ፈልግ

የየካቲት 17/2016 ዓ.ም ዘጥምቀት - አስተርእዮ 6ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ የየካቲት 17/2016 ዓ.ም ዘጥምቀት - አስተርእዮ 6ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ  (©khanchit - stock.adobe.com)

የየካቲት 17/2016 ዓ.ም ዘጥምቀት - አስተርእዮ 6ኛ ዕለተ ስንበት አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት

1.     ዕብ. 12፥12-21

2.     2ኛጴጥ. 1፥19-25

3.     ሐዋ.ሥ. 7፥29-34

4.     ዮሐ. 10፡34-42

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በሕጋችሁ፣ ‘እናንት አማልክት ናችሁ አልሁ’ ተብሎ አልተጻፈምን? የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ‘አማልክት’ ካላቸውና መጻሕፍም ሊሻር የማይቻል ከሆነ፣ ታዲያ፣ ‘የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ’ ስላልሁ፣ አብ ለራሱ ለይቶ የቀደሰውንና ወደ ዓለም የላከውን፣ ተሳድበሃል ብላችሁ ለምን ትወነጅሉኛላችሁ? አባቴ የሚያደርገውን ባላደርግ አትመኑኝ፤ የማደርገው ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ፣ አብ በእኔ እንዳለ እኔም በአብ እንዳለሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ታምራቱን እመኑ” እንደ ገናም ሊይዙት ሞከሩ፤ እርሱ ግን ከእጃቸው አመለጠ።

ከዚያም ኢየሱስ፣ ቀደም ሲል ዮሐንስ ያጠምቅበት ወደነበረበት፣ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ተመለሰ፤ በዚያም ሰነበተ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጡ። እነርሱም፣ “ዮሐንስ አንድም ታምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ነገር ግን ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ” አሉ። በዚያም ስፍራ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ።

 

የእለቱ አስተንትኖ

በእግዚአብሔር የተወደዳችሁና የተመረጣችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ከሁሉ አስቀድሜ የእግዚአብሔር ፀጋና ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን እያልኩ፤ እንደሚታወቀው ያለንበት ወቅት እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር  ዘጥምቀት - አስተርእዮ 6ኛ ሰንበትን እናከብራለን።

በዚህም ወቅት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የተገለጠበትን ጊዜ እያሰብን በዚህ አጋጣሚ በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ቆም ብለን በማጤን  የምንታደስበት የምንለወጥበትና አዲስ ሰው ወይም ፍጡር በሁለንተናችንና በተለይም በክርስትና አማካይነት የተቀበልነውን ኃላፊነት የምንወጣበት እና የምንለማመድበት ወቅት ነው።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ሲያስተምረን እኛ ክርስቲያኖች ደህንነታችን የተጠበቀ ሆኖ እንዲገኝ ከሁሉ በላይ የቅድስና ኑሮ እንደሚያስፈልገን አበክሮ ይመክረናል። “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ በቅድስናም ለመኖር ትጉ ምክንያቱም ያለቅድስና ማንም እግዚአብሔርን ማየት አይችልም” (ዕብ 12፥14) ይለናል።

የአንድ ክርስቲያን የህይወቱ የመጨረሻ ግቡ እግዚአብሔርን ማየት ነው ወይም የእርሱ ክብር ተካፋይ መሆን ነው። እግዚአብሔርን ደግሞ በሁለቱ የሕይወታችን ጉዞአችን ውስጥ እናገኘዋለን አንደኛው በምድራዊ ጉዞአችን ለሰማያዊ ጉዞአችን ነፀብራቅ ነው። እኛ ክርስትያኖች እንደመሆናችን መጠን የየዕለት ኑሮአችን ጤናማ እና እንደ ክርስቲያን የተለየ መሆን አለበት፤ ይህም ማለት አካሄዳችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የተቆራኘ እና የተጣበቀ መሆን ይገባዋል። ለእዚህም መመዘኛና ማረጋገጫው የቅድስና ሕይወት ነው።

የቅድስና ሕይወት ማለት እንከን የለሽ ሕይወትን መኖር አልያም ምንም ኃጢአት ሳይሰሩ መኖር ማለት አይደለም። ይልቁንስ በኃጢአት ቀንበር በምንያዝበት ወቅት እና ከቅድስና ሕይወት መስመር በምንስትበት ጊዜ ከኃጢአት ጋር ተጋድሎ የምናደርግበት መሣርያ ነው። ይህንንም ቃል ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልዕክቱ አበክሮ ይገልጽልናል። “ስለዚህ የእግዚአብሔርን የጦር መሣርያ በሙሉ አንሱ፣ በዚህ ሁኔታ ክፉ ቀን ሲገጥማችሁ የጠላትን ኃይል መቃወምና እስከመጨረሻም ከተዋጋችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁ” (ኤፌ 6፥13)   በምድራዊ ሕይወት እስካለን ድረስ ሁላችንም የክርስቶስ ወታደሮች ነን።

ሙሉ ለሙሉ የቅድስና ሕይወታችንን ታጥቀን በተጋድሎ እንኖር ዘንድ ክርስቲያናዊ ኃላፊነት አለብን፤ ይህም ትጥቃችን የእግዚአብሔር ቃል እና ምስጢራት ናቸው። በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ቃል ከከበረው ዕንቁ በላይ ልንከባከበው የሕይወታችን መሣርያ ልናደርገው ይገባል ምክንያቱም ቃሉ ለሕይወታችን ስንቅ ለመንገዳችን ብርሃን ነውና። በኃጢአት በምንወድቅበት ወቅት እንደገና ኃይል የሚሰጠን ከጸጋው ሙላት እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህም ለቅድስና ሕይወታችን ጉዞ ስንቅ ይሆነን ዘንድ በቃሉና በምስጢራቱ በሙላት በመሳተፍ ከሁሉ አብልጠን በልባችን ልንይዘው፣ ልንለማመደው፣ የእራሳችን ልናደርገው እና ዕለት በዕለት መሣርያችን ልናደርገው ይገባል።

