ፈልግ

የሄይቲ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ ስልጣን እንዲለቁ በፖርት ኦ ፕሪንስ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የሄይቲ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንሪ ስልጣን እንዲለቁ በፖርት ኦ ፕሪንስ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ  (ANSA)

የሄይቲ ሊቀጳጳስ ብጹእ አቡነ ሜሲዶር ሄይቲ የእርስ በርስ ጦርነት አፋፍ ላይ ነች አሉ

በሄይቲ ባለፈው ሳምንት ታጣቂ ወረበሎቹ እስር ቤት ሰብረው በርካታ እስረኞችን ካስፈቱ በኋላ ሃይላቸውን በማጠናከራቸው ሃገሪቷ ወደ ከባድ ብጥብጥ እየገባች ባለችበት ወቅት፥ የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ሀገሪቱ በአደገኛ ሁኔታ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እየተጓዘች መሆኗን በማስጠንቀቅ፥ የወረበሎቹ ጥቃት ቤተክርስቲያኗን በእጅጉ እየጎዳ ነው ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ሃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ባለፈው ሳምንት ታጣቂ ወረበሎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ስልጣን እንዲለቁ በመጠየቅ ቁልፍ የሆኑ የመንግስት ተቋማትን እና ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ሄይቲ ወደ ከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ ገብታለች።

ጠቅላይ ሚኒስተር ሄንሪ የሄይቲን ወንጀለኞች ለማስቆም የሚችል ዓለም አቀፍ ሃይል ለማግኘት ኬንያ በነበሩበት ወቅት፥ በሁከትና ብጥብጥ የተመሰቃቀለችው ሀገር ባለፈው እሁድ የታጠቁ ቡድኖች በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ከእስር ቤት ካስለቀቁ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ገብታለች።

ባለፈው የካቲት 29 አርብ ዕለት በዋና ከተማዋ ፖርት-ኦው ፕሪንስ በሚገኘው የሄይቲ ብሔራዊ ቤተ መንግስት አቅራቢያ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን እና ሌሊት ላይ ደግሞ በርካታ የፖሊስ ጣቢያዎች እና የመንግስት ህንጻዎች ላይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ሄንሪ በሚቀጥለው ዓመት ነሀሴ ወር ላይ ምርጫ ለማካሄድ ቃል ገብተዋል የሚለውን ዜና ተከትሎ በሃገሪቷ በተከሰተው ታይቶ የማይታወቅ ብጥብጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሽባ አድርጓል፣ ብሎም የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት በእጅጉ ቀንሷል።

በአሁኑ ጊዜ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች በሄይቲ ውስጥ ታግተው እንደሚገኙ እና በከበባ ውስጥ ያለችውን ሀገር ለቀው መውጣት እንዳልቻሉ ተነግሯል።

ወረበሎቹ “የተደራጀ ሠራዊት” ሆነዋል

የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ሆነው የሚያገለግሉት የፖርት ኦው ፕሪንስ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ማክስ ሜሲዶር ሀገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለመግባት አፋፍ ላይ ናት ብለዋል።

ችግር ላይ ያሉትን ቤተክርስቲያናት የሚረዳው ‘ኤ ሲ ኤን’ ለተባለ ጳጳሳዊ ተቋም እንደተናገሩት፥ የሄይቲ የፖሊስ ሃይሎች “የተደራጀ ሰራዊት” እየሆኑ በመጡት እና በደንብ የታጠቁ ወረበላ ቡድኖች አንፃር ሲታዩ አቅመ ቢስ እንደሆኑ እና እነሱን ለመዋጋት ከሲቪሉ ማህበረሰብ ውስጥ የታጠቁ ቡድኖች መፈጠሩን ተናግረዋል።

ምንም እንኳን በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ችግሩ የከፋ ቢሆኑም፥ በዋና ከተማዋ ፖርት-ኦው-ፕሪንስ ግን “ምንም አስተማማኝ የሆነ ቦታ እንደሌለ” ብጹእ አቡነ ሜሲዶር ተናግረዋል።

የሄይቲን ህዝብ እያሰቃየ ያለው እገታ

ታጣቂ ቡድኖቹ ከሚያጠቋቸው እና እየተስፋፋ የመጣውን የእገታ ተግባር ከሚፈፅሙባቸው ዋና ዋና ኢላማዎች መካከል ቤተክርስቲያኒቱ አንዷ መሆኗን ብጹእነታቸው በማረጋገጥ፥ ታጣቂ ወረበሎቹ የሚፈጽሙት እገታዎች “የሄይቲን ህዝብ እያስጨነቀ ያለ ተግባር ሆኗል” ብለዋል።

