ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤  (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፥ ጠንካራ ስሜታዊ ፍቅር

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እንደሚያስተምረው፥ “ይህ የትዳር ፍቅር የሰውን ሁለንተናዊ ጥቅም ያካትታል። ለመንፈስ ስሜቶችና ለእነርሱም አካላዊ መገለጫ ልዩ ክብር ይሰጣል። ለጋብቻ የተገባ ወዳጅነትን ልዩ ባሕርይና መገለጫ ያስከብራል”። በዚህ ምክንያት ደስታ ወይም ስሜት የሌለበት ፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን የሰውን ልብ አንድነት ለማሳየት በቂ አይደለም። “መንፈሳዊያን ሰዎች ሁሉ እንዳረጋገጡት፥ መለኮታዊ ፍቅርና ሰማያዊ ፍቅር የሚፈልጉትን ተምሳሌት የሚያገኙት በወዳጅነት፣ በልጅ ፍቅር ወይም በዓላማ ጽናት ውስጥ ሳይሆን በጋብቻ ፍቅር ውስጥ ነው። ለዚህም ምክንያቱ የጋብቻ ፍቅር ምሉእነት ነው”። እውነታው ይህ ከሆነ ታዲያ ቆም ብለን በጋብቻ ውስጥ ስለሚያጋጥሙ ስሜቶችና ወሲባዊነት የማንናገረው ለምንድነው?

የስሜቶች ዓለም

የጥንት ሰዎች “ጥልቅ የፍቅር ስሜቶች” የሚሉዋቸው ምኞቶችና ስሜቶች ሁሉ በትዳር ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አላቸው። እነዚህ ስሜቶች “ሌላው ሰው” በሚገኝበትና የሌላው ሰው ሕይወት አካል በሚሆንበት ጊዜ ይነቃቃሉ። ሌሎች ነገሮችን መቅረብ የሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ባሕርይ ሲሆን፥ ይህ ዝንባሌ ምን ጊዜም ደስታን ወይም ሥቃይን፣ ፍስሐን ወይም ሐዘንን፣ ርኅራኄን ወይም ፍርሃትን የመሰሉ መሠረታዊ ስሜታዊ ምልክቶች አሉት። እነዚህም ስሜቶች እጅግ መሠረታዊ በሆነ የሥነ-ልቡና ተግባር ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሰዎች በዚህ ዓለም ላይ ይኖራሉ፤ የሚያደርጉትና የሚሹት ነገር ሁሉ በስሜት የተሞላ ነው።

ኢየሱስ እውነተኛ ሰው በመሆኑ ስሜቶቹን ገለጸ። ኢየሩሳሌም ባልተቀበለችው ጊዜ አዘነ (ማቴ. 23፡ 27)። በዚህም ምክንያት አለቀሰ (ሉቃ. 19፡ 41)። እንደዚሁም በሌሎች ሰዎች መከራ እጅግ አዘነ (ማር. 6፡ 34)። ሐዘናቸው እጅግ ተሰማው (ዮሐ. 11፡ 33)። በጓደኛው ሞት አለቀሰ (ዮሐ. 11፡ 53)። እነዚህ የስሜታዊነቱ ምሳሌዎች ሰብዓዊ ልቡ ምን ያህል ለሌሎች ክፍት እንደ ሆነ ያሳያሉ፡፡

ስሜትን መለማመድ በራሱ ከግብረ ገብ አኳያ ጥሩም መጥፎም አይደለም። የምኞት ወይም የጥላቻ ስሜት መቀስቀስ ኃጢአትም የሚያስነቅፍም አይደለም። ከግብረ ገብ አኳያ ጥሩ ወይም መጥፎ የሚሆነው በተወሰነ ስሜት ላይ ተመሥርተን ወይም በዚያ ስሜት ተጽዕኖ ሥር ሆነን የምናደርገው ነገር ነው። ሆኖም ስሜቶች ሲቀሰቀሱ ወይም ሲፈለጉ ከዚህም የተነሣ ክፉ ድርጊት ብንፈጽም፥ ይህ ክፉ ነገር እነዚህን ስሜቶች ለማቀጣጠል ለሚደረግ ውሳኔና ለክፉ ድርጊቶቹ ውጤት ምክንያት ይሆናል። በተመሳሳይ፥ በአንድ ሰው ውበት መማረኬ ወዲያው ጥሩ ነገር ነው ማለት አይቻልም። በዚያ ሰው መማረኬ ግን እርሱን ወይም እርስዋን ለመጫን ከሆነ ስሜቴ የሚያገለግለው ራስ ወዳድነቴን ብቻ ነው። “ደስታ ስለሚሰማን” ብቻ ጥሩዎች ነን ብለን ማመን ትልቅ ቅዠት ነው። ለመወደድ ትልቅ ፍላጎት ስላላቸው ብቻ በትልቁ የማፍቀር አቅም አለን ብለው የሚያስቡ፥ ነገር ግን ሌሎችን የሚያስደስት ነገር የማድረግ ጥረት የሌላቸው ሰዎች አሉ።  እነዚህ ሰዎች በራሳቸው ፍላጎቶችና ምኞቶች የተጠመዱ ናቸው። እነዚህን የመሰሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ስሜቶች ከትልልቆቹ እሴቶች ይርቃሉ። ጤናማና ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት እንዳይዳብር የሚያደርገውን ራስን ብቻ ወዳድነትን ይደብቃሉ። ጥልቅ ስሜት ከነጻ ምግባር ጋር ከተያያዘ የዚያን ድርጊት ጥልቀት ያሳያል። የጋብቻ ፍቅር የሰው ስሜታዊ ሕይወት መላውን ቤተሰብ የሚጠቅምና የዚያን ቤተሰብ የጋራ ሕይወት የሚያገለግል መሆኑን ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋል። አንድ ቤተሰብ ጠንካራ የሚሆነው የአባላቱ ስሜታዊ ሕይወት ታላላቅ ውሳኔዎችንና እሴቶችን የሚያፍን ሳይሆን የእያንዳንዱን ነጻነት የሚከተል፣ ከእርሱም የሚመነጭ፣ ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ እርሱን የሚያዳብር፣ የሚያጠራና የሚያስማማ የስሜት ዓይነት ሲሆን ነው።