ከእዚህም ጋር በማያያዝ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በም. 1፡13-16 እንዲህ ይለናል “ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ እራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁ እየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ። ታዛዦች ልጎች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ተጽፎአልና። እንዲሁም በብሉይ ኪዳን “እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ ጌታ ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (ዘሌ. 11፥45) በማለት እግዚአግሔር እርሱን እንድንመስል በቃሉ ይመክረናል።

ሁልጊዜም በቅድስና ለኖር ስንተጋ በክርስቶስ በተሰጠን ጸጋ እና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በየጊዜው እግዚአብሔር ቅዱሳን ያደርገናል። ከዚያ በተጨማሪ ግን እኛ ራሳችንም ቅዱሳን ለመሆን መትጋት አለብን። የምንቀደሰውም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ብቻ ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ ለእኛ የትሕትና ብቻ ሳይሆን ይመታዘዝ ምሳሌ ነው።  “በትሕትና ራሱን ዝቅ አደረገ፤ በዚህም የመስቀልን ሞት እንኳ በመስቀል እስከ ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ” (ፊል.2፥8)።

በሐዋርያት ሥራ በዛሬው መልዕክት ላይ የምናገኘው “ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ  አለው”  (ሐዋ. 7፥3) እውነት ነው ካልተለየንና የቅድስና ሕይወትን መኖር ካልተለማመድን የእግዚአብሔርን ክብር ማየት አይቻልም፤ ሙሴ ከኃጢአት ይነፃ ዘንድና እስራኤላውያንንም ለእግዚአብሔር በቅድስና ያቀርብ ዘንድ አስቀድሞ እራሱን ለአምላኩ ክብር ቀደሰ፣ ለየ፤ በቁጥቋጦ ውስጥም ያናገረው መልአክ ሙሴን ከፊቱ ለሚጠብቀው የቅድስና ሕይወትና ጉዞ ኃይል አስታጠቀው።

የዛሬው የወንጌል መልዕክትም ይህንን ያጠናክርልናል፤ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በቅድስና እንኖር ዘንድና ፍሬም እንድናፈራ ይጋብዘናል። የእርሱ ዋናው ተልዕኮ እኛን ለቅድስና ሕይወት ማብቃት ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ “ታድያ አብ የቀደሰውንና ወደዓለም የላከውን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላለ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ትናገራለህ ትሉታላችሁን? እኔ የአባቴን ሥራ የማልሠራ ከሆንኩ ግን በእኔ እንኳን ባታምኑ በሥራዬ እመኑ በዚህ ዓይነት አብ በእኔ እንደሆነና እኔም በአብ እንደሆንኩ በሚገባ ታውቃላችሁ” (በዩሐ 7፥36 – 38 ) በማለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ስለ ተልዕእኮውና ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ኅብረት ይናበራል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እራሱ በብዙ መልኩ በምሳሌ በማስተማርና ምሳሌ በመሆን በሕይወታችን የሚከብደንንና ልንወጣ የማንችለው የሚመስለንን ነገር ያስተምረናል። ይህንንም በእራሱ ሕይወት ሰው ሆኖ እንደሰው እና የሰው ልጅ ሊቋቋመው በማይችለው መንገድ ፈተናን በመቀበልና በመኖር በመራብ፣ በመሰቃየት፣ በምድረበዳ ክብደቱን ለመግለጽ የሚይስቸግር መስቀልን በመሸከም ረጅም መንገድ በመጓዝና በመስቀል ላይ በመሞት ከአብ ጋር በመሆን ሁሉንም ፈተና በድል ተወጥቷል። ይህም ዛሬ ለሁላችንም የሕይወት ምሳሌአችን ነው።

በክርስትና የቅድስና ጉዞአችን ፈተና ሲገጥመን እና ይህንን ማለፍ የተሳነን ሲመስለን ልክ እንደ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር በመጣበቅ የእርሱን ሕይወት በመመልከት ለኃጢአት እጃችንን ሳንሰጥ ዳግም ከወደቅንበት በመነሣት ወደ ቅድስና የሕይወት መስመር ውስጥ መመለስ ይገባናል።

በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ እንዳለን ሁሉ ዕለት ተዕለት ዲያቢሎስን እየተቃወምነው መንፈሳዊ ጉዞአችንን እንድንቀጥል በቃሉ ይመክረናል በሕይወቱም ምሳሌ ይሆነናል። “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም ውጪ እንድትወስዳቸው አይደለም።” (ዮሐ. 17፥15)  ስለዚህም የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ወደ ፀጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ ከፀጋው ሙላት እንካፈል የሚያበረታን መንፈስ እርሱ ራሱ ይሰጠናል፤ እንዲሁም በቅድስና በመኖር ተጋድሎን እያደረግን ከእርሱ ጋር ደስ የሚያሰኝ ሕይወትን እንኑር።

ይህንንም ለማድረግ በቅድስና ሕይወት በመኖር ምሳሌ የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት የሆነች ጸጋና በረከቱን ከልጇ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን የሰማነውንም  የእግዚአብሔር ቃል በሕወታችን ለመተርጎም እንድንችል ልባችንን ያነሳሳልን፡፡

ምንጭ፡ ሬዲያ ቫቲካን የአማርኛው ክፍል

        

 

24 February 2024, 12:10