ፈልግ

በአውሮፓዊያኑ የገና ሳምንት በናይጄሪያ በደረሰ ጥቃት ለሰለባዎች በፕላቱ ግዛት የቀብር ስነ ስርዓት ሲካሄድ በአውሮፓዊያኑ የገና ሳምንት በናይጄሪያ በደረሰ ጥቃት ለሰለባዎች በፕላቱ ግዛት የቀብር ስነ ስርዓት ሲካሄድ 

የአውሮፓ ህብረት ጳጳሳት በናይጄሪያ የገና ሰሞን የተከሰተውን ጥቃት ሃይማኖታዊ ገጽታ አጉልተው ገለጹ

የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን ሰሞኑን የአውሮፓ ህብረት የገና ሰሞን ላይ በናይጄሪያ የተፈጸመውን ጭፍጨፋን ያወገዘበት ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበል በመግለጽ፥ ነገር ግን ተቋሙ ያወጣው ፅሁፍ የጥቃቱን ሃይማኖታዊ ምክንያቶች ዝቅ አድርጎ ያሳያል ሲል በቁጭት ገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአውሮፓ ጳጳሳት በናይጄሪያ በሚገኙ የክርስቲያን ማህበረሰቦች ላይ እየደረሰ ያለውን ስደት በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፥ የአውሮፓ ህብረት ተቋማት በአፍሪካ ሀገር ውስጥ ለሚታየው እስላማዊ አሸባሪነት የበለጠ ግልጽ የሆነ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ፓርላማ ባለፈው ሳምንት ባፀደቀው አስቸኳይ ውሳኔ፥ በማዕከላዊ ናይጄሪያ ፕላቶ ግዛት ውስጥ ባሉ ቦክኮስ፣ ባርኪን ላዲ እና ማጉ አስተዳደር ውስጥ ባሉ ከ160 በሚበልጡ መንደሮች ላይ በአውሮፓዊያኑ የገና ሰሞን በሙስሊም ፉላኒ ታጣቂዎች የደረሰውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ አጥብቆ አውግዟል።

በአውሮፓዊያኑ የገና ሳምንት ስምንት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል በተባለው ጥቃት፥ የአውሮፓ ፓርላማ ጭፍጨፋውን አስመልክቶ በሰጠው ውሳኔ፥ በትንሹ 200 ክርስቲያኖች እንደተገደሉ እና ከ300 በላይ የሚሆኑት እንደቆሰሉ፥ በርካቶች ደግሞ ቤት አልባ እንደሆኑ፣ ብሎም በጥቃቱ ምክንያት ወደ 15,000 የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።

የአውሮፓ ህብረት ባፀደቀው የውሳኔ ሃሳብ፥ በዋናነት በክርስቲያን አርሶ አደሮች እና በሙስሊም ፉላኒ እረኞች መካከል በተፈጠረው ግጭት እንደ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው “የአየር ንብረት ለውጥ ሚና፣ የአላቂ ሀብቶች ይዞታነት ፉክክርን እና ውጤታማ የሽምግልና ሥርዓቶች መጥፋት” መሆናቸውን አጉልቶ አሳይቷል።

የፉላኒ ጽንፈኞች በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱት ስልታዊ የሽብር ጥቃት

የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን የውሳኔ ሃሳቡን በደስታ እንደሚቀበል በመግለጽ፥ ነገር ግን ጽሑፉ የድርጊቱን ሃይማኖታዊ ገጽታ እና የሽብርተኝነት ባህሪውን የሚያሳንስ መሆኑን ገልጸዋል።

የናይጄሪያ ጳጳሳት በበኩላቸው “ተባብሶ የቀጠለው በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በታጠቁ እረኞች እየደረሰ ያለው ጥፋት፥ ከአሁን በኋላ በአርብቶ አደሮች እና በገበሬዎች መካከል እንደሚከሰት ተራ ግጭት ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፥ ይልቁንም እንደ ሽብርተኝነት መወሰድ አለበት” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።

የአውሮጳ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ የሆኑት አባ ማኑኤል ባሪዮስ ፕሪቶ እንደተናገሩት “አካባቢያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ብቻቸውን የጥቃቶቹን አስከፊነት እና በፉላኒ እስላማዊ አሸባሪዎች የተፈጸሙ የተቀናጁ እና ስልታዊ ጥቃቶችን በበቂ ሁኔታ መግለጽ አይችሉም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በእርግጥ የአውሮፓዊያኑ የ2023 የገና ዋዜማ ጥቃቶች የተለዩ ድርጊቶች ባይሆኑም፥ ከእስላማዊ ሽብርተኝነት እስከ ሽፍቶች ያሉ የደህንነት ተግዳሮቶች እያደጉ ባለበት ወቅት፥ ክርስቲያኖች በተለየ ሁኔታ ኢላማ እንደሚሆኑ ብሎም ለጥቃት እንደሚጋለጡ ተነግሯል።

የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን ጥር 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ ጥቃት የፉላኒ ሰርጎ ገብ አሸባሪዎች ከ30 በላይ ሰዎችን እንደገደሉ እና በርካታ ቤቶችን እና የአምልኮ ማዕከሎችን ማውደማቸውን አስታውሷል። ባለፈው መስከረም፥ የካፋንቻን ሀገረ ስብከት የስነ መለኮት ተማሪ የሆነው ናአማን ዳንላሚ ስቴፈን በአስከፊ የሽብር ጥቃት በእሳት ተቃጥሎ መገደሉ እንደሚታወስ እና በተጨማሪም በቤንዩ ክልል ከ2 ሚሊዮን በላይ ክርስቲያኖች በሁከቱና ብጥብጡ ምክንያት መፈናቀላቸው ተዘግቧል።

