ፈልግ

ኪዳነ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት  (Copyright (c) 2017 Renata Sedmakova/Shutterstock. No use without permission.)

ኪዳነ ምሕረት

«ኪዳንሽ በኃጥአተኞች ላይ ሆነ፣ ኪዳንሽ ለእኛ ለኃጢአተኞች የደነንነት ተስፋ ነው´ እያልን ዛሬ እመቤታችንን እናመሰግናት። ይህ ቀን ለማርያም ክብር ለእኛ ለአዳም ልጆች ደግሞ ተስፋ እና ደስታ ነው። ዛሬ በልባችን የምንሰማው የምሥራች የደኀንነትና የምሕረት ተስፋ ነው።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ኪዳነ ምሕረት ከታላቁ የማርያም ስም አንዱ ነው። ክብርና ጸጋን የሚያመለክት ነው። ኪዳነ ምሕረት የእምቤታችን ማርያም የደኀንነት መሰላል የአምላክ እና የሰው መገናኛ ማለት ነው። እግዚአብሔር አዳምን ሲፈጥረው ከመጀመሪያ አንስቶ ከሁሉ ግዙፍ ፍጥረት አስበልጦ እና ከፍ አድርጐ በታላቅ ግርማና ሞገስ አጊጦ ፈጠረው። በመልኩ ፈጠረው ነገር ግን ሰው ክብሩንና ማዕረጉን ደረጃውንም አላወቀም። 

ፈጣሪው በሰው ጸጋ አላመሰገነም፣ ሊያውቀውና ሊታዘዘው አልፈለገም እንጂ እንደ እርሱ ጌታ፣ እንደ እርሱ እሆናለሁ የሚል የትዕቢት መንፈስ አሳደረበት። ውጤቱስ ምን ሆነ፣ መዓት ቁጣ ወረደበት፣ ትዕቢትን የሚጠላ አምላክ አዳምን በፍጥነት በትዕቢቱ እጅግ አዝኖ በብርቱ ቀጣው። በዚህ ትልቅ ቅጣት የነበረውን ግርማና ሞገስ ገፈፈው፣ ሀብትና ሽልማቱን ሁሉ መልሶ ወሰደበት። ከሁሉ የባሰና የከፋ ደስ ከሚያሰኝ አትክልት ምድረ ገነት አባረረው። አዳም በገዛ ራሱ ባመጣው መጥፎ ዕድሉ አለቀሰ፣ «አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ´ (ዘፍጥረት 3፡19) እያለ ከንቱነቱን አሳወቀው፣ አዳም ብቻውን ባዶ እጁን ቀረ፣ በስጋት ተጐዳ። አንቺ ማርያም ከገነት በተባረረ ጊዜ ተስፋው ነሽ አዳም ከምድረ ገነት ሲባረር አንቺ የእርሱ ተስፋ ነበርሽ። እግዚአብሔር አዳምን በጭራሽ አልጨከነበትም። ምንም እንኳ ቀድሞ እውነተኛ ፈራጅ በመሆኑ ቢቀጣውም በታላቅ ምሕረት ተመለከተው። ነቢያት በጊዜያቸው ለአዳም ልጅ «አይዞ ተስፋ አትቁረጥ፣ የብርሃን ቀን ሊመጣ ነው አዳኝ መድኃኒት የምትወልድልን የተባረከች የአዳም ዘር ትመጣለች´ እያሉ የደኀንነት ተስፋ ሰጡት። ይህች የአዳም ተስፋ እመቤታችን ናት፤ እግዚአብሔር ማርያምን ለሰው ልጆች የደኀንነት ተስፋ እንደትሆን መረጣት። በዚህም ኪዳነ ምሕረት ተብላ ትጠራለች። አምላክ በፈለገው ቀን ይህች የተባረከች የአዳም ተስፋ ብቅ አለች።

ማርያም በእግዚአበሔር ጸጋ ተከባ አጊጣ የተወለደች እንደገና እግዚአብሔር በወሰነው ቀንና ጊዜ እመቤታችን ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ያን ዓለም ይጠብቀው የነበረው አዳኝ ወለደች። ኢየሱስ የእግዚአብሔርና የማርይም ልጅ በዕፀ መስቀል ላይ ስለ እኛ ተሰቀለ። በሕይወቱ መስዋት ሁላችንን አዳነን፣ ከአባቱ ጋር አስታረቀን። ኪዳነ ምሕረት በርኀሩኀ ሕሊና በተወደደው ልጇ ሕማማትና ሞት ዋጀችን፣ ቤዛችን ሆነች። በዚህ ደግሞ የዓለም ቤዛ ተባለች። ርኀርኀት እናታችንን ኪዳነ ምሕረትን እንመልከት እናስብ።

እግዚአብሔር እንዴት ያለች ርኀርኀት ሰማያዊት እናት እንደሰጠን አስተውለን በመንፈስ አንደበት ኪዳነ ምሕረት እንዴት አድርጋ እንደምትወደን እንደምታስብልን እናታችን የደኀነነታችን ዋስትና በመሆንዋ በታላቅ ተስፋ በእርሷ እንማጠን። ጭንቃችንን እናዋያት፣ እንንገራት፣ ዕርዳታዋንም እንለምን፣ ሳትሰማንም አትቀርም፤ ይህ እምነትና ተስፋ እውነት ነው።

 

24 February 2024, 11:58