ፈልግ

ወደ ቻድ የሚሸሹ የሱዳን ተፈናቃዮች (ከማኅደር) ወደ ቻድ የሚሸሹ የሱዳን ተፈናቃዮች (ከማኅደር)  (ZOHRA BENSEMRA)

የሱዳን ብጹዓን ጳጳሳት ጦርነቱን ለማስቆም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያግዝ ጠየቁ

የሱዳን የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በጦርነት የምትሰቃይ ሱዳን ሁኔታ አስመልክተው ባወጡት የጋራ መግለጫ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሀገሪቱ ያለውን ሁከት ለማስቆም የሚያደረገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። በሱዳን ውስጥ የዘለቀው ውጊያ በአገሪቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ሊያደናቅፍ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (RSF) መሪ አቶ መሐመድ ሃምዳን ዳግሎ በሀገራቸው ለዘጠኝ ወራት ያህል የዘለቀውን ጦርነት የሚያስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ድጋፍ ለማግኘት አህጉራዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

በሱዳን ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳዊው ከሚያዝያ 15/2023 ዓ. ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት በሱዳን ጦር ሃይሎች (SAF) እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (RSF) መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተቀሰቀሰ እንደሆነ ይታወቃል። ብጥብጡ የተጀመረው በዋና ከተማይቱ ካርቱም ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመላ የአገሪቱ ክፍሎች ተስፋፍቶ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና የጦር ወንጀሎች እየታዩ እንደሆነ ይነገራል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግጭቱ በድርድር እንዲፈታ ደጋግመው የጠየቁ ሲሆን፥ በቅርቡ በተከበረው የአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓልን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥ በሱዳን ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዳይዘነጋው ጠይቀው፥ የሳህልን አካባቢን፣ የአፍሪካ ቀንድን እና ሱዳንን የሚያስጨንቁ ውጥረቶችን እና ግጭቶችን መርሳት እንደማይገባ አደራ ብለዋል።

የሱዳን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጥሪ

በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በጋራ ባወጡት መግለጫ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኖርዌይ እንዲሁም ትሮይካ እየተባለ የሚጠራው - እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት በአካባቢው እየደረሰ ያለውን ሁከት ለማስቆም የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም በአመጽ ለተጎዱ አካባቢዎች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የሱዳን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ታኅሣሥ 16/2016 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፥ ሱዳን ውስጥ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ በመቃወም፥ ግጭቱ ከፍተኛ የሰው ሕይወት እና የንብረት ውድመት እያስከተለ መሆኑን ገልጸው፥ ይህን የመሰለ አሳዛኝ ክስተት ፈጽሞ ያልጠበቁት በመሆኑ ብዙዎችን እንዳስገረማቸው ገልጸዋል።

ግጭቱ የረዥም ጊዜ አምባገነን መሪ የነበሩት ኦማር አልበሽር ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ጦር ኃይሉን በሚመሩ ጄኔራሎች፣ በጥቃቅን ቡድኖች መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ እና በሱዳን ወታደራዊ እና የሲቪል ባለስልጣናት መካከል በተደረገው ወደ ሲቪል መንግሥት የሽግግር ማዕቀፍ ስምምነት ውጤት እንደሆነ ይነገራል።

በግጭቱ ወቅት የሚፈናቀልሉ የሰላማዊ ዜጎች ችግር በማስመልከት ብጹዓን ጳጳሳቱ በመግለጫቸው እንደገለጹት፥ በዳርፉር እና በኮርዶፋን ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ምዕምናን ተግዳሮቶችን በሐዘን ሲገልጹ፥ መንደሮች በእሳት መጋየታቸውን እና ዜጎች ያለ መጠለያ መቅረታቸውን ገልጸዋል።

የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ወዲህ ተዋጊ ጄኔራሎቹ ፊት ለፊት አለመገናኘታቸው ሲታወቅ፥ ነገር ግን ሁለቱ የአንጃ መሪዎች መሐመድ ሃምዳን ዳግሎ እና የሱዳን ጦር አዛዥ አብደል ፋታህ አል ቡርሃን በመካከላቸው ውይይት ለማካሄድ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል።

የመሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ መላው ሱዳንን በኃይል ለመያዝ ቀጣናዊ ድጋፍ ለማግኘት ነው” ሲሉ ተንታኞች ስጋታቸውን ገልጸዋል። ባለፈው ወር የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ለሱዳን የዳቦ ቅርጫት የሆነችውን የጌዚራ ግዛት በቁጥጥር ስር ማዋላቸው፥ ቡድኑ በጦር ኃይሉ ላይ የበላይነት እንዲኖረው አድርጎታል ተብሏል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች በተንሰራፉባቸው ምዕራባዊ የዳርፉር ክልል ውስጥ በርካታ ጦር ሠፈሮችን መማረኩ ሲንገር፥ በአሜሪካ ድጋፍ በጄዳ እና በሳዑዲ አረቢያ የሚደረገው የሽምግልና ጥረት ከረጅም ጊዜ ማቋረጥ በኋላ ሊጀምር እንደሆነ ተገልጿል።

ጸሎት ኃይል አለው!

የሱዳን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በመግለጫቸው፥ በሱዳን የሚገኙ የተለያዩ ፓርቲዎች መሪዎች የሕዝቡን ጥቅም ለማስቀደም፥ ለፖለቲካ ሥልጣን በሚያደርጉት ትግል ላይ ለማሳተፍ የተለያዩ መድረኮችን ለመጠቀም የገቡትን ቃል እንደሚጠብቁ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በመግለጫቸውም፥ “ጉልበት የሚገኘው ከጸሎት ኃይል ነው” ያሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፥ የሱዳን ሕዝብ በዘለቀው ግጭት ተስፋ እንዳይቆርጥ አደራ ብለው፥ ይልቁንም “ከመከራ ሁሉ በላይ በሆነው እና ተስፋን በሚሰጥ እግዚአብሔር እንዲታመን” በማለት አሳስበዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ አክለውም፥ ግጭቱ በሱዳን ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለማደናቀፍ የተደረገ ሴራ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸው፥ ሱዳን ውስጥ ያለው የተራዘመ ግጭት ሕዝቦች በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት የሚኖሩበትን የማኅበረሰብ ፍላጎት ለመግታት የሚደረግ ሙከራ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ጠንካራ ስሜት ገልጸዋል።

 

03 January 2024, 15:14