ፈልግ

በዩክሬን በመሳሪያ ተመቶ የወደመ ህንፃ በዩክሬን በመሳሪያ ተመቶ የወደመ ህንፃ  (AFP or licensors)

የካናዳ ክርስቲያኖች በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት እና ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቀረቡ

በካናዳ የሚገኙ ዋና ዋና የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተክርስቲያን ማህበረሰቦች በጋራ በመሆን ክርስቲያኖች እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ሁሉ በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን በህብረት ጸሎት እንዲያደረጉ እና የሰላም እርምጃ እንዲወስዱ የሚያሳስብ "የካናዳ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ" አወጡ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ በሙሉ ወረራ የጀመረችበትን ሁለተኛ ዓመት ከመከበሩ በፊት፥ የካናዳ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት ማኅበረሰቦች ብሔራዊ ተወካዮች በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን ክርስቲያኖች በጋራ እንዲጸልዩ እና የሰላም እርምጃዎችን እንዲወስዱ በሚያሳስበው “ዩክሬን፣ ካናዳ እና ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ሃዋሪያዊ ደብዳቤ” ላይ ፈርመዋል።

ሃዋሪያዊ ደብዳቤው የወጣው ከካናዳ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ሲሆን፥ ከአባላቱ መካከል የካናዳ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ፣ እንዲሁም የዓለም ወንጌላውያን ህብረት የሰላም እና እርቅ ጥምረት እና የካናዳ ወንጌላውያን ህብረት አባላት ይገኙበታል።

የጸሎት እና የተግባራዊ እርምጃ ጥሪ

ደብዳቤው “በሌሎች የዓለም ክፍሎች በጦርነትና በዓመፅ ምክንያት የሚደርሰውን መከራና ሐዘን ሳናቃልል ወይም ችላ ሳንል በዩክሬን ሰላም እንዲሰፍን አስተዋፅዖ ሊያደርግ ስለሚችል ክርስቲያኖችንና በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ሁላችንም በተጠራንበትን መንገድ በጸሎት እንዲያስቡ በመጋበዝ አብረን እንቆማለን” በማለት ይጀምራል።

ሃዋሪያዊው ደብዳቤ በተለይ በሲቪል ሰዎች እና በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ የተፈፀመውን ኢላማ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች እና ነጻነቶች ጥሰቶችን በማውገዝ፥ የሩሲያ ወረራ ያስከተለውን "ግዙፍ" የሰው ልጅ ስቃይ ይናገራል።

“ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይም” ይላል ደብዳቤው “ሕፃናትን ከቤታቸውና ከቤተሰባቸው በግዳጅ የማፈናቀል ተግባር ነው” በማለት ይገልፃል።

ጦርነቱ እንዲቆም ጠይቀዋል

ደብዳቤው የሩስያ መሪዎችን “ይህን ጦርነት እንዲያቆሙ፣ ይህን ኢፍትሃዊ ጥቃት እንዲያቆሙ፣ በዩክሬን እና በህዝቦቿ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያቆሙ እና ወታደራዊ ሀይላቸውን ክሬሚያን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካላቸው የዩክሬን ድንበሮች በአስቸኳይ እንዲያስወጡ ጥሪ አቅርቧል።

ደብዳቤው በመጨረሻም ጸሎትን ጨምሮ፣ የዩክሬን ስደተኞችን በመደገፍ እና በዩክሬን ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎችን በማበረታታት ክርስቲያኖች ሰላምን መፍጠር የሚችሉባቸውን ጠቃሚ መንገዶችን ይጠቁማል።
 

23 February 2024, 14:50