ወንጀለኞችን አለመቅጣት

የአውሮፓ ፓርላማ ግንቦት 2012 ዓ.ም. ላይ “ከ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ከ6,000 በላይ ክርስቲያኖች በጂሃዲስት ቡድኖች ተገድለዋል ወይም በፉላኒ ታጣቂዎች በተካሄደው ‘መሬታችሁ ወይም ደምህ’ በሚል ፖሊሲ ምክንያት ጠፍተዋል” ሲል አውግዞ እንደነበር ይታወሳል።

ጂሃዲስቶችን ጨምሮ እነዚህን ወንጀሎች የፈፀሙት ወንጀለኞች እምብዛም ስለማይከሰሱ እና ስለማይወገዙ ወንጀሉን በተደጋጋሚ እንዲፈፅሙት አድርጓል ተብሏል።

እንደ አባ ባሪዮስ ፕሪቶ አባባል “እነዚህ ሁሉ ወንጀሎችን የፈፀሙ ሰዎች ከአሁን በኋላ ተጠያቂ የማይሆኑበት ምክንያት ተቀባይነት ዬለውም” ካሉ በኋላ “የናይጄሪያ መንግሥት ስልታዊ በሆነ መንገድ በሃይማኖታቸው ምክንያት ለሚሰደዱ የክርስቲያን ማህበረሰቦችን ጨምሮ ዜጎቹን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት” ብለዋል።

ከአውሮፓ ህብረት ከዚህ የበለጠ ወሳኝ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ

በመሆኑም የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን፥ የአውሮፓ ህብረት “ከህጎቹ ጋር የሚጣጣሙ ጠንካራ እርምጃዎችን እንዲወስድ እና በናይጄሪያ ውስጥ የሁሉንም ዜጎች ጥበቃ ለማረጋገጥ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን እንዲጠቀም” ጥሪውን አቅርቧል።

በዚህ አውድ የአውሮፓ ህብረት የሃይማኖት ወይም የእምነት ነፃነት ልዩ መልዕክተኛ እና የአውሮፓ ህብረት የሰብአዊ መብቶች ልዩ ተወካይም ጠቃሚ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ ይችላሉ ብሏል ጉባኤው።

የአውሮፓ ኅብረት የጳጳሳት ጉባኤ ኮሚሽን በናይጄሪያ ከ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እየጨመረ የመጣውን በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ስደት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያወግዘው ጠይቋል። ግንቦት 2015 ዓ.ም. ይህ የጳጳሳት ኮሚሽን የሶኮኮውን ብጹእ አቡነ ማቲው ሀሰን ኩካህን በመጋበዝ ከአውሮፓ ህብረት እና ከአባል ሀገራት ተወካዮች ጋር የውይይት መድረክ እንዲካሄድ አመቻችቶ እንደነበርም ተገልጿል።

በናይጄሪያ ለሽብርተኝነት እና ለአጠቃላይ ደህንነት ሁኔታዎች ተጋላጭ የሆኑ ክርስቲያኖች

‘ኦፕን ዶር’ የተባለው ለስደት የሚዳረጉ ክርስቲያኖችን እና አብያተ ክርስቲያናትን የሚደግፈው ዓለም አቀፍ ተሟጋች ድርጅት በቅርቡ እንዳረጋገጠው፥ በእስልማዊ አሸባሪነት እስከ ተራ ውንብድና ድረስ ለዓመታት እጅግ በርካታ የጸጥታ ፈተናዎች ውስጥ የምትገኘው ናይጄሪያ ክርስቲያኖች ለመኖር አስቸጋሪ ከሆኑባቸው ሃገራት ቀዳሚዋ እንደሆነች አሳውቋል።

በ2013 ዓ.ም. በዓለም ዙሪያ ካሉት አጠቃላይ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ከተገደሉት 90% የሚሆኑት ናይጄሪያ ውስጥ እንደሆኑ እና በየቀኑ በሃገሪቷ ውስጥ በአማካይ 14 ክርስቲያኖች እንደሚሞቱ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ከ2019 ዓ.ም. ጀምሮ ናይጄሪያን ሠላም እያሳጣ ያለው እስላማዊው የቦኮ ሃራም ጥቃት፥ ክርስቲያኖች ላይ ከተደቀነባቸው ዋና ዋና የጸጥታ ስጋቶች አንዱ ነው። እነዚህ አሸባሪዎች የምዕራባውያንን ትምህርት የሙስና እና የሞራል ውድቀት ምልክት አድርገው በመመልከት አጥብቀው ይቃወማሉ።

ለማስለቀቂያ ገንዘብ ተብሎ የሚደረገው የእገታ ጥቃት

ይህ በእንዲህ እያለ ለማስለቀቂያ ገንዘብ ተብሎ የሚደርሰው የእገታ ጥቃትም በየቤተክርስቲያኑ እየተስፋፋ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ ካህናት እና ገዳማዊያት በየጊዜው በዘራፊዎች እንደሚታገቱ ተገልጿል።

በጣም በቅርብ ጊዜ ከተከሰቱት የእገታ ወንጀሎች መሃል፥ የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ሁለት ክላሬቲያን የሚባሉ የቅድስት ልብ ማርያም ሚስዮናውያን በፕላቶ ግዛት ውስጥ በታጣቂዎች ታግተው እንደተወሰዱ እና ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደተፈቱ ማስታወስ ይቻላል።
 

13 February 2024, 13:30