ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤   (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ የፍቅር ተሐድሶ

በአሁኑ ጊዜ ረጅም ዕድሜ ሲባል የባለ ትዳሮች ጥብቅ እና ልዩ ፍቅራዊ ግንኙነቶች ለአራት፣ ለአምስት ወይም ለስድስት አሥርተ ዓመታት መዝለቅ እንዳለባቸው አመላካች ነው። በመሆኑም የመጀመሪያው ውሳኔ የጋብቻ ፍቅር በየጊዜው መታደስ ይኖርበታል። ከጥንዶቹ አንዱ ለሌላው ጥልቅ የሆነ ወሲባዊ ፍላጎት ባይኖረውም እንኳ እርሱ ወይም አንዳቸው የአንዳቸው የመሆናቸውን ደስታ ሊያጣጥሙና በሕይወት ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚካፈልላቸው “አጋር” እንዳላቸው እንጂ ማናቸውም ቢሆኑ ብቸኛ ያለመሆናቸውን ግንዛቤ ሊያዳብሩ ይችላሉ። እርሱ ወይም እርስዋ በሕይወት ጉዞ ላይ አብሮ ተጓዥ፣ የሕይወትን ችግሮችና ከሕይወትም የሚገኘውን ደስታ ተካፋይ ናቸው። ይህ እርካታ ለጋብቻ ፍቅር የተገባ የመዋደድ አካል ነው። ዕድሜ ልክ ተመሳሳይ ስሜት ይኖረናል የሚል ዋስትና የለም። ሆኖም ባልና ሚስት የሚጋሩት ለዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ዕቅድ ካላቸው እርስ በርስ መዋደድና ሞት እስኪለያቸው ድረስ ገንቢ ቅርበት ፈጥረው በአንድነት መኖር ይችላሉ። እነርሱ ቃል የሚገቡት ፍቅር ከማናቸውም ጥልቅ ስሜት ወይም እነዚህን ሁሉ ከሚያካትት የአስተሳሰብ ሁኔታ የላቀ የቤተሰብ ጉዳይ ጥምረቶች ነው። ጥልቅ ፍቅርና ልባዊ የሆነ የዕድሜ ልክ ውሳኔ ነው። ያልተፈቱ ግጭቶችና የሚያደናግሩ ስሜታዊ ሁኔታዎች ቢኖሩም ጥንዶቹ የመውደድ፣ አንዳቸው የአንዳቸው የመሆን፣ ሕይወታቸውን የመጋራት እንዲሁም በፍቅራቸውና በይቅርታቸው የመቀጠል ውሳኔአቸውን በየዕለቱ ያድሱታል። እያንዳንዳቸው በራስ የዕድገትና የሕንጸት ጎዳና ወደ ፊት ይራመዳሉ። በዚህ ጉዞ ላይ ፍቅር በእያንዳንዱ እርምጃና አዲስ ደረጃ ደስታን ያገኛል።

በማንኛውም የጋብቻ ሂደት ውስጥ አካላዊ ገጽታዎች ይቀየራሉ። ይህ ማለት ግን ፍቅርና መተሳሳብ ይደበዝዛል ማለት አይደለም። ሌላውን ሰው የምንወደው በአካሉ ማማር ሳይሆን በማንነቱ ነው። ሰውነት ቢያረጅም፣ ልባችንን የሰረቀውን የመጀመሪያ ማንነቱን አሁንም ያሳያል። ሌሎች ያንን ውበት ማየት ቢሳናቸውም የትዳር አጋር ግን በፍቅር ዐይን ማየቱን ስለሚቀጥል የእርሱ ወይም የእርስዋ ፍቅር አይቀንስም። እርሱ ወይም እርስዋ አንዱ የሌላው መሆናቸውን ዳግመኛ ያረጋግጣሉ። ያንንም ምርጫ በታማኝነትና በፍቅራዊ ቅርበት ይገልጹታል። እነርሱም የጋብቻ ተልዕኮአቸውን ሲፈጽሙ የዚህ ምርጫ ክቡርነት በጥልቀቱና በስፋቱ ለአዲስ ዐይነት ስሜት ያነሣሣቸዋል። ምክንያቱም “እንደ ሰው በሌላ ሰው የሚቀሰቀስ ውስጣዊ ስሜት… በራሱ ወደ ወሲባዊ ድርጊት አያመራም”። ሌላ ትርጉም ያላቸው መገለጫዎችም ይኖሩታል። በእርግጥ ፍቅር “ብቸኛ እውነታ ቢሆንም የተለያዩ ገጽታዎች ያሉትና በተለያዩ ጊዜያት አንዱ ወይም ሌላው ገጽታው ይበልጥ ጎልቶ ሊወጣ የሚችል ነው”። የጋብቻ ትስስር አዲስ መገለጫዎች ይኖሩታል። በቀጣይነት እንዲጠነክርም አዳዲስ ዘዴዎች ያስፈልጉታል። እነዚህም ዘዴዎች ትስስሩን ለመጠበቅም ለማጠንከርም የሚረዱና የየዕለት ጥረትን የሚጠይቁ ናቸው። ሆኖም ይህ ሁሉ ሊሳካ የሚችለው ጸጋውን እንዲያፈስ፣ በእያንዳንዱ አዲስ ሁኔታ ውስጥ ፍቅራችንን እንዲያጸና፣ እንዲመራና እንዲያድስ መለኮታዊ ብርታቱንና መንፈሳዊ እሳቱን እንዲያወርድ ወደ መንፈስ ቅዱስ ስንጸልይ ነው።