“በየቦታው አፈናዎች አሉ… ሀብታምም ሆነ ድሀ፣ ምሁርም ሆነ መሃይም፣ ማንኛውም ሰው ሊታገት ይችላል። ይህ ክፉ ተግባር ነው፥ ሁላችንም በጋራ ልንታገለው የሚገባ ድርጊት ነው” በማለት የድርጊቱን አስከፊነት ተናግረዋል።

ብጹአን ጳጳሳት በጋራ ይመሰክራሉ

ለሄይቲ ጳጳሳት በተለይም እንደ ዋና ከተማ ፖርት-ኦው-ፕሪንስ ባሉ የወሮበሎች ቡድን ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች በህይወት መቆየት በጣም ከባድ ሆኗል፥ “ነገር ግን፣” ይላሉ ብጹእ አቡነ ሜሲዶር “አንድ ላይ ለመሥራት እና ለመመስከር እንሞክራለን፥ ይህ ቀላል አይደለም፥ ነገር ግን በተለይ በዚህ የዐብይ ጾም ወቅት መስቀላችንን ተሸክመን ክርስቶስን መከተል አለብን” ብለዋል።

ሁከቱ በሄይቲ የካህናት እና የአማኞች ሃዋሪያዊ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፣ ሁሉም ሰው በከፍተኛ ፍርሀት ውስጥ ስለሚኖር አንዳንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ለመዘጋት ተገድደዋል። ይሄንን በማስመልከት “አብዛኛዎቹ መንገዶች ስለተዘጉ እኔ ራሴ የሀገረ ስብከቴን ሁለት ሦስተኛውን መጎብኘት አልቻልኩም” ሲሉ ብጹእ አቡነ ሜሲዶር ተናግረዋል።

ህዝባችን መኖር ይፈልጋል

ምንም እንኳን ችግሮች እና አደጋዎች ቢኖሩም፥ የሄይቲ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ጥንካሬን በማሳየት ስራውን ቀጥሏል። “ህዝባችን መኖር ይፈልጋል” ያሉት ጳጳሱ፣ በሄይቲ ውስጥ ያለው የቤተክርስቲያኑ ዋና ተልእኮ ተስፋን ህያው ማድረግ እና ሰዎችን በተለይም ወጣቶችን ተስፋ እንዳይቆርጡ ማበረታታት እንደሆነ ገልጸዋል።

የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ቃለ ምልልሱን ሲያጠቃልሉ፥ ያለ ኤ ሲ ኤን እርዳታ የሄይቲ ቤተክርስቲያንን ህልውና ማስቀጠል በጣም ከባድ እንደሆነ በመግለጽ፥ ምክንያቱም ብዙ የሄይቲ ደብሮች ተግባራቸውን ለማስቀጠል በገንዘብ እጥረት ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል።

ኤ ሲ ኤን በሄይቲ የሚገኘውን ቤተክርስትያን ደግፏል

በዓለም ዙሪያ ስደት የሚደርስባቸውን ክርስቲያኖች የሚደግፈው ይህ ጳጳሳዊ ተቋም ባለፈው ዓመት ብቻ በአገሪቱ ውስጥ የሚሰሩ 60 የሚያህሉ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ ደግፏል።

እነዚህ ፕሮጄክቶች ለስነ መለኮት ተማሪዎች፣ ለገዳማዊያን፣ ለካቴኪስቶች እና ለምእመናን የሥልጠና ኮርሶችን መስጠትን ያካትታሉ። በተጨማሪም የወጣቶች ሃዋሪያዊ ሥራ ተግባራትን በማገዝ እና ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ለተገደዱ ሰዎች እርዳታ መስጠት፣ ለሶስት የሀገረ ስብከት ሬዲዮ ጣቢያዎች መሳሪያዎችን በማሟላት፣ ለሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ እና የፖርት-ኦው-ፕሪንስ ሃገረ ስብከት የፀሐይ ፓነሎች መትከልን ጨምሮ ለመነኮሳት የድንገተኛ ጊዜ እርዳታ መስጠትን በመሳሰሉት ተግባራት ላይ ተሳትፏል።
 

11 March 2024, 13:09