ፈልግ

ካርዲናል ፒተር ቱርክሰን በካሜሩን ዱዋላ ጉብኝት ሲያደርጉ ካርዲናል ፒተር ቱርክሰን በካሜሩን ዱዋላ ጉብኝት ሲያደርጉ 

ካርዲናል ቱርክሰን የካሜሩን ከተማ የሆነችውን ዱዋላን ጎበኙ

ብፁዕ ካርዲናል ፒተር ቱርክሰን በቅርቡ ካሜሩን በሚገኘው የዱዋላ ሃገረስብከት የ4 ቀናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ በዚያም ለክህነት አገልግሎት ሲዘጋጁ ለነበሩ ዲያቆናት ማዕረገ ክህነት የሰጡበትን ሥርዓተ ቅዳሴ መርተዋል። በሥነ ስርዓቱም ላይ የዱዋላ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሳሙኤል ክሌዳ እና የካሜሩን እና የኢኳቶሪያል ጊኒ ሐዋርያዊ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሆሴ አቬሊኖ ቤተንኮርት ተገኝተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጳጳሳዊ የሳይንስ ከፍተኛ ት/ቤት ቻንስለር የሆኑት ብጹእ ካርዲናል ቱርክሰን በካሜሮን በነበራቸው ቆይታ በርካታ ስብሰባዎችን ያደረጉ ሲሆን፥ በነዚህም ስብሰባዎች ለምእመናን ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ወቅት ተጨባጭ የሆነ ሰላም እና ዕርቅ እንዲመጣ፣ እንደ ወንድም እና እህት አብረው እንዲኖሩ አሳስበዋል።

በሰላም አብሮ መኖርን የሚያበረታታ በጎ ፈቃድ ጉብኝት

የብጹእ ካርዲናል ቱርክሰን ጉብኝት በሰላም አብሮ መኖርን ለማበረታታት እንደመጣ ወዳጅ የሚታይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ በደቡብ ሱዳን እና በአይቮሪ ኮስት ከዚህ ቀደም ያደረጉትን የመልካም ምኞት መግለጫ እና ሌሎችንም እንደ ዋቢነት ተነስተዋል።

በቫቲካን የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ማስፋፊያ ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩት ካርዲናሉ፥ የዱዋላ ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ሳሙኤል ክሌዳ በአፍሪካ በኮቪድ-19 ወቅት ክትባት እና መድኃኒት ለማግኘት ያደረጉትን ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ካርዲናሉ እንደገለፁት፥ ‘ከዚህ በፊት እሳቸውን ለማመስገን እድሉ አልነበረንም፥ ስለዚህ ይህ ጉብኝት ለእርሳቸው ምስጋና የምናቀርብበት አንዱ ሂደት ነው፥ ምክንያቱም እዚህ ያሉትን እና የሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ያሉ የበርካታ ሰዎችን ህይወትን ስላዳኑ ነው” ብለዋል የጋና ተወላጁ ሊቀ ጳጳስ።

ለክርስቶስ እና ለህዝቡ አገልግሎት ይሁኑ

በዱዋላ በሚገኘው የቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ካቴድራል ውስጥ በብፁዕ ካርዲናል ቱርክሰን የተመራው የአምስት ዲያቆናት ሲመተ ክህነት ቅዳሴ ላይ የሃገረስብከቱ መሪ የሆኑት ብጹእ አቡነ ክሌዳ የወቅቱ ጳጳሳዊ የሳይንስ ከፍተኛ ት/ቤት ቻንስለር የሆኑት በመሃከላቸው ስለተገኙ፣ ለተግባራቸው እና ስለ ወዳጅነታቸው ካርዲናሉን ካመሰገኑ በኋላ፥ ካህናቱ የግል ሥራዎቻቸውን እንዲተውና ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለክርስቶስና ለሕዝቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ጋብዘዋቸዋል።

“የካህኑ ብቸኛው ጉዳይ እና ሥራ መሆን ያለበት” ይላሉ ብጹእ አቡነ ክሌዳ፥ “ሊፈጽመው የሚገባው ተግባር ጌታ በሰጠው ተልእኮ ወንጌልን መስበክ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ካህኑ የተቀባው የግል ሥራዎቹን ለማከናወን አይደለም፥ በአጠቃላይ ለጌታ እና ለቤተክርስቲያኑ አገልግሎት መሆን አለብን” ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናል ቱርክሰን የቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ካቴድራልን በጎበኙበት ወቅት አንዳንድ የዱዋላ ምዕመናንን አግኝተው ነበር። በመቀጠልም የቅዱስ ጄሮም የካቶሊክ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምን ጎብኝተዋል።

ካርዲናል ቱርክሰን የካሜሩንን በጎ ፈቃድ ጉብኝታቸውን እሁድ የካቲት 17 በማክፔ-ዱዋላ በሚገኘው የቅዱስ ሞኒኬ ደብር ቤተ ክርስቲያን የምስጋና ቅዳሴ በማሳረግ አጠናቀዋል።

ሃዋሪያዊ ጳጳሱ የካሜሩንን ቤተክርስቲያን አመስግነዋል

ብፁዕ ካርዲናል ፒተር ቱርክሰንን ለመቀበል የመጡት የካሜሩን እና የኢኳቶሪያል ጊኒ ሐዋርያዊ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ጆሴ አቬሊኖ ቤተንኮርት ከጥቂት ቀናት በፊት በሮም ያገኟቸውን የቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሞቅ ያለ ሰላምታ እና ሐዋርያዊ ቡራኬ ለካሜሩን ሕዝብ አስተላልፈዋል።

“እዚህ ካሜሩን ውስጥ ከሦስት ወራት በላይ ቆይቻለሁ፥ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከባህላዊ መሪዎች፣ በተለይም ሙስሊም ወንድሞቻችንን፣ ኢማሞችን፣ ፕሮቴስታንቶችን፣ በዚህች አገር ያሉትን የካቶሊክ ማኅበረሰብ እና በርካታ ሰዎችን ለማግኘት እድሉን አግኝቻለሁ” በማለት ሐዋርያው ጳጳሱ ተናግረዋል።

የቤተክርስቲያን የወንጌል ምስክርነት

ሊቀ ጳጳስ ጆሴ ቤተንኮርት የካሜሩናዊያንን ቤተ ክርስቲያን ሕያውነትና የፈጠራ ሥራ በመመስከር፥ “በካሜሩን ያለችው ቤተክርስትያን ህያው ቤተክርስትያን መሆኗ መታወቅ አለበት፥ በጣም ትልቅ፣ ብዙ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የጤና ማዕከላት፣ እንዲሁም የቤተክርስቲያኑ ማህበራዊ እና የበጎ አድራጎት መዋቅሮች ያሏት ቤተክርስቲያን ናት፥ ይህ በጣም የሚያበረታታ የወንጌል ምስክርነት ነው” ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ተወካይ እንዳሉት ‘በሙሉ ልቤ፥ በካሜሩን በመገኘት እዚህ ላሉት የእግዚአብሔር ሰዎች አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ለአገሪቱ ሰላምና ልማት የበኩሌን ለማበርከት በመቻሌ በጣም ተደስቻለሁ’ ብለዋል።

ሐዋርያዊ ጳጳሱ ከዱዋላ ወደ ደቡብ-ምዕራብ ካሜሩን ክልል በመሄድ የማንፌ ሀገረ ስብከት የተቋቋመበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ላይ ተሳትፈዋል።
 

28 February 2024, 15:09