ፈልግ

በሙንስተር የተደረገው ሰልፍ በሙንስተር የተደረገው ሰልፍ 

የጀርመኑ ካሪታስ ሙንስተር ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እንሰራለን አለ

‘ኤ.ኤፍ.ዲ’ ተብሎ የሚጠራው የጀርመን አክራሪ ቀኝ ክንፍ ፓርቲ ደጋፊዎች እየጨመሩ በመጡበት በአሁኑ ወቅት፥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሰብአዊ እርዳታ ድርጅት የሆነው ካሪታስ ዜጎች ለዲሞክራሲ እና ለጋራ እሴቶች እንዲቆሙ የሚጠይቅ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጀምሯል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጀርመን ከተሞች "ዲሞክራሲን እንጠብቅ" በሚል መሪ ቃል ተቃዋሚዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ሲሆን፥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በርሊን፣ ሃኖቨር፣ ማግድበርግ፣ ቦኩም፣ ሪትበርግ፣ ሙንስተር እና ኤሰንን ጨምሮ በተከታታይነት ትናንሽ ከተሞች እና ማህበረሰቦች ውስጥ ትልልቅ ሰልፎች ተካሂደዋል።

ስደተኞችን መቀበልን፣ ብዝሃነትን እና አካታችነትን የሚቃወመውን የቀኝ አክራሪ የሆነውን የ‘ኤውሮሴፕቲክ ኦልተርኔቲቭ ፈር ዶችላንድ (AfD) ፓርቲ ግስጋሴን በመቃወም ሰልፈኞች ድምጻቸውን እያሰሙ ሲሆን፥ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚናገሩት ፓርቲው ሀገሪቱን ወደ አምባገነን መንግስት መቀየር እንደሚፈልግ ይገልፃሉ።

የጀርመን ጳጳሳት ባለፈው ጥር ወር ላይ ባወጡት የጋራ መግለጫ፥ ‘ጥገኝነት የሚፈልግ ማንኛውንም ሰው ማባረር፣ አካል ጉዳተኞችን ማግለል እና የአየር ንብረት ለውጥ ሰው ሰራሽ ቀውስ መሆኑን የሚክዱ ፖሊሲዎችን በማውገዝ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

የካቶሊክ የእርዳታ ተቋም የሆነው ‘ካሪታስ ሙንስተር’ ከሀገረ ስብከቱ ጋር በመተባበር ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እና በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ አክራሪ ፓርቲዎችን በመቃወም የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ አዘጋጅቷል።

የካሪታስ ሙንስተር ኃላፊ የሆኑት አቶ ዶሚኒክ ሆፕፌንዚት ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ድርጅቱ ለማህበረዊ ፖለቲካ ስላለው ሃላፊነት እና ተቻችሎ ለመኖር፣ ለአብሮነት እና ለማህበራዊ ትስስር የመሳሰሉ እሴቶች የመታገል ግዴታ እንዳለበት ደጋግመው አሳውቀዋል።

ሃላፊው እንደገለጹት “በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ #ለመብታችን እንታገላለን፣ ዲሞክራሲያዊ እሴቶቻችንን እና ክርስቲያናዊ እሴቶቻችንን የሚጋሩ ሰዎችን ማግኘት እንፈልጋለን” ካሉ በኋላ፥ ቤተክርስቲያን እና ድርጅታቸው ካሪታስ ለአብሮነት፣ ለመቻቻል እና ለማህበራዊ ትስስር ይታገላል ሲሉ አብራርተዋል።

አቶ ዶምኒክ አክለው እንደተናገሩት መሪዎቻችንን እና ፖሊሲ አውጭዎቻችንን ለመምረጥ እየተዘጋጀ ላለው ህዝባችን ማሳየት የምንፈልገው ነገር፥ ለአክራሪ ቀኝ ክንፍ ፓርቲዎች ድምጽ መስጠት “ትክክለኛ መንገድ እንዳልሆነ ነው” ብለዋል።

ሃላፊው ባለፈው ሳምንት በሙንስተር የተካሄደውን ሰልፍ በማስታወስ፥ ከ30,000 በላይ ሰዎች ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ያላቸውን ድጋፍ እያሳዩ እና ጽንፈኛ ፓርቲዎች የሚያሰሙት ተራ የመፍትሄ ሃሳቦች ትክክለኛ መንገድ እንዳልሆኑ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቤተ ክርስቲያን ሚና

የጀርመን ቤተ ክርስቲያን እና የካሪታስ ድርጅቶች ይላሉ አቶ ዶምኒክ፥ “ዲሞክራሲን ለማስፈን እና ጽንፈኛ አስተሳሰቦችን በመቃወም ልዩ ሚና እና የማህበራዊ ፖለቲካ ሃላፊነት አለባቸው” ካሉ በኋላ “ህብረተሰቡ የካሪታስ እና የቤተክርስቲያንን አመለካከት እና አስተያየት መስማት ብሎም ማወቅ ይፈልጋል ብለን እናስባለን” ሲሉ አክለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ምርጫ

ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በጀርመን የሚካሄደውን የየአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ በጉጉት እንደሚጠባበቁ በመግለጽ፥ “በጀርመን እና በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ያሉ ህዝቦች ጽንፈኛ ፓርቲዎች መፍትሄ እንዳልሆኑ ይገነዘባሉ” በማለት ያላቸውን ተስፋ በድጋሚ ተናግረዋል።

የመራጮች ንቁ ተሳትፎ እየታየበት ባለበት በዚህ ወቅት ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውንና ግዴታቸውን እንደሚጠቀሙበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በቅርቡ በጀርመን እየታየ ያለው የዲሞክራሲ ደጋፊ ንቅናቄዎች መነቃቃት የጀመረዉም የቀኝ ክንፍ አክራሪ ፓርቲ የውጭ ዜጎችን ከሀገር እንዲባረሩ ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁበት የቴሌ ቪዥን ቃለ ምልልስ ከታየ በኋላ እንደሆነም አቶ ዶምኒክ ገልጸዋል።

ሃላፊው ቃለ ምልልሳቸውን ሲያጠቃልሉ “ዲሞክራሲያዊ ህዝቦች ጎዳና ላይ ወጥተው ሃሳባቸውን ለመግለጽ በጣም ትልቅ ጽናት እንዳላቸው እና የቀኝ ክንፍ ጽንፈኛ ፓርቲዎችን ስለመምረጥ ለሚያስቡ ሰዎች መልዕክት እንደሚያስተላልፉ፥ ብሎም በሃገሪቷ ውስጥ ዴሞክራሲ የበለጠ ጠንካራ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
 

22 February 2024, 12:43