ፈልግ

የፍልስጤም ሴቶች በዘመዶቻቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የፍልስጤም ሴቶች በዘመዶቻቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ  

አባ ፋልታስ ‘ሴቶች የሰላም መሳሪያ ናቸው’ አሉ

በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ ‘ላ ኦዘርቫቶር ሮማኖ’ ለሚባለው ዕለታዊ የጣሊያን ጋዜጣ በፃፉት ፅሁፍ ሴቶች ትልቅ የሰላም ምስክሮች እና ምንጮች እንደሆኑ ቢታወቅም በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በአማካይ በየሰዓቱ ሁለት ሴቶች ይገደላሉ ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አባ ፋልታስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ታህሳስ 22 በሚከበረው የዓለም የሰላም ቀንን ለማስታወስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባደረጉት ስብከት “አንዲትን ሴት የሚጎዳ ሁሉ እግዚአብሔርን እንዳረከሰ ይቆጠራል” ማለታቸውን በማስታወስ፥ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣውን ዘገባ “መስከረም 26 በተጀመረው የእስራኤል - ሃማስ ጦርነት በጋዛ ውስጥ በአማካይ በየሰዓቱ ሁለት ሴቶች ይገደላሉ፥ እንዲሁም አጠቃላይ ከሞቱት ሰዎች መሃል ሴቶች እና ህጻናት 70 በመቶውን ይይዛሉ”ብለዋል።

አባ ፋልታስ ሴቶች ላይ እየደርሰ ያለውን ጉዳት ሲገልጹ በቅርብ ቀናት ውስጥ የተከሰተውን አሳዛኝ ክስተት በመጥቀስ “ቅዳሜ ዕለት እስራኤል ባደረሰችው የቦምብ ጥቃት አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ከባድ ጉዳት ደርሶባት ሆስፒታል የገባች ቢሆንም ዶክተሮቹ ሕፃኑን ማትረፍ ቢችሉም እናቲቱ ግን ሞታለች” ብለዋል።

“...እግዚአብሔርን ያረክሳል” ፣ “ከሴት የተወለደ” የሚለውን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱን ቃል መለስ ብዬ አሰብኩ ይላሉ ካህኑ።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምድርና በሰማይ መካከል አገናኝ ድልድይ ነች፥ እሷ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሰምታ ተቀበለች፥ ውጤቱንም ተቀበለች፥ እሷ አስተዋይ ፣ ልባም እና ብዙ የተሰቃየች እናት ነበረች። የማሪያም ህይወት ለአማኞች እና እምነት ለሌላቸው፣ ለእናቶች፣ ለቅዱሳን፣ አጠቃላይ ለሁሉም ሴቶች እንዴት ያለ ምሳሌ ነው! በማለትም ጠቅሰዋል።

በቤተክርስቲያንም ሆነ በሲቪል ማህበረሰብ ውስጥ የሴቶችን ሚና እንድናከብር ቅዱስ አባታችን ብዙ ጊዜ ጥሪ ያቀርቡልናል። ሴቶች በተፈጥሮ ባላቸው የውስጥ ጥንካሬያቸው እና ለጎረቤቶቻቸው ባላቸው ቁርጠኝነት በዓለም ላይ ሰላምን ለመገንባት አስፈላጊ መሆናቸውን እርግጠኛ ነኝ ይላሉ አባ ፋልታስ።

"ሴቶች እራስ ወዳድነት የማያውቁ፣ ለሁሉም የጋራ ህይወት ጉዳዮች ሃላፊነት የሚወስዱ፥ እራሳቸውን እና የጎረቤታቸውን ህይወት ለማሻሻል በጎውን የሚመርጡ ለዚህም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አይቻለሁ፥ ሰብዓዊነትን በትኩረት እና በዝምታ አይን በሚመለከቱ፣ ለሌሎች ጥቅም ስቃይን በሚቀበሉ፣ ፍላጎቶችን በሚገነዘቡ እና ለዚህም በቁርጠኝነት በሚሰሩ እናቶች እና ሴቶች ልብ እንድንመራ መፍቀድ አለብን"ብለዋል።

እኔ በእግዚአብሔር ቸርነት በዝምታ እና በመስዋዕትነት ህይወቷን ለልጆቿ፣ ለቤተሰቧ እና ለድሆች የሰጠች፣ ሃይማኖተኛ ሴት የሆነችዋን እናቴን እንደ ተምሳሌት አያት ነበር። ሴቶች የሰላም መሳሪያ ሊሆኑ ይችላሉ፥ ራሳቸውን ለክፉ ነገር አሳልፈው አይሰጡም፥ ለመፈወስ እና ለመጠበቅ ይፈልጋሉ፣ ሀብቶችን እና ግንኙነቶችን እንዴት ማስተዳደር እንደሚችሉ ያውቃሉ፣ በቸልተኝነት ወይም በመርሳት የማይሞት እውነተኛ ፍቅር እንዲጎድል በፍጹም አይፈቅዱም” በማለት የሴቶችን ጥንካሬ አብራርተዋል።

"ያ የእናት ፍቅር፥ ልጇን ሳታያት እና በእቅፏ መያዝ ከመቻሏ በፊት ቀድማ የወደደቻን፥ ያቺን በጋዛ ወላጅ አልባ ሆና የተወለደችውን ትንሿን ህፃን አምላክ በቸርነቱ እንዲያድን አድርጓል" ካሉ በኋላ፥ "እነዚህን ንፁሀን ተጎጂዎችን፣ የሞቱትን እንዲሁም የተረፉትን አንርሳ፥ የእናቶችን ፍቅር እና የሴቶችን ጥንካሬ አንርሳ" ብለዋል።

ይህንን ሰብአዊነት የተሻለ ለማድረግ እና ጥላቻን እና ጥቃትን ለማሸነፍ የሴቶችን ክብር እንጠብቅ ፣ እንከላከልላቸው እንዲሁም እናክብራቸው። በማለት ጽሁፋቸውን ደምድመዋል በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት አባ ኢብራሂም ፋልታስ::
 

25 January 2024, 15:22