እግዚአብሔር የልጆቹን ደስታ ይወዳል

ይህ ነገሮችን የመተው ውሳኔን ያካተተ የትምህርት ሂደትን ይጠይቃል። ይህ የቤተ ክርስቲያን አስተሳሰብ የሰውን ደስታ ይቃረናል በሚል ሰበብ ብዙ ጊዜ ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቶአል። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነድክቶስ 16ኛ፥ “ቤተ ክርስቲያን በትእዛዛትዋና በክልከላዎችዋ ሁሉ በሕይወት ውስጥ እጅግ ክቡር የሚባለውን ነገር ወደ ምሬት አትቀይረውምን? የፈጣሪ ስጦታ የሆነው ደስታ በራሱ መለኮታዊ ተምሳሌት የሆነውን ደስታ ሲሰጠን እምቢልታ አትነፋምን?” በማለት ይህን ክስ በታላቅ ግልጽነት አጠቃልለውታል። በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ የተጋነኑና አፈንጋጭ የብህትውና ዓይነቶች የነበሩ ቢሆንም፥ የቤተ ክርስቲያን ይፋ አስተምህሮ ለቅዱሳት መጻሕፍት ታማኝ በመሆን፥ “ፍቅርን ራሱን አልጠላውም፣ በሽፍንፍንና አጥፊ በሆነው የፍቅር ዓይነት ላይ ጦርነት አወጀ እንጂ። ምክንያቱም አስመሳይ የፍቅር አምልኮ … የፍቅርን መለኮታዊ ክብር ይገፍፋል፤ ሰብዓዊ ክብሩንም ያዋርዳል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ስለዚህ በስሜትና በተፈጥሮ ባሕርይ ዙሪያ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል። ይህም አንዳንዴ ገደብ ማስቀመጥን ይጠይቃል። ከልክ ያለፈ፣ ቁጥጥር የሌለበት ወይም መሳጭ የደስታ ዓይነት የኋላ ኋላ ደስታን ያዳክማል፣ ያጎድፋል ፣ የቤተሰብ ሕይወትንም ይጎዳል። አንድ ሰው ጥልቅ ስሜቶቹን ወደ ውብና ጤናማ መንገድ እንዲያመሩ፣ ይበልጥ ለሌሎች ጥቅም ቅድሚያ ወደሚሰጥና በቤተሰብ ልብ ውስጥ የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ወደሚያዳብር የተቀናጀ የግል ስኬት እንዲያተኩሩ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ማለት ግን ጥልቅ የሆነ ደስታ የሚገኝባቸውን ወቅቶች መተው ሳይሆን ይልቁንም ከሌሎች የልግስና፣ የትዕግሥት፣ የተስፋና ዓላማን ለማሳካት ከሚደረግ አድካሚ የትግል ወቅቶች ጋር ማቀናጀት ነው። የቤተሰብ ሕይወት ማለት ይህ ሁሉ ስለሆነ በሙላት መኖር ይገባል፡፡

አንዳንድ የመንፈሳዊነት ፈርጆች፣ ከሥቃይ ተላቅቆ በነጻነት ጎዳና ለመራመድ ከተፈለገ ምኞት መጥፋት አለበት ሲሉ ያስተምራሉ። እኛ ግን እግዚአብሔር የሰዎችን ደስታ እንደሚወድ እናምናለን። ፈጣሪያችን “ደስ እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ ይሰጠናል (ጢሞ. 6፡17)። በታላቅ ፍቅሩም፥ “ልጄ ሆይ፣ በሚቻልህ መጠን ራስህን በመልካም አስተዳደር አዘጋጅ… የዛሬው ደስታ አያመልጥህ” (ሲራክ 14፡ 11-14) ብሎ ሲነግረን ሐሤት እናድርግ። እንደዚሁም ባለትዳር ጥንዶች “ጊዜው መልካም ሲሆን ደስ ይበልህ” (መክ. 7፡14) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ ሲሰሙ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ምላሽ ይሰጣሉ። ስለዚህ ቁም ነገሩ፣ ደስታ በተለያዩ የሕይወት ጊዜያት የሚከሰት፣ በጋራ ፍቅር ፍላጎት ላይ የተመሠረተና የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት መሆኑን በነጻነት ማወቅ መቻል ነው። በዚህ ረገድ ዕይታችንን በሚጋርደን በአንድ ውስን ተሞክሮ እንዳንጠመድ ንቃተ ኅሊናችንን እንድናሰፋ የሚያበረታቱንን አንዳንድ የምሥራቅ ሊቃውንት ማመስገን እንችላለን። ንቃተ ኅሊናን ማስፋት፣ የማስፋቱንና የማጥራቱን ያህል ምኞትን መካድ ወይም ማጥፋት አይደለም።

ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርዕሠ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 136- 149 ላይ የተወሰደ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳልን።

አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ ዳንኤል ኃይለ

10 February 2024, 17:26