ፈልግ

ከቱርክ ብጹዓን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት ከቱርክ ብጹዓን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለቤተ ክርስቲያን ላሳዩት ፍቅር የቱርክ ጳጳሳት ምስጋናቸውን አቀረቡ

የቱርክ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ አቡነ ማርቲን ክሜተክ በቫቲካን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። ብጹዕ አቡነ ማርቲን የካቲት 1/2016 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተው በአገራቸው ውስጥ በሚታዩ አንዳንድ ችግሮች እና በወደ ፊት ተስፋዎች ላይም ተወያይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢስታንቡል ከተማ በምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ እሑድ ጥር 19/2016 ዓ. ም. ጥቃት ከተፈጸመባቸው ወዲህ ምእመናኑ በፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው ሽብር ከሚያስከትለው አደጋ መውጣት አለብን ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ማርቲን ክሜተክ በማከልም እንደ ጎሮግሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ ካስከተላቸው ቁስሎች ለመፈወስ ቤተ ክርስቲያን ቁርጠኛ ሆና እየሠራች እንደምትገኝ አስረድተዋል።

ብጹዕ አቡነ ማርቲን ከቱርክ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር የካቲት 1/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተገናኝተው፥ ቅዱስነታቸው በቱርክ ለምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናን ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በቱርክ የሰምርኔስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና የቱርክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ አቡነ ማርቲን ቅዱስነታቸው ለቱርክ ቤተ ክርስቲያን ለሰጡት ትኩረት እና ላደረጉት እንክብካቤ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በቱርክ ውስጥ በሚታዩ አንዳንድ ችግሮች እና ተስፋዎች ላይም ውይይት አድርገዋል።

ጥልቅ ውይይት አድርገዋል

የቱርክ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በቫቲካን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ከሞላ ጎደል ሁሉንም የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶችን ጎብኝተው፥ ከምክር ቤቱ አባላት ጋር ባደረጓቸው ስብሰባዎች በኩል በቱርክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አወንታዊ ምልክቶችን ለማሳወቅ መቻላቸውን ብጹዕ አቡነ ማርቲን ገልጸዋል።

በርካታ የሙስሊም ማኅበረሰብ በሚገኝባት የምዕራብ እስያ አገር ቱርክ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 0.07 በመቶ የሚሆንነውን የአገሪቱን ሕዝብ እንደምትወክል ያስታወሱት ብጹዕ አቡነ ማርቲን፥ በአገሪቱ የሚገኙ የካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር አናሳ ቢሆንም በጥንት የክርስትና ምድር ውስጥ መገኘታቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ድፍረት እና ተስፋ

በሰሜን ኢስታንቡል በምትገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ እሑድ ጥር 19/2016 ዓ. ም. በተፈጸመው ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት ከጠፋ ወዲህ በምእመናን መካከል ፍርሃት እየጨመረ መምጣቱ ሳይሸሽጉ የተናገሩት የቱርክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት አቡነ ማርቲን፥ የወንጀል ድርጊቱ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ክርስቲያኖች በሙሉ ለማሸበር የተፈፀመ እንደ ነበር ገልጸዋል።   

በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ካቶሊካዊ ምዕመናን ማኅበረሰቦች በከፍተኛ ጭንቀት እና ፍርሃት ውስጥ ሊቆዩ እንደማይችሉ እርግጠኛ በመሆን ተናግረው፥ ሕይወት በድፍረት እና በተስፋ መቀጠል እንዳለበት ብዙ ጊዜ ደጋግመው መናገራቸውን ገልጸዋል። የምዕመናኑ የወደ ሕይወት አስደሳች በሆኑ ሚስዮናዊ ሃሳቦች የተሞላ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ማርቲን፥   በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልዩልዩ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ብዙ ዕድሎች መኖራቸውን እና ሁሉንም ነገር በታላቅ ትሕትና እና መረጋጋት ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል።

መልሶ ግንባታ እና አዲስ ተግዳሮት

የቱርክ ቤተ ክርስቲያን ሌሎች ፈተናዎችን ለመቋቋም ጥረት ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ማርቲን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. በሶርያ ወጥስም የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንዳጠፋ አስታውሰው፥ ይህን ቁስል ለመፈወስ በቱርክ እና አናቶሊያ ውስጥ የሚገኝ “ካሪታስ” የተሰኘ ካቶሊካዊ ዕርዳታ አድራጊ ድርጅት እንደየ አቅማቸው በችግር ውስጥ የሚገኙትን ለመርዳት ሁሉን እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የአስክንደሩን ካቴድራል ጨምሮ አደጋ የደረሰባቸውን አብያተ ክርስቲያናት መልሶ ለመገንባት አስፈላጊ የሆኑ የአሠራር መንገዶችን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ እና ከባለሥልጣኖቻቸው ጋር በመተባበር ለሁሉም ሰው አጥጋቢ መፍትሔ እንደሚገኝ ያላቸውን እርግጠኝነት የቱርክ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ አቡነ ማርቲን ክሜተክ ገልጸዋል።

12 February 2024, 16:30