ፈልግ

ጳጳስ ክላውዲዮ ጁሊዮዶሪ በዶዶማ ከተማ ከልጆች ጋር ሆነው ጳጳስ ክላውዲዮ ጁሊዮዶሪ በዶዶማ ከተማ ከልጆች ጋር ሆነው 

የጣሊያን ጳጳሳትና የጄሜሊ ሆስፒታል በጋራ በታንዛኒያ የወሊድ እንክብካቤ ድጋፍ እየሰጡ ነው ተባለ

እ.አ.አ. በ 1921 በሚላን ከተማ የተመሰረተው የጣሊያን የግል የምርምር ዩኒቨርሲቲ የሆነው ልበ ቅዱስ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ እና በሮም የሚገኘው ጄሜሊ ሆስፒታል በጋራ ሆነው በታንዛኒያ ሃገር ዶዶማ ከተማ ውስጥ ለእናቶች የማህፀን ህክምና እና የወሊድ አገልግሎት የሚሰጥ የጤና እንክብካቤ ክሊኒክ በማቋቋም ላይ እንደሆኑ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ (CEI) በታንዛኒያ ውስጥ ለነፍሰ ጡር ሴቶች የወሊድ እንክብካቤን ለማቅረብ እየሰራ ለሚገኘው ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

ከልበ ቅዱስ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የተወጣጡ በርካታ ተወካዮች እና የአጎስቲኖ ጄሜሊ ዩኒቨርሲቲ ፖሊ ክሊኒክ ፋውንዴሽን ተወካዮች በጋራ በመሆን ከጥር 18 እስከ 27 2016 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በዶዶማ ከተማ የሚገኘውን የወደፊቱን ክሊኒክ እየጎበኙ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ፕሮጀክቱ በምስራቅ አፍሪካ ማህበራዊ እና ጤና እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማሳደግ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ከፍተኛ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ከሚደረገው ሰፊ ፕሮጀክት አንዱ አካል እንደሆነም ተነግሯል።

ተልዕኮው በዶዶማ የሚገኘውን የቅዱስ ጌማ ሆስፒታልን የማማከር እና የማሰልጠን ስራን ለማሻሻል ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።

ይህ ፕሮጄክት የቀዶ ጥገና ክፍል እና የማዋለጃ ክፍልን ጨምሮ አዲስ የእናቶች ክፍል ግንባታን እንደሚያጠቃልል ተብራርቷል።

በፕሮፌሰር አንቶኒዮ ላንዞን የሚመራው የጄሜሊ ፋውንዴሽን የማህፀን ሕክምና እና የማዋለድ ሕክምና ክፍል ለተቋሙ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል።

የጣሊያን ጳጳሳት ድጋፍ

በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ረዳት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ክላውዲዮ ጁሊዮዶሪ የልኡካን ቡድኑን እየመሩ ያሉ ሲሆን፥ ቡድኑ የማህፀን ስፔሻሊስቶችን እና የጄሜሊ ፋውንዴሽን የቴክኒክ፣ አይሲቲ እና የጤና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፎች ባለሙያዎችን ያካተተ እንደሆነም ተገልጿል።

ከዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት፣ ብጹእ አቡነ ጁሊዮዶሪ ከ2000ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በቅዱስ ጌማ ሆስፒታል ልማት ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን፥ በተጨማሪም በጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ የሚደገፉ የቀድሞ የታንዛኒያ ፕሮጀክቶችን ይቆጣጠሩ እንደ ነበር ተመላክቷል።

ለፕሮጀክቱ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ የሚገኘው የጣሊያን ግብር ከፋዮች ከሚያገኙት ገቢ 0.8 በመቶ ግብራቸውን ጣሊያን ለምትገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለመለገስ ከሚያስችለው የ‘ኤክስሚሌ ምርጫ’ በሚባለው እና መንግስት በተለይ ለሃይማኖታዊ ተቋማት እና ለራሱም ጭምር ለማህበራዊ እና ሰብአዊ ዓላማዎች የሚመድበው፡ ከግብር የሚያገኘው ገንዘብ እንደሆነ ይታወቃል።

ለአካባቢያዊ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት

በዶዶማ ከተማ፥ በተለይ በድንበር ወረዳ ባሉ አከባቢዎች ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፥ የቅዱስ ጌማ ሆስፒታል በከተማዋ ለሚግኙ ድሃ ቤተሰቦች ተመራጭ ቁልፍ ቦታ አድርጎታል ተብሏል።

የኢጣሊያ ጳጳሳት የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ፥ ነባር የጤና ተቋማትን ያስፋፋል፣ ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚያርፉበትን የአልጋ ብዛት ይጨምራል፣ አዲስ የእናቶች ክፍል ይገነባል፣ ብሎም ያለጊዜ ለተወለዱ ሕፃናት እንክብካቤ መስጫ ማሽኖች እንዲኖሩ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ እና ከዚህም በተጨማሪም እነዚህ ማሻሻያዎች በዶዶማ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የጤና ተቋማትንም እንደሚደግፉ ተገልጿል።

በመጨረሻም የጄሜሊ ሆስፒታል አባላት በአዲሱ የወሊድ ክሊኒክ ውስጥ ለሚያገለግሉ የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጡ ተነግሯል።
 

01 February 2024, 12:39