ፈልግ

በሄይቲ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት በሄይቲ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት  (AFP or licensors)

የሄይቲው ብጹዕ አቡነ ዱማስ እየደረሰ ባለው እገታና ግድያ ቤተክርስቲያን እና ህዝቡ ተሰላችቷል አሉ

የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የአንሴ-ቬው-ሚራጎን ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፒየር-አንድሬ ዱማስ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በካሪቢያን አገር ያለውን መቋጫ ያላገኘውን ተከታታይ ጥቃት አውግዘው፥ ለመላው ህዝብ ጥቅም ሲባል በጥበብ ጣልቃ መግባት እንደሚያስፈልግ ለባለስልጣናት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከጥቂት ቀናት በፊት የአንድ ገዳም የበላይ አለቃ የሆኑ የአንድ መነኩሲት ዘመድ ያለ ምንም ፍንጭ እንደጠፉ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ እገታ የተፈጸመው ባለፈው ጥር ወር መገባደጃ ላይ በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት-ኦ ፕሪንስ ውስጥ የሚገኙት የቅድስት አኔ ገዳም ስድስት እህቶች ታግተው ከበርካታ ቀናት ምርኮ በኋላ የተለቀቁበት ክስተተ በኋላ ይህ ሁለተኛው መሆኑ ነው የተነገረው።

የሄይቲ የግድያ እና የእገታ ተግባራት ከቀን ወደ ቀን እየባሰበት ቢሄድም፥ የሃገሪቷ ጳጳሳት በጉዳዩ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ በትጋት እየሰሩ እንደሆነ እና ይህንንም አስመልክቶ የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ “የሄይቲን ሕዝብ ስቃይ እንዲያቆሙ ባለሥልጣናትን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን” ብለዋል።

ምንም እንኳን የጳጳሳቱ ልባዊ ምክር ሰሚ ያገኘ ባይመስልም፥ ጥረታቸው ለህዝባቸው ባላቸው ፍቅር እና በጌታ በማመናቸው ነው ተብሏል።

“ብዙ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና እገታ ደርሶብናል፥ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተከታታይ ተከስተዋል” በማለት የአካባቢው ባለሥልጣናት “የአሁኑን ሁኔታ አሳሳቢነት እንዲገነዘቡ እና መሠረታቸው ከፍተኛ አደጋ ላይ ለወደቀው መላው ሕዝብ የሚጠቅም ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንዲያደርጉ” አስር የሄይቲ ጳጳሳት የማሳሰቢያ ጽሁፍ ለባለስልጣናቱ ጽፈዋል።

የእርስ በርስ ጦርነት ስጋት

ብጹእ አቡነ ፒየር-አንድሬ ዱማስ በጉባኤው ውስጥ ካላቸው ሚና ባሻገር፥ ስድስቱ እህቶች የታገቱበት የአንሴ-ቬው-ሚራጎን ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪ ናቸው። በወቅቱም መነኮሳቱን ለማዳን ሲሉ ራሳቸውን ለአጋቾቹ እንደ መደራደሪያ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።

ብጹእ አቡነ ዱማስ ከቫቲካን የዜና ወኪል ፌዴሪኮ ፒያና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በታጠቁ ቡድኖች መካከል ያለው ግጭት ወደ እርስ በርስ ግጭት ሊሸጋገር እንደሚችል በመጠቆም፥ ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዳይኖር፥ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተቻለ ፍጥነት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግሩን እንዲመሩ አሳስበዋል።

ጳጳሱ በማከልም “ጥር 29 በተከበረው የአምባገነኑ ስርዓት የወደቀበት ዓመታዊ በዓል ላይ፥ ከተደረጉት የፖለቲካ ስምምነቶች በኋላ ለዴሞክራሲያዊ ተቋማት መወለድ ሁኔታዎችን የሚፈጥርበት አዲስ ጅምር ትክክለኛ ቀን ሊሆን እንደሚችል አሳምነውን ነበር፥ ነገር ግን ይህ አልሆነም” ሲሉ አስረድተዋል።

ሰላማዊ መፍትሄዎች ያስፈልጉታል

ብጹእ አቡነ ዱማስ ህዝቡ ከአሁን በኋላ ይሄንን ጉዳይ ሊታገሰው እንደማይችል በማሳሰብ፥ በሃገሪቷ ውስጥ እየተበራከተ ያለውን የህዝቡን አመፅ እና ብጥብጥ በማስተዋል፥ ሄይቲያውያን “በሞት እና በድህነት ተሰላችተዋል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

ከጳጳሳት ጉባኤው ጋር ሙሉ በሙሉ በመስማማት ቤተክርስቲያን ከሕዝብ ጎን መሆኗን አጽንኦት ሰጥተው ከገለጹ በኋላ፥ ነገር ግን የቤተክርስቲያን ተግባር “ሰላማዊ መፍትሄዎች መፈለግ እንዳለበት ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ዱማስ የሄይቲ ማህበረሰብ በግጭቱ ምክንያት እየተዳከመ እና ሽባ መሆኑን በምሬት ተናግረዋል። ይህንንም አስመልክተው እንደተናገሩት “ህጻናት ትምህርታቸውን ካቆሙ አራት ሳምንታት ተቆጥረዋል፥ ምክንያቱም በሁከቱ መባባስ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል” ካሉ በኋላ “ይህም የውድቀት ምልክት ነው” በማለት የሄይቲ ቤተክርስቲያን ለባለሥልጣናት ባቀረበችው ጥሪ መሰረት “በጥበብ የተሞላ ወሳኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ” አሳስበዋል።

የሰላም እና የነፃነት መንገድ

ብጹእ አቡነ ዱማስ ለምእመናን የጻፉት የጾም ጸሎት ደብዳቤ፥ ከሰላምና ከወንድማማችነት ፍቅር የሚመነጭ “ወደ እውነተኛ የነፃነት ጉዞ” መደረግ እንዳለበት የሚገልጽ ማጣቀሻ ይዟል።

በዚሁ መልዕክታቸውም የወንጌልን ቃል በመጠቀም “ልንሄድ ይገባናልና ተነሱ” በሚለውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል መነሳሳት አለብን በማለት አበረታተዋል።

ስለዚህም በጥቂቱም ቢሆን ሄይቲያዊያን ‘ሕዝቡ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ መኖር እንዲችል እና ከገባበት መንፈሳዊ ድክመት ለማውጣት የሄዱትን ኤልያስን፣ ሙሴን፣ ኢያሱንና ዮናስን መምሰል አለባቸው’ ብለዋል።
 

14 February 2024, 13:03