ፈልግ

እስራኤል በጋዛ በምትፈጽመው የቦምብ ጥቃት የወደሙ ቤቶች እስራኤል በጋዛ በምትፈጽመው የቦምብ ጥቃት የወደሙ ቤቶች   (AFP or licensors)

የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ጋዛ ውስጥ በአስቸኳይ ተኩስ እንዲቆም ግፊት አደረጉ

በኃይል በተያዘው የፍልስጤም ግዛት የአሥርተ ዓመታት ልምድ ያለው እና በዓለም አቀፍ የሰላም ግንባታ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የተፈረመው መልዕክት፥ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት እንድታቆም እና ተኩስ እንዲቆም ጥሪን እንዲያቀርቡ ግፊት አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ካፎድ “CAFOD” የተሰኘው የእንግሊዝ እና የዌልስ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት፥ እስራኤል ተኩስ በማቆም በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት እንድታበቃ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ግፊት እንዲያደርጉ ከፈረሙት 22 የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።

የዓለም አቀፍ የሰላም ግንባታ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እና የዕርዳታ ድርጅቶች ለጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የጋራ መልዕክታቸው የላኩት የእስራኤል መከላከያ ሃይል በጋዛ ሰርጥ በስተደቡብ በምትገኝ ራፋህ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ መሆኑን ባሳወቀበት ወቅት ሲሆን፥ አካባቢው በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች መውጫ አጥተው የሚሰቃዩበት አካባቢ እንደሆነ ይነገራል።

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው የሐማስ ታጣቂዎች መስከረም 26/2016 ዓ. ም. 1,200 የእስራኤል ዜጎችን ገድሎ 240 የሚጠጉን አግቶ ከወሰዳቸው በኋላ እንደነበር ይታወሳል። እስካሁን በእስራኤል የተገደሉት ፍልስጤማውያን 28,663 መድረሱ ታውቋል።

የካፎድ የእስያ እና መካከለኛው ምሥራቅ ክልል ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ጃኔት ሲምስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ተጨማሪ የዜጎች ህይወት እንዳይጠፋ፣ ታጋቾች እንዲፈቱ እና የሕይወት አድን ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲገባ ማድረግ የሚቻለው አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሲደረስ ብቻ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ወ/ሮ ጃኔት ለብሪታኒያ መንግሥት እና ለሁሉም መንግሥታት እንደገለጹት፥ እየተባባሰ ያለውን ቀውስ ለመቅረፍ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ያቀረቡትን ጥሪ አብራርተዋል።

ወ/ሮ ጃኔት በማብራሪያቸው፥ የእንግሊዝ መንግሥት እና ሌሎች የዓለም መንግሥታት የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸው አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ የጋራ መልዕክት መላካቸውን ገልጸዋል። የተጠናከረ የቦምብ ጥቃት እና በራፋህ የመሬት ወረራ እያንዣበበ መሆኑን ወ/ሮ ጃኔት ገልጸው፥ በማከልም ጦርነቱን በአስቸኳይ ለማስቆም ድርድር እንዲደረግ እና ለጋዛ ሕዝብ አስፈላጊው ሰብዓዊ ዕርዳታን ለማድረስ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ጠይቀዋል።

በሐማስ የታገቱት የእስራኤላውያን መፈታትም ወሳኝ ነው ያሉት ወ/ሮ ጃኔት፥ ነገር ግን የፍልስጤም ሲቪሎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የድርድር ሂደት መከናወን አለበት ብለው፥ ከዚህ ቀደም ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የተኬደው ስኬታማ መንገድ ድርድር እንደሆነ መረጋገጡን ጠቁመዋል።

በጋዛ ነዋሪዎች በተለይም በጤና አጠባበቅ ዘርፍ ያጋጠሙትን አስከፊ እውነታ ያስታወሱት ወ/ሮ ጃኔት፥ ጋዛ ውስጥ ማግኘት የማይችሉትን የጤና እንክብካቤ ወደ ሌላ ቦታ ሄደው ለማግኘት የሚጠባበቁ 8000 ያህል ታማሚዎች እንደሚገኙ ተናግረው፥ በግጭቱ ምክንያት ዶክተሮች ለሕሙማኑ የጤና እንክብካቤ መስጠት በጣም አዳጋች እንደሆነ አስረድተዋል።

