ፈልግ

ለአዲሱ መተግበሪያ የተዘጋጀ በራሪ ወረቀት ለአዲሱ መተግበሪያ የተዘጋጀ በራሪ ወረቀት 

የህንድ ጳጳሳት የካቶሊክ ምዕመናኖች ከደብሮቻቸው ጋር የሚገናኙበትን የመገናኛ መተግበሪያን አስተዋወቁ

የካቶሊክ ኮኔክሽን መተግበሪያ በህንድ ላሉ ካቶሊኮች በተለያዩ መንገዶች ከቤተክርስቲያን ጋር በተሻለ ሁኔታ እንዲገናኙ የሚረዳ የሞባይል መተግበሪያ ሲሆን፥ ይህም መተግበሪያ በአቅራቢያቸው ያለውን አብያተ ክርስቲያናትን ለማግኘት፣ የቅዳሴ ሰዓታትን ለማግኘት፣ ከቁምስናቸው ጋር ለመገናኘት እንዲሁም እርስ በእርስ ለመረዳዳት እና ለመደጋገፍ እንደሚያገለግልም ተብራርቷል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በህንድ የሚገኘው የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ አዲስ ‘የካቶሊኮች መገናኛ የሞባይል መተግበሪያ’ የተባለውን በሀገሪቱ ያሉ ምእመናን የሚረዳ አዲስ የስማርት ስልክ መተግበሪያን አስመርቋል።

መተግበሪያው ረቡዕ ዕለት በባንጋሎር ከተማ በቅዱስ ዮሃንስ ብሄራዊ የጤና ሳይንስ አካዳሚ በተካሄደው የምልአተ ጉባኤ ወቅት በይፋ ተጀምሯል።

የሕንድ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ፊሊፔ ኔሪ ፌራኦ፣ የቦምቤይ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኦስዋልድ ግራቺያስ፣ የሃይደራባድ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አንቶኒ ፑላ እና በጉባኤው አመራር ውስጥ ያሉ ሌሎች በርካታ ሰዎች በሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

የጳጳሳቱ ጉባኤ በሰጠው መግለጫ እንዳብራራው፥ መተግበሪያው የጤና መድህን፣ ትምህርት፣ ስራ እና የአደጋ ጊዜ እርዳታን ጨምሮ መንፈሳዊ ግብዓቶችን፣ ተዛማጅ ዜናዎችን እና የተለያዩ የካቶሊክ ህይወት አገልግሎቶችን በማቅረብ ሁሉን አቀፍ መድረክ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።

አብያተ ክርስቲያናትን እና አገልግሎቶችን ማግኘት

በተጨማሪም ተጠቃሚዎች በአቅራቢያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ዬት እንዳሉ ማግኘትን ጨምሮ በህንድ ውስጥ ባሉ ቤተክርስቲያናት የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ።

የመተግበሪያው ዓላማ ተጠቃሚዎችን ስለአካባቢያዊ እድገቶች እንዲያውቁ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፥ በባህሪውም የጂኦግራፊካዊ አካባቢያቸው ምንም ይሁን ምን፥ በተጠቃሚዎች መካከል ያሉ ማህበረሰባዊነትን እና ግኑኝነትን ለማሳደግ የታሰበ ነው ተብሏል።

መተግበሪያው በተጨማሪም “የእኔ አጥቢያ” እና “የእኔ ሀገረ ስብከት” በሚል መግቢያ አማራጭ ሥር ለመረጃ፣ ለዝግጅቶች፣ ለማስታወሻዎች፣ ለማስታወቂያዎች እና የዜና እረፍት ክፍሎችን የያዘ ገፅ ስለሚያዘጋጅ ይህ መሳሪያ ካቶሊኮች ከየአጥቢያዎቻቸው እና ሀገረ ስብከታቸው ጋር እንዲገናኙ ይረዳቸዋል።

የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች ወደ መተግበሪያው ለመግባት ምዝገባ በሚያደርጉበት ወቅት ደብራቸውን እና ሀገረ ስብከታቸውን መምረጥ ይችላሉ ተብሏል።

አጠቃላይ እና ሁሉን ያማከለ የመረጃ መድረክ

በተጨማሪም፣ መተግበሪያው ለህንድ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽኖች ተግባራቸውን፣ የስልጠና ክፍለ ጊዜዎችን እና ፕሮግራሞችን የሚያሳዩበትን የተለየ ቦታ እንደሚሰጥ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ሁሉን አቀፍ የሆነው መድረክ የኮሚሽኑ ፀሃፊዎች ተነሳሽነታቸውን በቀጥታ እንዲያሳዩ እንደሚያስችላቸው እና በዚህም የህንድ ጳጳሳት ጉባኤ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ተደራሽነት እና ተፅእኖ ያሳድጋል ተብሏል።
 

01 February 2024, 15:03