴራል ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ተወካይ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካይ፣ የኦሮሚያ ክልል የትምህርት የውሃ የጤናና የመንገድ ቢሮ ተወካዮች፣ የምስራቅ ሸዋ ዞን እና ወረዳዎች ተወካዮች፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና በሺዎች የሚቆጠሩ የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

08 March 2024, 16:37