ከሞት የማይተርፍ ቤተሰብ እና የቆሰለ ሕጻን

ጦርነቱ ያስከተለው አሳዛኝ መዘዞች እና በልጆች ላይ ያስከተለው አስከፊ ውጤት "WCNSF" ወይም ከሞት የማይተርፍ ቤተሰብ እና የቆሰለ ሕጻን የሚል አዲስ ምህጻረ ቃል እንዲፈጠር አድርጓል። ወ/ሮ ጃኔት በዚህ ላይ አስተያየት ሲሰጡ፣ ይህ ግጭት በጋዛ ውስጥ ባሉ ቤተሰቦች ላይ ይህን ያህል አስከፊ ተጽእኖ ማሳደሩን ገልጸው፥ የሕዝብን ብዛት ሲመለክቱ ብዙ ቤተሰብ ያሏቸው ቤተሰቦች በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ አብረው እንደሚኖሩ ገልጸው፥ ስለዚህ አንድ ሕንፃ በቦምብ ሲመታ ሙሉ ቤተሰብ እንደሚሞት አስረድተዋል።

“ምህጻረ ቃሉ እንደሚለው፥ በሕይወት የሚተርፉ የቤተሰብ አባላት የሌላቸው ሕጻናት ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው” ሲሉ አክለዋል። በእርግጥ ይህ እውነታ በራሱ አሳዛኝ እንደሆነ እና የእነዚህ ሕጻናት እና የሕዝቡ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከባድ ስጋት እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የጋዛ የወደፊት እጣ ፈንታ በመልሶ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በግጭቱ የተሰባበሩ ቤተሰቦችን እና ማኅበረሰቦችን መልሶ የመገንባት ትልቅ ተግባር ላይ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ገልጸው፥ ወላጆቻቸውን ያጡ በርካታ ሕጻናት እና የሚወዷቸውን ያጡ በርካታ ቤተሰቦች ሲኖሩ ማኅበረሰቡን መልሶ ማቋቋም እና ማስተዳደር እጅግ ከባድ ሥራ ይሆናል” ብለዋል ወ/ሮ ጃኔት።

ጦርነት ለሁሉም ሰው ሽንፈት ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ "በጦርነት አሸናፊ የለም" በማለት የሰጡትን የማስጠንቀቂያ መልዕክት የደገሙት ወ/ሮ ጃኔት፥ የአሁኑ ቀውስ የሚያስከትለውን የረዥም ጊዜ ውጤቶች አስታውሰው፥ “ጋዛ ውስጥ ሰዎች ሁሉን ነገር እያጡ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ግጭቱ አሁን ቢያበቃም ዓመታትን እና ዓመታትን ሊወስድ የሚችል የሕዝቦች መከፋፈል ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ተናግረዋል።

የ “CAFOD” አገልግሎት በጋዛ

የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ወደ ጋዛ ለመግባት ችግሮች ቢኖሩም፣ ድርጅታቸው “ካፎድ” በአገር ውስጥ ድርጅቶች አማካይነት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ወ/ሮ ጃኔት አብራርተው፥ ይህም የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ እና አስፈላጊ የሆኑ አቅርቦቶችን፣ ለተፈናቀሉት ሕጻናት መጠለያን ማመቻቸትን እንደሚያካትት አስረድተዋል።

ካፎድ “CAFOD” የተሰኘው የእንግሊዝ እና የዌልስ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት ዋና ሃላፊ ወ/ሮ ጃኔት፥ ሰዎች ለሰብዓዊ ድርጅቶች ገንዘብ በመለገስ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ አሳስበው የጸሎት እገዛንም ጠይቀዋል።

"በጋዛ እና በሌሎች ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ያልተረሱ መሆናቸውን እና ችግሩን ለመፍታት ሰዎች የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ማወቃቸው አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ የዓለም አቀፍ መሪዎች መፍትሄን በማፈላለግ ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማምጣት የሚያስችል ጥንካሬ እንዲያገኙ ሰዎች በጸሎታቸው እንዲረዷቸው አደራ ብለዋል።

 

17 February 2024, 16:29