ፈልግ

ናይጄሪያውያን የእገታ ተግባሩን ሲቃወሙ ናይጄሪያውያን የእገታ ተግባሩን ሲቃወሙ  

የቅድስት መንበር የወንጌል ስርጭት ጽ/ቤት ናይጄሪያ ውስጥ የሚፈጸመውን የእገታ ተግባር አወገዘ

ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ እና ብጹእ አቡነ ፎርቹኔተስ ዋቹኩ ለናይጄሪያ ጳጳሳት በፃፉት መልዕክት የቫቲካን ጽ/ቤት በናይጄሪያ ውስጥ በሚፈፀመው የእገታ ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ያለውን አጋርነት በመግለጽ መልእክት አስተላልፈዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቫቲካን የወንጌል ስርጭት ጽ/ቤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የእገታ ተግባር ጋር በመታገል ላይ ላለው የናይጄሪያ ሕዝብ ያለውን “ጥልቅ እና ልባዊ አጋርነት” ገልጿል።

በዘራፊዎች ወይም በታጣቂዎች የሚፈፀመው ይህ የጠለፋ ተግባር ለወንጀለኞቹ እንደ ‘አትራፊ ሥራ’ የሚታይ ሲሆን፥ ለናይጄሪያ ህዝብ ግን በሰሜን የሚገኘውን የጂሃዲስቶች ዓመፅን ጨምሮ የሚከሰቱት የጸጥታ ችግሮች ትልቅ ፈተና እየሆነ መምጣቱ እየተነገረ ነው።

ቤተክርስቲያንም ዒላማ ተደርጋለች

ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግል የቫቲካን የወንጌል ስርጭት ጽ/ቤት አለቃ እና የልዩ አብያተ ክርስቲያናት ጽ/ቤት ተጥሪ፣ እንዲሁም በሮማ ኩሪያ ውስጥ የወንጌል ስርጭት ክፍል ጸሃፊ ሆነው እየሰሩር የሚገኙት ናይጄሪያዊ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፎርቹኔተስ ዋቹኩ በጋራ በመሆን ለናይጄሪያ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ለሆኑት የኦዌሪው ሊቀ ጳጳስ ለብጹእ አቡነ ሉሲየስ ኡጁሩ ኡጎርጂ በፃፉት መልዕክት፥ ‘በእነዚህ አስጸያፊ ድርጊቶች በአሳዛኝ ሁኔታ ከታገቱት መካከል ካህናት፣ ገዳማዊያት እና ምዕመናን እንደሚገኙበት’ በመግለጽ፥ ወንጀሉን በጽኑ አውግዘዋል።

ቤተክርስቲያን ላይ ትኩረት ያደረገ ጥቃት የጀመረው የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ሁለት ክላሬቲያን (የቅድስት ልበ ማርያም ሚስዮናውያን) በፕላቱ ግዛት ውስጥ በተወሰኑ ታጣቂ ሃይሎች ታፍነው ከጥቂት ቀናት በኋላ ከተለቀቁ ጀምሮ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የእገታን ተግባር ምንም ነገር ፍትሃዊ ሊያደርገው አይችልም

የቫቲካን የዜና ተቋም የሆነው ‘ፊደስ ኤጀንሲ’ እንደዘገበው “የእገታን ክፋት ምንም ነገር ፍትሃዊ ሊያረገው አይችልም” ሲል አፅንዖት በመስጠት መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፥ ምክንያቱም ደግሞ ይላል መልዕክቱ “ከአፈና ጋር ተያይዞ የሚደርሰው አካላዊ ጥቃት እና አእምሮአዊ ስቃይ የጥቃቱ ሰለባዎች፣ ቤተሰቦቻቸውን እና በአጠቃላይ ማህበረሰቡን በጽኑ እንደሚጎዳ ብሎም የዜጎችን እና የማህበረሰቡን የጋራ እሴቶች ያበላሻሉ” ብሏል።

መልዕክቱ በመቀጠል “ሐሳባችንና ጸሎታችን ከጳጳሳት፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከገዳማዊያን፣ ከስነመለኮት ተማሪዎች፣ ከታማኝ የቤተ ክርስቲያን አባላት፣ በመላው ዓለም ላይ ካሉ ክርስቲያኖች እና በጎ ፍቃድ ካላቸው ህዝቦች ጋር ነው” ካለ በኋላ፥ የእገታው ሰለባ ለሆኑ ንጹሐን ወገኖቻችን እና ቤተሰቦቻቸው ጥልቅ የሆነ ርኅራኄ እንዳለው ገልጿል።

መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ የተደረገ ጥሪ

የቫቲካን ጽ/ቤት ኃላፊዎቹ የናይጄሪያ ጳጳሳት ለናይጄሪያ መንግሥት “ይህን ችግር በአስቸኳይ እንዲቀርፍ እና እያንዣበበ ያለውን ቀውስ ለመቅረፍ እንዲቻል ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ” ያቀረቡትን ተደጋጋሚ ጥሪ አስተጋብተዋል። በተጨማሪም “መንግስት ከቤተክርስቲያን ጋር በጋራ በመስራት ህይወትን እና ንብረትን ለማስጠበቅ ወሳኝ እርምጃ እንዲወስድ እና በኢኮኖሚ እድገት፣ በፖለቲካዊ መረጋጋት እና በሃይማኖታዊ ትስስር ላይ ሀገሪቱን ለማስተካከል መንገዶችን መፈለግ አለበት” ብለዋል።

በመጨረሻም መልዕክቱ “ተስፋችን በዚህ የጀመርነው የዐብይ ጾም በናይጄሪያ ውስጥ ላሉ አማኞች እና ማኅበረ ቅዱሳን ሁሉ በመንፈሳዊ ህይወት ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ ነው፥ ለዚህም ጌታ ይባርካችሁ፣ የናይጄሪያዋ ጠባቂ ቅድስት ድንግል ማርያም ትጠብቃችሁ” በማለት ቋጭቷል።

ከግንቦት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በናይጄሪያ ወደ 4,000 የሚጠጉ እገታዎች ተከስቷል

አዲስ የተመረጡት ፕሬዝዳንት ቦላ አህመድ ቲኑቡ ግንቦት 2015 ዓ.ም. ስልጣን ከያዙ በኋላ በናይጄሪያ ወደ 4,000 የሚጠጉ እገታዎች የተመዘገቡ ሲሆን፥ ታግተው ብር መክፈል ያልቻሉ በርካታ ታጋቾችም እንደተገደሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

ዋና ከተማዋን አቡጃን እንኳን ከዚህ መቅሰፍት ማዳን እንዳልተቻለ የተነገረ ሲሆን፥ ታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. አንድ አባት እና ስድስት ሴት ልጆቹ ታግተው በወቅቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ እንደነበረ እና ለአጋቾቹ የማስለቀቂያ ክፍያ ተከፍሎ የነበረ ቢሆንም፥ ታጋቾቹ በምትኩ አንዲት ሴት ልጁን ገድለው ተጨማሪ ገንዘብ መጠየቃቸው ይታወሳል።
 

19 February 2024, 15:01