ፍሬያማ የሆነ ፍቅር

ፍቅር ምን ጊዜም ሕይወትን ይሰጣል። የጋብቻ ፍቅር “በባልና ሚስት አያበቃም… ባልና ሚስት ራሳቸውን ለእርስ በርሳቸው ሲሰጣጡ የሚሰጣጡት ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የእነርሱ የፍቅር ሕያው መገለጫዎች፣ የጋብቻ አንድነታቸው ምልክትና አባትና እናት ለሚያደርጋቸው ሕያውና የማይነጣጠል ውህደት ምሳሌ የሚሆኑ ልጆች የማፍራት እውነታን ጭምር ነው”።

አዲስ ሕይወትን በደስታ መቀበል

ቤተሰብ አዲስ ሕይወት የሚወለድበት ብቻ ሳይሆን ያንን አዲስ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ስጦታ የሚቀበሉበት ዐውድ ነው። እያንዳንዱ አዲስ ሕይወት “ሁሌም ያስገርመናል፤ ነጻ የሆነውን የፍቅር ገጽታንም እንድናደንቅ ያደርገናል። አስቀድሞ የመወደድ ድንቅ ውበት ነው፤ አዎን ሕጻናት ገና ከመወለዳቸው በፊት ይወደዳሉ”። ስለሆነም እዚህ ላይ ምን ጊዜም ቅድሚያ የሚሰጠውን የእግዚአብሔርን ቀዳሚ የፍቅር ነጸብራቅ እናያለን፤ ምክንያቱም ሕጻናት “ገና የሚወደዱበትን አንዳች ነገር ሳያደርጉ እንዲሁ ይወደዳሉና”። ሆኖም፣ “ከሕይወታቸው የመጀመሪያ ሰዓታት አንሥቶ ብዙ ልጆች ተቀባይነትን አያገኙም። ይጣላሉ፣ የልጅነትና የወደ ፊት ተስፋቸውን ይሰረቃሉ። አንዳንዶች የራሳቸውን ትክክለኛነት ለማሳየት ሲሉ እነዚህን የመሰሉ ሕጻናት ወደዚህች ዓለም ማምጣት ስሕተት ነው በማለት በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ይህ አሳፋሪ ነው! … “በጎልማሶች ስሕተት ሕጻናትን እንዲህ የምንቀጣ ከሆነ ሰብዓዊ መብቶችንና የሕጻናትን መብቶች ስለማክበር እንዴት መለፈፍ እንችላለን?” አንድ ሕጻን በማይፈለጉ ሁኔታዎች ወደዚህች ዓለም ሲመጣ ወላጆችና ሌሎች የቤተሰብ አባላት ያንን ሕጻን እንደ እግዚአብሔር ስጦታ አድርገው ለመቀበል የሚቻለውን ሁሉ ማድረግና እርሱንም/እርስዋንም በሙሉ ልብና በፍቅር የመቀበል ኃላፊነት መውሰድ ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም “ወደዚህች ዓለም ስለሚመጡ ሕጻናት ሲነገር ሕጻኑ በስሕተት የተወለደ፣ ወይም ዋጋ ቢስ እንደ ሆነ ወይም ለአራቱም ነፋሳትና ለሰው ልጅ እብሪት የተተወ መስሎ እንዳይሰማው ከተፈለገ የጎልማሶች መሥዋዕትነት በወጪም መጠንን እጅግ የበዛ ነው ተብሎ ሊታሰብ አይገባም”። ጌታ ለአባትና ለእናት የሚሰጠው የአዲስ ልጅ ስጦታ የሚጀምረው በመቀበል ሲሆን፥ የዕድሜ ልክ ጥበቃ በማድረግ ይቀጥላል። የመጨረሻ ግቡም የዘላለማዊ ሕይወት ደስታ ነው። የእያንዳንዱን ሰው የመጨረሻ ስኬት በጽናት በማሰላሰል ወላጆች ስለ ተሰጣቸው ክቡር ስጦታ ይበልጥ ግንዛቤ ይኖራቸዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ራሱ ልጃቸው ለዘላለም የሚጠራበትን ስም እንዲመርጡለት ለወላጆች ዕድሉን ይሰጣቸዋል።

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ፥ “ጋውዲዩም ኤት ስፔስ” የተሰኘ ስለ ዘመናዊ ቤተ ክርስቲያን የወጣ ሐዋርያዊ ሠነድ ቁ. 51 “የሰው ሕይወትና እርሱንም የማስተላለፍ ትርጉሙ በዚህ የሕይወት አድማስ ብቻ የተገደቡ እውነታዎች አይደለም፤ የዚህንም እውነተኛ ግምገማና ሙሉ ትርጉም መረዳት የሚቻለው ከዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችን አንጻር ብቻ ነው”።

ብዙ አባላት ያሏቸው ቤተሰቦች ለቤተ ክርስቲያን ደስታና የፍቅር ፍሬያማነት መገለጫ ናቸው። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በትክክል እንዳብራሩት፥ ኃላፊነት የሚሰማው ወላጅነት ማለት “ያልተገደበ ተዋልዶ ወይም ልጆችን በማሳደግ ረገድ ያለውን እውነታ አለመረዳት ሳይሆን ባልና ሚስት የማይጣስ ነጻነታቸውን በማስተዋልና ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ እንዲጠቀሙ፣ ማኅበራዊና የሕዝብ ብዛት እውነታዎችን እንዲሁም የራሳቸውን ሁኔታና ተገቢ ምኞቶች ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ማብቃት ነው”።

ምንጭ፡- ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሥ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 164-167 ላይ የተወሰደ።

02 March 2024, 17:07